አዲስ አበባ፡- በግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ አስተባባሪነት በሁለት ዓመት ተሞክሮ አበረታች ውጤት የታየበት ‹‹አገር ዓቀፍ ገበያ መር ኩታ ገጠም የግብርና ልማት›› ይፋ ተደረገ።
የግብርና ልማቱ ትናንት ይፋ በተደረገበት ወቅት የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ወይዘሮ ሳህለወርቅ ዘውዴ ‹‹ ገበያ መር ኩታ ገጠም የግብርና ልማት›› አነስተኛ ይዞታ ያላቸው አርሶ አደሮችን ህይወት ለመለወጥ የሚከናወን ገበያ መር የእሴት ሰንሰለት መሆኑን ገልጸዋል።
‹‹ዋነኛ ዓላማው በአምስት ዓመታት ውስጥ ወደ አምስት ሚሊዮን የሚጠጉ አነስተኛ ይዞታ ያላቸውን አርሶ አደሮች ገቢ በእጥፍ ማሳደግ ነው።›› ያሉት ፕሬዚዳንቷ መርሐ ግብሩ የአርሶ አደሩን ህይወት ከመለወጥ ባለፈ ግብርናው በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ጉልህ አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ታስቦ የተወጠነ መሆኑንም ገልጸዋል።
የግብርና ልማቱ በግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ አስተባባሪነት በመንግሥትና በልማት አጋሮች የገንዘብ ድጋፍ ተግባራዊ የሚደረግ መሆኑን ጠቅሰው፤ ገበሬው ሁሉን አቀፍ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የራሱንም ሆነ የአገሩን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥበትና የቴክኖሎጂ ሽግግር የሚያደርግበት ዘመናዊ የግብርና ሥርዓት እንደሆነ ገልጸዋል።
የግብርናውን ዘርፍ ለማሳደግ ሲታሰብ ሴቶችን ከግምት ማስገባት እንደሚያስፈልግ የገለጹት ፕሬዚዳ ንቷ፤ በሴቶች ይዞታ ሥር ያለው መሬት 20 በመቶ ብቻ መሆኑን ጠቅሰዋል። እነዚህም ጥቂት ሴት አርሶ አደሮች ቢሆኑ የግብርና ልማት አገልግሎትና ብድር የማግኘት እድላቸው አናሳ ነው ብለዋል።
ሴቶችን ማበረታታት ማለት አገሪቱ በፍጥነት እንድታድግ ማገዝ ነው ያሉት ወይዘሮ ሳህለወርቅ፤ ግማሹን የህብረተሰብ ክፍል ትቶ መጓዝ የሚታሰ በውን እድገት በዚያው ልክ እንዲቀንስ ያደርጋል ብለዋል።
በመጨረሻም ገበያ መር ኩታ ገጠም የግብርና
ልማት በመላ አገሪቱ እንዲስፋፋ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ በማሳሰብ በዘርፉ ትብብርና ድጋፍ ያደረጉ የልማት አጋሮችን ሁሉ በማመስገን መርሐ ግብሩን ይፋ አድርገዋል።
የግብርና ሚኒስቴር ምኒስትር ዴኤታ አቶ ሳኒ ረዲ በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ ግብርና ለዘመናት በአርሶ አደሩ ጉልበትና በበሬ ትከሻ ላይ ወድቆ ከቤት ፍጆታ የዘለለ ውጤት እንዳልታየበት ገልጸዋል። ምንም እንኳ ኢትዮጵያ ካላት የመሬት ሀብት 74 በመቶው ለግብርና ምቹ ቢሆንም አገሪቱ ከዘርፉ ማግኘት የሚገባትን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ማረጋገጥ ያልቻለችበትና የምግብ ፍጆታን ከውጭ ለማስገባት የተገደደችበትን ምክንያት ለማጥናት መሞከሩን ገልጸዋል።
በጥናቱ ውጤትም የአርሶ አደሩ መሬት አነስተኛ መሆኑና ያም ቢሆን በተራራቀ ቦታ ተበጣጥሶ ያለ መሆኑ ዘመናዊ እርሻና ተመሳሳይ ሙያዊ ድጋፍ ለማድረግ አስቸጋሪ ሁኔታ መፍጠሩ ታውቋል።
አርሶ አደሩ ቴክኖሎጂን የመጠቀም አቅሙ ባለመዳበሩ ግብዓቶችን እንደልቡ አያገኝም። ብድር አቅራቢዎችም አርሶ አደሩ ይከፍለናል የሚል አመኔታ ስለሌላቸው ብድር አያቀርቡም፤ ጥናቱ ያሳያቸው ችግሮች በዚህ መልክ ተለይተው አዋጭ የሆነውን መንገድ በመከተል መፍትሄ ለመስጠት ተሞክሯል ብለዋል።
በዚህ መሰረት የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀ ንሲ ተመስርቶ አርሶ አደሩን ግንዛቤ በማስጨበጥ በአጠቃላይ በ421 ወረዳዎች በአራት ዋና ዋና የምግብ ሰብሎች ማለትም በገብስ ፣ በስንዴ፣ በጤፍና በበቆሎ ላይ ተግባራዊ በማድረግ 20 በመቶ የምርታማነት ጭማሪ መታየቱን ገልጸዋል።
የአግሪካልቸራል ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ካሊድ ቦምባ በበኩላቸው፤ እንዳስረዱት ገበያ መር ኩታ ገጠም ግብርና ቀደም ሲል አርሶ አደሮች በአነስተኛ መሬት ላይ በተበታተነ መልክ የሚያካሂዱትን ግብርና በኩታ ገጠም በማዋሃድ ተመሳሳይ ዘር በመዝራትና ተመሳሳይ የቴክኖሎጂ አገልግሎትን በማግኘት ምርትና ምርታማነታቸውን እንዲያሳድጉ የሚያስችል ነው ብለዋል።
የብድርና የገበያ ትስስርን በመፍጠር የአርሶ አደሩን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት የሚያሳድግ መሆኑንም ጠቅሰው፤ በሁለት ዓመት ተሞክሮው አርሶ አደሮችን ውጤታማ ያደረጉ አፈጻጸሞች መመዝገባቸውን ያበሰሩት አቶ ካሊድ በዘንድሮው ዓመትም አንድ ነጥብ ሶስት ሚሊዮን አርሶ አደሮች በኩታ ገጠም ተደራጅተው እየሰሩ መሆናቸውንም አስታውሰዋል። ይፋ የተደረገው የገበያ መር ግብርና ልማት በተግባር ተፈትሾ አበረታች ውጤት የታየበት መሆኑንም ገልጸዋል።
ፕሮግራሙን በቀጣይ አምስት ዓመታት በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ለማስፋፋት እየተሰራ መሆኑን የገለጹ ሲሆን፣ ለዚህም ከኔዘርላድ እና ዴንማርክ ኤምባሲዎች እንዲሁም ከአውሮፓ ህብረት ጋር ከ 1 መቶ ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ የድጋፍ ስምምነት መደረጉን ገልፀዋል።
አዲስ ዘመን ህዳር 19/2012
ኢያሱ መሰለ