አዲስ አበባ፡- የብልጽግና ፓርቲ ህብረ ብሔራዊና ፌዴራላዊ ኢትዮጵያን የሚገነባና ምስረታውም ህጋዊ መስመርን የተከተለ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓቢይ አህመድ አስታወቁ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ትናንት በግል የፌስ ቡክ ገጻቸው የብልጽግና ፓርቲን አቋምና ምኞት በተመለከተ ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብና ለፓርቲው አባላት ባስተላለፉት መልዕክት፤ የብልጽግና ፓርቲ የመመስረት ሂደት በምሁራን ሲጠና መቆየቱና በየደረጃው ሁሉም አመራሮች የተወያዩበት መሆኑን አውስተዋል ።
የኦሮሞ ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ኦዲፒ) እና የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) ባካሄዱት አስቸኳይ ድርጅታዊ ጉባኤ በሙሉ ድምጽ የኢህአዴግ ውህደት ማጽደቃቸውን የገለፁት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢህዴን) በአስቸኳይ ድርጅታዊ ጉባዔውን እንደሚያፀድቀው ይጠበቃል ብለዋል።
የብልጽግና ፓርቲ ፕሮግራሙን እያሻሻለ ለሚቀጥሉት 10 ዓመታት ኢትዮጵያን ወደ ብልጽግና ጎዳና የሚወስደውን እቅድ የነደፈ መሆኑን የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓብይ፤ ከሕዝቡ ጋር ውይይት የሚካሄድበት እና የሚዳብር መሆኑንም ተናግረዋል።
‹‹ኢትዮጵያን ወደ ብልጽግና የመውሰድ ህልማችን እውን የምናደርግበት ትክክለኛው መንገድ እየተጀመረ ነው›› ካሉ በኋላ፤ ቄሮ ፋኖና ዘርማ በለውጡ ሂደት ትልቅ ተሳትፎ እንደነበራቸው አስታውሰው፤ “ቄሮ ፋኖና ዘርማዎች የታገላችሁለት ፓርቲ ተመስርቷል” በማለት ወጣቶቹ ከፓርቲው ጋር በመሆን የታገሉለት ጥያቄ ወደ ተግባር እንዲመለስ አስፈላጊውን ጥረት እንዲያደርጉም ጥሪ አስተላልፈዋል። ድርጅታቸው የፋኖንና የቄሮን ትግል የሚያስታውስ የተግባር ማስታወሻ እንደሚያስቀምጥም ጠቁመዋል።
አንዳንድ ኃይሎች አዲሱ የብልጽግና ፓርቲ አሐዳዊ ሥርዓትን የሚያመጣና የፌዴራል ሥርዓትን የሚያጠፋ የሚል አሉባልታ ሲናገሩ ይደመጣል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በፓርቲው ፕሮግራም ላይ በግልጽ እንደተቀመጠው ህብረ ብሔራዊት፣ ፌዴራላዊት፣ ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን የሚያጠናክር እና የሚገነባ እንጂ የማያፈርስ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስረድተዋል።
መንግሥት ለህግ ልዕልና መረጋገጥ ኃላፊነቱን እንደሚወጣ የገለፁት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ ውስጥ ሀሳብ ያለው አሳምኖ ወደ ስልጣና ከመውጣት ውጪ በኃይልና ህዝብን በማወክ የህዝብን ሰላም የሚያሳጣ አካል ላይ መንግሥት ህጋዊ እርምጃ እንደሚወስድም አመላክተዋል።
ሌሎች ፓርቲዎች ብልጽግና ፓርቲን በመክሰስ ሳይሆን አማራጭ ሐሳብ በማምጣት እንዲሞግቱ እና ለኢትዮጵያ ሕዝብ አማራጭ ሐሳብ ይዘው እንዲቀርቡም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓቢይ ጥሪ አቅርበዋል።
አዲስ ዘመን ህዳር 19/2012
ተገኝ ብሩ