አዲስ አበባ ፡- በአዲስ አበባ ከተማ ባለፉት ሁለት ዓመታት በተካሄደ የከተማ የምግብ ዋስትና መርሀ ግብር የታቀፉ ነዋሪዎች ከ145 ሚሊዮን ብር በላይ መቆጠባቸውን የከተማዋ የሥራ ዕድል ፈጠራና የምግብ ዋስትና ኤጀንሲ አስታወቀ፡፡ በመርሀ ግብሩ 325 ሺህ የሚጠጉ ነዋሪዎች ታቅፈዋል፡፡
የኤጀንሲው የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ዘላለም ወጋየሁ በተለይ ለጋዜጣው ሪፖርተር እንደገለፁት፤ የከተማ የምግብ ዋስትና ፕሮግራሙ ተጠቃሚዎች ራሳቸውን ከመደጎም አልፎ በሥራው ሲሳተፉ የውዴታ ግዴታ ከገቢያቸው ላይ 20 በመቶ እንዲቆጥቡ ይደረጋል፡፡ አንዳንዶች በራሳቸው ፍላጎት ጨምረው እየቆጠቡ ይገኛሉ። በአጠቃላይ በቁጠባው ከ145 ሚሊዮን ብር በላይ መቆጠብ ችለዋል፡፡
መርሀ ግብሩ መንግሥት በመደበው 100 ሚሊዮን ዶላርና የዓለም ባንክ በሰጠው 300 ሚሊዮን ዶላር ብድር በአፍሪካ ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ 11 ከተሞች እየተተገበረ እንደሚገኝ አቶ ዘላለም ጠቅስው፣ ከዚህ ውስጥ 70 በመቶው በአዲስ አበባ ላይ እየተተገበረ ነው ይላሉ፡፡
መርሀ ግብሩ በአዲስ አበባ ከተማ ሲተገበር በመጀመሪያው ዙር በ35 ወረዳዎች 123ሺህ 918 ነዋሪዎች እንዲታቀፉ ተደርጓል ብለዋል፡፡ ከነዚህ ውስጥ 16በመቶው ወጥተው መሥራት የማይችሉ ዜጎች መሆናቸውን ጠቅሰው፣ እነሱም በቀጥታ ድጋፍ እየተደጎሙ እንደሚገኙም ተናግረዋል፡፡
በሁለተኛው ዙር የምግብ ዋስትና ፕሮግራም 55 የከተማዋ ወረዳዎች እንዲታቀፉ መደረጉን ጠቅሰው፣ በዚህም 200ሺህ ነዋሪዎች እየተሳተፉ እንደሚገኙ አስታውቀዋል፡፡ ከነዚህ ውስጥ 165ሺህ ሰዎች በማኅበረሰብ አቀፍ ሥራዎች እየተሳተፉ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ሥራው ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው ዳይሬክተሩ ተናግረው፣ ዜጎች አካባቢያቸውን በማጽዳት የራሳቸውንና የማኅበረሰቡን ጤንነት እንዲጠብቁ፣ ለሥራው ተሳታፊዎች ገቢ ለማስገኘት፣ የቁጠባ ባህልን ለማዳበር እየረዳ እንደሚገኝ አብራርተዋል፡፡ እንደ ጉለሌ ክፍል ከተማ ባሉ አካባቢዎች ደግሞ በእርከንና ተፋሰስ ልማት ችግኞችን በመትከልና በማልማት እየተሠራ መሆኑን ጠቁመዋል።
ሥራው ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር የሚሠራ ነው ያሉት አቶ ዘላለም፣ በመጪው ጥር ወር አጋማሽ ቀሪ 26 ወረዳዎችን በማካተት ሦስተኛውን ዙር ፕሮግራም ለማስጀመር ኑሯቸው የተሻሻሉትን የማጥራትና የልየታ ሥራ መከናወኑን ጠቁመዋል።
እንደ ዳይሬክተሩ ማብራሪያ፤ ከአንድ ቤተሰብ እስከ 4 ሰዎች ሊሳተፉ ይችላሉ፡፡ ስድስት ወር የሆነው በአዲስ አበባ ነዋሪ የሆነ ማንኛውም ሰውም ተጠቃሚ መሆን ይችላል፡፡ እስከ አሁን በከተማ ሴፍቲኔት መርሀ ግብሩ 325 ሺህ የሚጠጉ ነዋሪዎች ታቅፈዋል፡፡
በምግብ ዋስትና ሥራው ግማሽ ሚሊዮን ህዝብ ተጠቃሚ ለማድረግ መታሰቡን ዳይሬክተሩ ጠቅሰው፣ ዓላማው በድህነት ውስጥ ያሉትን ወገኖች ለመደገፍና የሥራ መነሳሳትን መፍጠር መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በዚህም ከሦስት ዓመት በኋላ ሥልጠና ተሰጥቷቸው በጥቃቅንና አነስተኛ ተደራጅተው አልያም በግል በቆጠቡት ገንዘብ ሊሠሩ የሚችሉበት ሁኔታ እንደሚመቻችም ጠቁመዋል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 23/2011
በኃይለማርያም ወንድሙ