አዲስ አበባ፡- ህብረተሰቡ በሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋ ለችግር ለተጋለጡ ዜጎች የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ጥሪ አቀረበ።
የማህበሩ ዋና ጸሐፊ ዶክተር መሸሻ ሸዋረጋ ትናንት በተካሄደው የእውቅና መስጠት መርሐ ግብር ላይ እንደተናገሩት፤ በአሁኑ ወቅትም በአገሪቱ ከስምንት ነጥብ ስምንት ሚሊዮን በላይ ዜጎች የተለያዩ እርዳታዎችን ይፈልጋሉ። ከነዚህ ውስጥ ስምንት ነጥብ ሶስት ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት የእለት ደራሽ ምግብ የሚያስፈልጋቸው በመሆኑ፤ ህብረተሰቡ እስካሁን በርካታ ተጎጂዎችን ለመታደግ ሲያደርግ የነበረውን ድጋፍ ማስቀጠል ይኖርበታል።
‹‹ባለፈው ዓመት ከሶስት ነጥብ አንድ ሚሊዮን በላይ ዜጎች የተፈናቀሉ ቢሆንም መንግሥትና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ባደረጉት ርብርብ ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ ማድረግ ተችሏል።›› ካሉ በኋላ ነገር ግን አሁንም ቢሆን እነዚህን ዜጎች መልሶ ለማቋቋም የተለያዩ ድጋፎች ካልተደረገላቸው ራሳቸውን መቻልና ምርታማ መሆን የማይችሉ እና በችግር ውስጥ ያሉ መሆናቸውን አሳውቀዋል። በተጨማሪም በአገሪቱ ካሉት 43 ሚሊዮን የሚጠጉ ህጻናት በዓመት ከ36 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት ለዘርፈ ብዙ ድህነት የተጋለጡና የተለያዩ ድጋፎችን የሚፈልጉ ናቸው ሲሉ ዶክተር መሸሻ ተናግረዋል ።
እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ በዓመት ከአንድ ነጥብ ስድስት ቢሊዮን ዶላር በላይ የሚያስፈልግ ሲሆን እስካሁን ከውጪ የሚመጣው ድጋፍ ግማሽ ብቻ ከመሆኑ ባሻገር እሱም እየቀነሰ ሊመጣ እንደሚችል ይገመታል ብለዋል። በአንጻሩ መንግሥት የተለያዩ የልማት ፕሮግራሞችን በማጠፍ ከስድስት መቶ ሚሊዮን በላይ ዶላር በመመደብ ዜጎችን ከችግር ለመታደግ እየሰራ ቢሆንም፤ ችግሩ ሰፊ በመሆኑ እንደ «የሰብዓዊ ድጋፍ ጥምረት» ያሉ ማህበራትና መላው ህብረተሰብ የጀመራቸው የድጋፍ ማሰባሰብና መለገስ ሥራዎች ከመቼውም ጊዜ በላይ አስፈላጊ መሆኑን አመልክተዋል።
ዶክተር መሸሻ ከሁሉም በላይ ደግሞ በአገሪቱ ከቀን ወደ ቀን እየደበዘዘ የመጣውን እርስ በርስ የመደጋገፍና የመተሳሰብ ባህል ማነቃቃት ከሁሉም ዜጋ እንደሚጠበቅ አስገንዝበዋል።
በመርሐ ግበሩ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ለተከሰቱ ችግሮች እርዳታ በማሰባሰብ ሲያደርሱ ለነበሩ «ለሰብአዊ ድጋፍ ጥምረት» አባላት እና የ25ተኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን በማስመልከት የአምስት ሚሊዮን ብር ድጋፍ ላደረገው የአዋሽ ባንክና አዋሽ ኢንሹራንስ የእውቅና ምስክር ወረቀት ተሰጥቷል።
አዲስ ዘመን ህዳር 19/2012
ራስወርቅ ሙሉጌታ