– ግንባታውን በሁለት ዓመት ለማጠናቀቅ ታቅዶ ስድስት ዓመት ወስዷል
ሙከጡሪ፡- በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ውጫሌ ወረዳ ሙከጡሪ ከተማ 275ሺ232 ዜጎችን እንዲያገለግል የተገነባው የሙከጡሪ ሆስፒታል በተቋራጩና አሰሪው አካል መካከል አለመግባባት የመጨረሻው ርክክብ ባለመደረጉና በግንባታው ላይ እንከኖች በመኖራቸው አገልግሎት ላይ ጫና ማሳደሩ ተገለፀ። ተቋራጩ በበኩሉ ኃላፊነቴን በአግባቡ ተወጥቻለሁ ብሏል።
የሆስፒታሉ ሥራ አስኪያጅ አቶ ላስቻለው ሐይማኖት እንዳሉት፤ ግንባታው በ2005 ዓ.ም ተጀምሮ በሁለት ዓመት ውስጥ እንዲጠናቀቅ ውል መገባቱን አስታውሰው ግንባታው በ2011 ዓ.ም መጠናቀቁንና መጀመሪያ ደረጃ ርክክብ መፈፀሙን ገልፀዋል። ይሁንና የመጨረሻ ደረጃ ርክክብ ለማድረግ የሚቀሩ ሥራዎች በመኖራቸውና ተቋራጩ ችግሮችን እንዲያስተካክል በተደጋጋሚ ቢነገረውም ችግሮቹን ለማስተካከል ፍቃደኛ ባለመሆኑ ርክክብ አለመፈፀሙን ጠቁመዋል።
እንደ አቶ ላስቻለው ገለፃ፤ በአሁኑ ወቅት ለሥራ አስቸጋሪ ሁኔታዎች መኖራ ቸውን አብራርተዋል። ለአብነትም ውሃ ማጠራቀሚያ ሮቶ እና ተያያዥ ሥራዎች በአግባቡ ባለመሰራታቸው እና ውሃው ወደ ውስጥ ስለሚሰርግ ከፍተኛ የሆነ የውሃ እጥረት አጋጥሟል። ይሁንና በየወሩ ለውሃ ቆጣሪ ከ6000 እስከ 9000 ብር ክፍያ ይፈፀማል። ከዚህም በተጨማሪ የጣሪያው ኮርኒስ በዝናብ የመበስበስና የመፈራረስ ሁኔታዎች በመኖራቸው ባለሙያዎችም በሥራ ወቅት መቸገራቸውን አብራርተዋል።
በተጨማሪም የተዘረጋው የኤሌክትሪክ መስመርና በሌላ ድርጅት የተተከለ ጀኔሬተር ባለመናበቡ የመብራት መቆራረጥ መኖሩን አስገንዝበዋል። ሆስፒታሉ የችግሩን አስከፊነት ከተቋራጩ ጀምሮ እስከ ክልል ድረስ ጉዳዩ ለሚመለከታቸው አካላት ቢያሳውቅም እልባት እንዳላገኘ ተናግረዋል።
የውጫሌ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ወልደዮሐንስ አበራ በበኩላቸው፤ የሆስፒታሉ ግንባታ ከታቀደለት ጊዜ በላይ የተራዘመ ሲሆን እስካሁን ድረስ ሙሉ ለሙሉ ርክክብ አልተፈጸመም። በአሁኑ ወቅት ደግሞ ከውሃ እና ኤሌክትሪክ መስመር ጋር በተያያዘ ችግር መከሰቱን አብራርተው ይህም በሆስፒታሉ ተገልጋዮች ላይ ቅሬታ እየፈጠረ መሆኑን አስገንዝበዋል።
እንደ አስተዳዳሪው ገለፃ፤ በኦሮሚያ ክልል በተመሳሳይ ወቅት 26 ሆስፒታሎች ተገንብተው የነበረ ሲሆን የሌሎች ሆስፒታሎች ርክክብ ተፈጽሞ ምረቃ የተከናወነ ሲሆን በሙከጡሪ ከተማ ያለው ግን ባለበት ችግር የተነሳ ርክክቡ ወደ ኋላ ቀርቷል፤ ምረቃው አልተከናወነም። ወረዳውም ሙሉ ርክክብ ሳይፈፀምና ችግሮቹ የመጨረሻ ውሳኔ ሳያገኙ ሆስፒታሉን ለመረከብ እንደሚቸገርም ጠቁመዋል። ለጊዜው ግን ከነ ችግሩም ቢሆን ከህብረተሰቡ ችግር አኳያ ሆስፒታሉ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን አረጋግጠዋል።
