ጨንቻ፡- ወጣቶች ሀገራዊ አንድነታቸውን በማስጠበቅ ራሳቸውን ከወንጀል ድርጊቶች ሊጠብቁ እንደሚገባ በደቡብ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል የጨንቻ ማረሚያ ቤት ታራሚዎች አሳሰቡ፡፡
ታራሚዎቹ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለፁት፣ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በሀገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች በተለይም በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚስተዋሉ ግጭቶች ወጣቶች ላይ ያነጣጠሩ መሆናቸው ስጋት የሚፈጥር ሲሆን ወጣቶች በወንጀል ድርጊቶች በመሳተፍ ከአላማቸው ሲደናቀፉ ብሎም የሀገር ሰላም ሲታወክ ይስተዋላል ብለዋል፡፡
ከብሄር ይልቅ ሀገራዊ ማንነት መቅደም እንዳለበት የተናገሩት ታራሚዎቹ ፣ችግሮች ሲፈጠሩ መነጋገርና ስምምነት ላይ መድረስን መልመድ እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡ ይህ ካልሆነ ግን በስሜት የሚከወኑ ድርጊቶች ነገን በፀፀት ለማሳለፍ እንደሚያስገድዱም ተሞክሯቸውን በማንሳት አስረድተዋል፡፡
በወንጀል ድርጊት የሚሳተፍ ወጣት ለእስር ሲዳረግ የወጣትነት ጊዜውን በማረሚያ ቤት ማሳለፉ ትልቅ የህይወት ጉድለት ለመሆኑ እኔ ምሳሌ ነኝ ሲል የተናገረው ታራሚ ወጣት መኮንን እንዳለ፤ ወጣቶች ከመለያየት ይልቅ አንድ መሆንን እና እርስ በእርስ በመግባባት ለሀገር እድገት የድርሻቸውን ሊወጡ ይገባል ብሏል፡፡
ሌላው የህግ ታራሚ ወጣት በልሁ ቆሎባ በበኩሉ አሁን አሁን የሚስተዋሉ ግጭቶች ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማትም በመዝለቅ ችግር እየፈጠሩ ስለመሆኑ በሚዲያ እንደሚከታተል ገልፆ፣ በብሄርና ሃይማኖት ልዩነት የሚነሱ ግጭቶች ከደረስንበት ጊዜ ጋር አብረው የማይሄዱና ጎታች በመሆናቸው ወጣቶች በመሰል ድርጊቶች ከመሳተፍ ሊቆጠቡ ይገባል ብሏል፡፡
የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚ መሆኑን የተናገረው የህግ ታራሚው፣ ወጣቶች በማህበራዊ ሚድያ የሚሰራጩ መልእክቶችን ሰከን ብለው የመፈተሽና እውነትን ከሀሰት የመለየት ስራ መስራት ይጠበቅባቸዋል ሲል መክሯል፡፡
በሀገር ውስጥና በውጪ ብሄርን ከብሄር እና ጎሳን ከጎሳ ለመለያየት በማህበራዊ ሚዲያው አስበው የሚሰሩ ሰዎች መኖራቸውን በመገንዘብ እስካሁን የደረሰው ጥፋት የመጨረሻ እንዲሆን ወጣቶች በጋራ እንዲሰሩም የህግ ታራሚው በልሁ ጥሪውን አቅርቧል፡፡
ወደ ጨንቻ ማረሚያ ቤት ከገባች ሶስት አመታት ማስቆጠሯን የተናገረችው የህግ ታራሚ መምህርት አማረች ዱሬ በማረሚያ ቤቶቹ የሴቶች ክፍል 24 ሴቶች እንዳሉ ገልፃ፣ ከተለያዩ አካባቢዎችና ብሄሮች የተሰባሰቡ ቢሆንም በብሄርና በሃይማኖት ሳይለዩ በመቻቻልና በአብሮነት የመታረሚያ ጊዜያቸውን እያሳለፉ እንደሆነ ገልፃለች፡፡
በተለይም ወጣቶች በብሄር በመከፋፈል ለህይወት መጥፋትና ንብረት ውድመት ምክንያት ከመሆን ይልቅ በኢትዮጵያዊነት ስሜት በመተባበር ራስንና ሀገርን መለወጥ ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ እመክራለሁ ብላለች፡፡
የጨንቻ ማረሚያ ቤት በ1945 ዓ.ም የተመሰረተ መሆኑ ይታወቃል፡፡
አዲስ ዘመን ህዳር 19/2012
ድልነሳ ምንውየለት