አርባ ምንጭ፡- በ2011 ዓ.ም የክረምት ወቅት እና በሐምሌ 22 የአረንጓዴ አሻራ ቀን በደቡብ ክልል የተተከሉ ችግኞችን ለማህበረሰቡ በሰነድ ማስረከብ መቻሉ የፅድቀት ምጣኔውን ከፍ በማድረግ ውጤት ማስመዝገቡን ክልሉ አስታወቀ፡፡
የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ መለሰ መና ለአዲስ ዘመን እንደተናገሩት፣ ክልሉ በሁለቱ መርሐግብሮች የተተከሉ ችግኞችን በከተማ ለነዋሪዎች እንዲሁም ለመንግሥትና ለግል ተቋማት፣ በገጠር ደግሞ ለአርሶና አርብቶ አደሩ ማህበረሰብ ሰነድ አዘጋጅቶ አስረክቧል፡፡
ችግኞቹ ባለቤት እንዲኖራቸው በተሰራው ሥራ በአብዛኛው የክልሉ አካባቢዎች የሰነድ ርክክብ የተደረገ ሲሆን ፣በቀሩት ውስን አካባቢዎች ስራው እየተከናወነ ስለመሆኑም አቶ መለሰ አስረድተዋል፡፡
ከተከላ በስተጀርባ የሚከናወንን ተግባር ያለን ጥቅም ከግምት ውስጥ በማስገባት በተከናወነው በዚህ ስራ ከዚህ ቀደም ይታይ የነበረውን ዝቅተኛ የፅድቀት ምጣኔ ማሻሻል መቻሉን የተናገሩት አቶ መለሰ፣ በዚህም እንደ ክልል በሁለቱ መርሐግብሮች የተተከሉ ችግኞች የፅድቀት ምጣኔ ከ85 በመቶ በላይ ማድረስ መቻሉን ተናግረዋል፡፡
ይህ ሥራ ያስገኘው ውጤት ከፍተኛ በመሆኑ ተሞክሮውን በሀገር አቀፍ ደረጃ ለመቀመርና ወደ ሁሉም ክልሎች ለማስተላለፍ ዝግጅት እየተደረገ ሲሆን፣ ክልሉ በ2012 በጀት ዓመትም ተግባሩን አጠናክሮ እንደሚሄድበት ኃላፊው ጠቁመዋል፡፡
የግብርና ሚኒስቴር በሁለቱ መርሐ ግብሮች የተተከሉ ችግኞች ያሉበትን ሁኔታ ለሚዲያዎች ባስጎበኘበት ወቅት የዝግጅት ክፍላችን ባደረገው ምልከታ ችግኞቹ የተተከሉባቸው ቦታዎች ከእንስሳትና ሰዎች ንክኪ ነጻ ሆነው የእድገት ሁኔታቸውም በጥሩ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ተገንዝቧል፡፡
ለአብነትም በደቡብ ክልል በጋሞ ዞን በአርባምንጭ ከተማ አስተዳደር ወዜ ቀበሌ እና ጨንቻ ማረሚያ ቤትን ጨምሮ በወረዳው አንዳንድ አካባቢዎች እንዲሁም በወላይታ ዞን በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ባደረግነው ምልከታ በተከላ ቦታዎቹ የጥበቃ ሠራተኞች ጭምር ተመድበው የአረምና ኩትኳቶ እንክብካቤ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ተመልክተናል፡፡
በተለይም በወዜ ቀበሌ ከዚህ በፊት ምንም የደን ሽፋን ያልነበረውና በተደጋጋሚ በጎርፍ ይጠቃ የነበረ ተራራማ ቦታ አሁን ላይ በተተከሉ ችግኞች በማገገሙ ሸሽተው የነበሩ የዱር እንስሳት ጭምር እየተመለሱ ስለመሆኑ በጋሞ ዞን እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት መምሪያ የተፈጥሮ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ፀጋየ ለታ ተናግረዋል፡፡
በደቡብ ክልል በ2012 በጀት ዓመት ከ400 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በአፈርና ውሀ ጥበቃ ሥራ ለማከናወንና 4.8 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ለማሳተፍ የታቀደ ሲሆን 1.3 ቢሊዮን ችግኝ ለማፍላት በአሁኑ ሰዓት 7 ሺህ የችግኝ ጣቢያዎች በመንግሥት፣ በአርሶአደሩ፣ በማህበረሰቡና በፕሮጀክቶች ድጋፍ መዘጋጀታቸው ተገልጿል፡፡
የክልሉ ዞኖችና ወረዳዎች ከጥር ወር አጋማሽ ጀምሮ ወደ ተግባር ለመግባት ዝግጅት እያደረጉ መሆናቸውን የገለጹት አቶ መለሰ፣ ክልሉም የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን ማጠናቀቁን ገልፀዋል፡፡
አዲስ ዘመን ህዳር 20/2012
ድልነሳ ምንውየለት