አዲስ አበባ፡- በኢትዮጵያ አሁናዊ የብሄር ጥያቄ አረዳድ ‹‹ተጨቁነሃል›› የሚል የታሪክና ፖለቲካ ትርክት ብሄርተኝነትን እያባባሰው መሆኑ ተገለጸ።
የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ስትራቴጂያዊ ጥናት ኢንስቲትዩት ‹‹የዋለልኝ የብሔሮች ጥያቄ በኢትዮጵያ ከ50 ዓመታት በኋላ›› በሚል መሪ ሀሳብ ትላንት በሸራተን አዲስ ሆቴል ህዝባዊ ሴሚናር አካሂዷል።
በውይይት መድረኩ መነሻ ሀሳብ ያቀረቡት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁርና የ‹‹ኢንስቲትዩት ፎር ሴኩሪቲ ስተዲስ›› የዘርፉ ከፍተኛ ተመራማሪ ዶክተር ሰሚር የሱፍ እንደተናገሩት፤ ‹‹ተጨቁነሃል›› የሚል ትርክት ብሄርተኝነትን አባብሷል። መንግስት ተኮር በሆኑና ህዝባዊ መሠረት ባላቸው አስተሳሰቦችም በኢትዮጵያ አሁንም ድረስ የብሄር ጥያቄ አመርቂ በሆነ ሁኔታ አልተመለሰም።
እንደ ዶክተር ሰሚር ማብራሪያ፤ የጭቆና ትርክት በብዛት መነሳቱ በአሁን ወቅት ያለውን የብሄር ጥያቄየተወሳሰበና ተቀናቃኝ የበዛበት አድርጎታል።
በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ውስጥ በስፋት የብሄር ፍላጎት አለመሟላት ተንሰራፍቷል። ይህም በአገሪቷ መረጋጋት እንዳይኖር አድርጓል። የውጭ ተጽእኖን ጨምሮ ሌሎች ምክንያቶች ቢጠቀሱም በዋናነት ግን የዚህ መነሻ ተደርገው የሚታሰቡት መንግስታዊ ተኮር የሆኑ ትንታኔዎች ማለትም ባለፉት 27ዓመታት የተዘረጋው የመንግስት መዋቅርና ንዑስ ብሄርተኝነት የወለደው አምባገነናዊ መንግስት ተጠቃሾች ናቸው።
በሌላ በኩል በሁሉም የመንግስት ሥርዓት የአካታችነት ፖለቲካ እሳቤ መኖሩን እንደ መልካም አጋጣሚ ያነሱት ዶክተር ሰሚር፣ የአምባገነንነት ዝንባሌና የሀይል እርምጃዎች መኖራቸው በተለይ ለብሄርተኝነት ጥያቄ ትግል መጋጋል ምክንያት መሆኑንም ጠቁመዋል።
በኢትዮጵያ መንግስታትና ንዑስ ብሄርተኞች መካከል የነበረው ፈርጀ ብዙ ተራክቦ የብሄር ጥያቄን እንዲሰፋ አድርጓል የሚሉት ዶክተር ሰሚር፤ በኢትዮጵያ የብሄር ጥያቄ በርካታ ዓመታትን ማስቆጠሩንና፤ የኢህአዴግ ተቋማት ብሄርተኝነትን እንደ ዋነኛ አጀንዳ በመውሰድ ተደጋጋሚ የብሄርተኝነት ስሜት እንዲንጸባረቅ ማድረጋቸው ንዑስ ብሄርተኝነት እንዲስፋፋ ከፍተኛ ሚና መውሰዱን በትንታኔያቸው አካትተዋል። የብሄር ጥያቄ ነባራዊ ፋይዳ ቢኖረውም የብሄር ጥያቄን ከጭቆና ጋር ብቻ ማያያዙ ተገቢ እንዳልሆነና በብሄርተኝነት አመክንዮ ላይ በመመርኮዝ አውዱን ማረጋጋት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የታሪክ ምሁሩ ፕሮፌሰር ገብሩ ታረቀ በበኩላቸው የብሄር ጥያቄ አሁንም ያለቀለት ጉዳይ እንዳልሆነ በመናገር፤ አሁን ላይ ያለው የፌዴራል ሥርዓቱ በቋንቋና በብሄር ላይ የተመሰረተ በመሆኑ ገና እልባት ያላገኘ አጀንዳ መሆኑን ጠቅሰዋል። ባለፉት የመንግስት ሥርዓት የቋንቋ፣ የባህል የብሄርና የኢኮኖሚ ጭቆና ነበር የሚሉ ትርክቶች አመጽ
ማስነሳታቸውን፣ ይህ ጥያቄ አሁንም ድረስ በሠላማዊ መንገድ እየቀረበ አለመሆኑን ጠቁመዋል።
በኢትዮጵያ የብሄር ትርክት ተጨቁነናል የሚሉ እንዳሉ ሁሉ የቀድሞ የመንግስት ሥርዓት የብሄር ጨቋኝ ተደርጎ መቅረብ እንደሌለበት የሚሞግቱና ጭቆና የሚለውን እሳቤ የሀሰት ትርክት አድርገው የሚያቀርቡ አካላት መኖራቸውን ተናግረዋል። ጭቆና የሚለው እሳቤ የኢትዮጵያን ታሪክ ወደ ሌላ አቅጣጫ እየወሰደው መሆኑንም ገልጸዋል።
በመሆኑም የሀሰት ትርክቱም መታረም እንዳለበት በማመላከት በተለይ ጥያቄው እልባት እንዲያገኝና እንዲህ ዓይነት ጽንፍ የያዙ ሀሳቦችን ለማስታረቅ የውይይት መድረኮች በስፋት መፈጠር እንዳለባቸውም ጠቅሰዋል።
በውውይት መድረኩ የዋለልኝ ዘመን ተሸጋሪ አስተሳሰብ በኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊያን ላይ ያሳደረው ተጽእኖ በተለያዩ ምሁራን ተዳስሷል፡፡
አዲስ ዘመን ህዳር 19/2012
አዲሱ ገረመው