በኦሮሚያ ጤና ቢሮ የፕሮጀክት እና ግንባታ ጥገና ዳይሬክተር አቶ ሞሲሳ አሰፋ በበኩላቸው፤ ግንባታው ለህብረተሰቡ አገልግሎት ለመስጠት ከታሰበው ጊዜ አኳያ የተወሰነ ጊዜ ቢዘገይም ከሌሎች ግንባታዎች በተለየ ሁኔታ ግን ተጓቷል የሚያስብል አለመሆኑን አብራርተዋል። ከውሃ እና ኤሌክትሪክ መስመር አኳያ የተጠቀሱት ችግሮች መኖራቸውንና ከተቋራጩ ጋር በመነጋገር መፍትሄ እንዲሰጠው ተደርጓል። ይሁንና ችግሩ ሙሉ ለሙሉ ባለመስተካከሉ የማስተካከያ ሥራዎች እንደሚከናወኑ አስገንዝበዋል። ተቋራጩ ሥራዎቹን ባለማጠናቀቁም አራት ሚሊዮን ብር ክፍያ እንዳልተፈፀመ አረጋግጠዋል። ሆኖም በህንፃዎቹ ላይ የመፍረስና ከፍተኛ ጉዳቶች የሚደርስ ከሆነ ተቋራጩ እስከ 10 ዓመት ድረስ ለማስተካከል የውል ግዴታ አለበት ብለዋል።
የሆስፒታሉን ግንባታ ያከናወነው ሳምሶን ሥራ ተቋራጭ ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ ህሊና መለሠ በበኩላቸው፤ ተቋራጩ በውሉ መሠረት ሥራዎቹን ማከናወኑንና የመጀመሪያ ደረጃ ርክክብ መፈጸሙን ገልፀዋል። ከመብራት መስመሮች ጋር በተያያዘ ችግሩ የተፈጠረው ከተቋራጩ ሳይሆን የዋናው ኤሌክትሪክ መስመርና የጀኔሬተሩ አቅም አለመመጣጠን ጋር በተያያዘ ነው። ከዚህም በተጨማሪ ጀኔሬተሩን ያመጣው አካል ሌላ አካል በመሆኑ ተጠያቂነት የለብንም ብለዋል።
እንደ ወይዘሮ ህሊና ገለፃ፤ የመጀመሪያ ደረጃ ርክክብ ከተፈመ በኋላ እንዲስተካከሉ የተባሉ ችግሮችን አስተካክለናል ብለዋል። ከጣሪያ ፍሳሽ ጋር በተያያዘ የሚነሳው ችግር ማስተካከል እንደሚቻልና በህክምናው ላይ ጫና እንደማይፈጥር ገልፀው፤ ተቋራጩ ከውሉም በተጨማሪ ሌሎች ሥራዎችን በቅንነት ማከናወኑን አስረድተዋል። ይሁንና ተቋራጩን በማይመለከተው ጉዳይ መወቀስ እንደሌለበትም አሳስበዋል። የመጨረሻ ደረጃ ርክክብ ለማድረግም እየተጠባበቅን ነው ብለዋል።
የሙከጡሪ ሆስፒታል 48ሺ400 ሜትር ስኩየር ቦታ ላይ በ31 ሚሊዮን ብር የተገነባ ሲሆን በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን የሚገኙበት ደብረሊባኖስ፤ ጅዳ እና ውጫሌ ወረዳ ለሚኖሩ 275ሺ232 ዜጎች አገልግሎት እንዲሰጥ ታስቦ የተገነባ ነው። ሆስፒታሉ በ2011 በጀት ዓመት 9ሺ955 ሰዎች ተመላላሽ ህክምና የሰጠ ሲሆን የእቅዱን 92 ከመቶ ማሳካቱን ከሆስፒታሉ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
አዲስ ዘመን ህዳር 20/2012
ክፍለዮሐንስ አንበርብር