. 1 ሺ 800 ዕድሜ ጠገብ ዛፎች ከተለያዩ አካባቢዎች ተጓጉዘው ቤተመንግስት አካባቢ ተተክለዋል
. ዕጽዋቶቹን የሚንከባከቡ ከ300 በላይ የቀን ሰራተኞች እና 35 የዕጽዋት ባለሙያዎች በሥራ ላይ ናቸው
አዲስ አበባ፡- በቻይናውያን እየተገነባ በሚገኘው የሸራተን አካባቢ ፓርክ ውስጥ በቋሚነት ለመትከል ታስቦ በልዩ ቴክኒክ ከተለያዩ አካባቢዎች ተጓጉዘው የመጡ 1ሺ 800 ዕድሜ ጠገብ ዛፎች መተከላቸውን ባለሙያዎች ገለጹ።
በቻይና መንግስት እየተገነባ በሚገኘው እና የሸገር ማስዋብ ወንዝ ዳርቻ ፕሮጀክት አካል በሆነው የሸራተን አካባቢ ፓርክ ግንባታ የዕጽዋት ባለሙያ አቶ ወንድዬ ከበደ እንደገለጹት፤ ፓርኩን ለማስዋብ የሚያስችሉ በመጀመሪያው ዙር ብቻ 1 ሺ 800 ዕድሜ ጠገብ ዛፎች ከተለያዩ ቦታዎች ሳይንሱን በጠበቀ መንገድ ተነቅለው ቤተመንግስት አካባቢ ተተክለው ልዩ እንክብካቤ እየተደረገላቸው ይገኛል።
እንደ አቶ ወንድዬ ገለጻ፤ በመናፈሻው ውስጥ በአንድ ዙር እስከ 3 ሺ 800 ያደጉ ዛፎችን ከተለያዩ ቦታዎች አንቀሳቅሶ ዳግም ለመትከል እቅድ አለ። ለዚህም እንዲረዳ ከተለያዩ የአዲስ አበባ አካባቢዎች በግንባታ እና መንገድ ስራ ምክንያት ሊቆረጡ የነበሩ ዛፎችን በሳይንሳዊ መንገድ ከነስራቸውና ከነአፈሩ ነቅሎ በማምጣት ልዩ እንክብካቤ እየተደረገላቸው ይገኛል። እንደ ወይራ፣ ግራር፣ ጥድ፤ ዘንባባ እና ሞጣ የመሳሰሉ 50 ዓመት የሞላቸው ሀገር በቀል ዛፎችም ልዩ እንክብካቤ አግኝተው ዳግም ህይወት ዘርተዋል። ከአምስት ሜትር በላይ ቁመት ያላቸው እና ግዙፍ ዛፎቹም በቤተመንግስት ፊት ለፊት በሚገኘው መናፈሻ ውስጥ ተተክለው ጥሩ አየር እንዲሰጡ ይደረጋል።
የፓርኩ ግንባታ የዕጽዋት ባለሙያ አቶ ካሌብ ምንውዬለት በበኩላቸው እንደገለጹት፤ በሳይንስዊ መንገድ እንዲነቀሉ ተደረገው የተንቀሳቀሱት ዛፎች አንዳንዶቹ ለመንገድ ማካፈያ የማይመቹ ቢሆኑም ተተክለው ትቦዎችን እና መንገዶችን ሲያፈራርሱ የነበሩ ናቸው። የተቀሩት ደግሞ ከተለያዩ የከተማዋ አካባቢዎች ተንቀሳቅሰው የመጡ ናቸው። በመሆኑም ዛፎቹ ተንቀሳቅሰው እንዲመጡ ሲደረግ በተነሱበት አካባቢም ያለውን ችግር ያቃልላሉ። ዛፎቹም በልዩ እንክብካቤ ከቆዩ በኋላ በፓርኩ ውስጥ ሲተከሉ እያንዳንዳቸው በተቀመጠላቸው የጂፒኤስ አድራሻ መሰረት ነው።
እንደ አቶ ካሌብ ከሆነ፤ ዛፎችን መቁረጥ ሳይሆን አንቀሳቅሶም ማሳደግ እንደሚቻል የታየበት ስራ ለኢትዮጵያ አዲስ ቢሆንም ውጤታማ ነገር ታይቶበታል። የቻይና መንግስት ድጋፍ ባደረገበት ግንባታ አጠቃላይ የፓርኩ ስራ ከተጀመረ ሁለት ወራት ሲሆነው የመሬት ዝግጅቱ እየተጠናቀቀ በመሆኑ በቀጣይ ወር የአበቦች እና የዛፎቹ ተከላ ይከናወናል። የተንቀሳቀሱትን ዛፎች እና ሌሎች ችግኞችን ለመንከባከብ ከ300 በላይ የቀን ሰራተኞች እና 35 የዕጽዋት ባለሙያዎች በስራ ላይ ናቸው።
ከዛፎቹ በተጨማሪ በርካታ የአበባ ዝርያዎች እየተባዙ መሆኑን የተናገሩት አቶ ካሌብ፣ ሰፊ ግሪን ሃውስ ተዘጋጅቶ በሁለት ወራት ውስጥ በመቶሺዎች የሚቆጠሩ አበቦች እንዲባዙ መደረጉን ገልጸዋል። በመሆኑም በፓርኩ ለሚገነባው ሰው ሰራሽ ሀይቅ እና ወንዝ ዳርቻዎች እንዲሁም የኢትዮጵያን ባህላዊ አኗኗር ሊገልጹ በሚችሉ ዲዛይኖች ላይ እንዲቀመጡ ይደረጋል።
በፓርኩ ውስጥ በቀላል ወጪ ከፈራረሱ ቤቶች በተገኙ ድንጋዮች እና የተለያዩ ቁሳቁሶች መናፈሻዎች የሚሰሩ ሲሆን እያንዳንዱ ሰው አበቦቹን በፓርኩ እንዲተክል እና የእኔነት ስሜት እንዲያድርበት ይደረጋል። የዚህ ዋና አላማም መናፈሻ መስራት ብቻ ሳይሆን በቀላል ወጪ እና በአካባቢ ከሚገኙ ነገሮች እንዴት ጥሩ መናፈሻ መስራት እንደሚቻል ማሳየት ላይ ያተኮረ መሆኑን አስረድተዋል።
ቻይና በሸገር ማስዋብ ፕሮጀክት 12 ኪሎ ሜትር የወንዝ ዳርቻ ለመገንባት ቃል በገባችው መሰረት መስከረም ወር ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በተገኙበት የሸራተን አካባቢውን ፓርክ ግንባታ በይፋ አስጀምራለች። በፓርኩ ውስጥ ከጅማ፣ ወላይታ፣ አዲስ አበባ ዙሪያ እና ከውጭ ሀገራት ጭምር የመጡ የቡና እና የፍራፍሬ ዛፎች እንዲሁም የዘንባባ አይነቶች እንደሚተከሉ ታውቋል።
አዲስ ዘመን ህዳር 20/2012
ጌትነት ተስፋማርያም