አዲስ አበባ፡- የደረሱ ሰብሎች ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብ እና አየር ፀባይ እንዳይጎዳ በወቅቱ እንዲሰበሰቡ የብሔራዊ የሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ አሳሰበ።
ኤጀንሲው ለዝግጅት ክፍላችን በላከው የአየር ሁኔታ ትንቢያ መሠረት ሰሞኑን አንዳንድ አካባቢዎች ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ የመከሰት እድሉ ሰፊ ነው። በመሆኑም ዝናቡ በየአካባቢው የደረሱ ሰብሎችን እንዳያበላሽ ሰብሉን መሰብሰብ እንደሚያስፈልግ አሳስቧል።
እንደ ኤጀንሲው መረጃ፤ በሰሜን፣ በምስራቅና በመካከለኛው የኢትዮጵያ አካባ ቢዎች በተለይም በምዕራብ ምስራቅ፣ ኦሮሚያ፣ በምዕራብ ምስራቅ ሸዋ ዞኖች፣ አርሲና ባሌ፣ በምዕራብና ምስራቅ ሐረርጌ በምስራቅና ደቡብ ትግራይ ዞኖች፣ የደቡብ ሰሜናዊ ክፍል፣ በሰሜንና ደቡብ ወሎ ዞኖች፣ በምስራቅና ምዕራብ ጎጃም ላይ ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ የማግኘት ዕድል ይኖራቸዋል። በመሆኑም በሰብል ስብሰባ እና ድህረ ሰብል ስብሰባ ላይ አብዛኞቹ ቦታዎች ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንደሚኖረው ይጠበቃል። በመሆኑም የደረሱ ሰብሎችን አስቀድሞ በቅንጅት መሰብሰብ ያስፈልጋል።
በአገሪቱ አብዛኛዎቹ አካባቢዎች ደረቃማ የእርጥበት ሁኔታ የሚስተዋል ሲሆን፤ በሌላ በኩል በደቡብ ምዕራብ፣ በደቡብና በደቡብ ምስራቅ እንዲሁም በጥቂት የመካከለኛው አካባቢዎች ላይ መጠነኛ የሆነ እርጥበት ያገኛሉ።
በሰሜን ምዕራብ አካባቢዎች የበጋው ደረቃማው የእርጥበት ሁኔታ በተለይም የመኸር ሰብል ለሚሰበስቡና የድህረ ሰብል ለሚያከናወኑ ተግባራት አዎንታዊ ሚና ይኖረዋል። በሌላ ጎኑ ደግሞ በዚህ ወቅት ዝናብ በሚጠበቅባቸው የደቡብ አጋማሽ የአገሪቱ ስፍራዎች ላይ እርጥበት እንደሚኖረው ይጠበቃል።
በተመሳሳይ ሰሞኑን የሚኖረው የአየር ሁኔታ አዝማሚያ በውሃው ፍላጎት ላይ የራሱን በጎ ተፅዕኖ ያሳድራል። አብዛኛዎቹ የደቡብ፣ ደቡብ ምዕራብ፣ የደቡብ ምስራቅ የመካከለኛው እንዲሁም በጥቂት ሰሜን አጋማሽ የሚገኙ ተፋሰሶች የተሻለ እርጥበት ያገኛሉ። የበጋ ወቅት ዝናብ ተጠቃሚ ባልሆኑ አብዛኞቹ የላይኛውና መካከለኛው አዋሽ አፋር ደናክል፣ በጥቂት የመካከለኛውና የታችኛው ዓባይ እንዲሁም በጥቂት የመካከለኛው ተከዜ ተፋሰሶች ላይ ከመጠነኛ እርጥበት እስከ ከፍተኛ እርጥበት እንደሚያገኙ ይጠበቃል።
አዲስ ዘመን ህዳር 20/2012
ክፍለዮሐንስ አንበርብር