– በውጭ ምንዛሬ እጥረት ምክንያት የስንዴ ግብይቱ ተጓትቷል
አዲስ አበባ ፡- ለአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ዳቦን በተመጣጣኝ ዋጋና በብዛት ለማቅረብ ታስቦ እየተገነባ ያለው የዳቦ ፋብሪካ ከጥር ወር በኋላ ሥራ እንደሚጀምር ተገለጸ። በውጭ ምንዛሬ እጥረት እስከ አሁን የስንዴ ግብይት አለመፈጸሙ ተግዳሮት መሆኑም ተጠቅሷል።
በሆራይዘን ፕላንቴሽን የዕቅድ ቢዝነስ ዴቨሎፕ መንትና የፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ አቶ ይበልጣል ሽመልስ ለአዲስ ዘመን እንዳስረዱት፣ ከቅርብ ወራት በፊት ግንባታው የተጀመረው ይህ ፕሮጀክት በቀን 18 ሰዓታትን በመስራት ከ90 በመቶ በላይ ተጠናቋል። በቀጣይ ወራትም የማሽን ተከላና ቀላል ሥራዎች ይከናወናሉ።
ማሽኑ በመጓጓዝ ላይ ያለ ሲሆን በሦስት ሳምንታት ውስጥ ወደ ሥፍራው ይደርሳልም ያሉት አቶ ይበልጣል፣በዕቅዱ መሰረትም ፕሮጀክቱ እስከ ጥር ወር መገባደጃ ተጠናቆ ሙሉ ለሙሉ ወደሥራ ለመግባት መዘጋጀቱን ገልጸዋል።
በአርባ ሺህ ካሬ ሜትር ላይ ያረፈው ይህ ፋብሪካ የስንዴ ጎተራ፣ የዱቄት ፋብሪካ፣ ዳቦ መጋገሪያና ጊዜያዊ ማከማቻ ያሉት ሲሆን፣ የከርሰ ምድር ውሃን በመጠቀም ሥራውን ለማከናወን የሚያስችል አቅምም ተፈጥሮለታል። ፋብሪካው በቀን ሁለት ሺ ሁለት መቶ ኩንታል ስንዴን በመጠቀም እስከ 1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ዳቦ ማምረት እንደሚችልም ተገልጿል።
ፋብሪካው የሚጠቀመው ስንዴ በርካታ መሆኑን ተከትሎ ስንዴን ከውጭ ለማስገባት እየተደረገ ያለው ሙከራ በውጭ ምንዛሬ እጥረት እየተጓተተ መሆኑም ተጠቅሷል። ገንዘብ ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክና ንግድ ባንክ በጉዳዩ ዙሪያ መክረው አፋጣኝ ውሳኔ ማስተላለፋቸውን የተናገሩት አቶ ይበልጣል የስንዴ ግብይቱ እስከ አሁን ያለመጀመሩ እቅዱን እንዳያስተጓጉለው ያላቸውን ሥጋት ገልጸዋል።
ድርጅታቸው ቀደም ሲል ከሩሲያ እና ዩኩሬን ጋር ስንዴን ለመግዛት ውል ተዋውሎ በውጭ ምንዛሬ እጥረት ምክንያት ውላቸውን እንዳፈረሱም ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል። መንግሥት ለህዝብ ጥቅም ለሚውለው ለዚህ ፕሮጀክት ትኩረት በመቸር አፋጣኝ ምላሽ መስጠት እንደሚገባውም ተናግረዋል።
የሚድሮክ ኢትዮጵያ እህት ኩባንያ የሆነው ሆራይዘን ፕላንቴሽን ይህንን የተቀደሰ ዓላማ ይዞ ወደሥራ ከገባ ቀን ጀምሮ ባለሀብቱ ሼህ ሙሃመድ ሁሴን አላ ሙዲን ጉዳዩን በትኩረት እየተከታታሉና ድጋፍ እያደረጉ መሆኑንም አቶ ይበልጣል አመልክተዋል። የዳቦ ማሽን ግብዓቶችንም ከመንግሥት የውጭ ምንዛሬ ሳይጠበቅ ወደ ሀገር ውስጥ የማስገባት እንቅስቃሴ መጀመሩን ገልጸዋል።
ሆራይዘን ፕላንቴሽን በኢትዮጵያ በተለያዩ የልማት ሥራዎች ላይ እንደተሰማራ የገለጹት አቶ ይበልጣል፣ በእርሻ ሥራ ላይ የተሰማራ እንደመሆኑ በሚቀጥሉት ሁለትና ሦስት ዓመታት ስንዴን በሰፊው በማምረት የውጭ ግዢን ለማስቀረት ጥረት እንደሚደረግ ተናግረዋል።
በሆራይዘን ፕላንቴሽን የዳቦ ፕሮጀክቱ ሥራ አስኪያጅ አቶ ሲሳይ ደበበ በበኩላቸው ፕሮጀክቱ በዕቅዱ መሰረት እንዲጠናቀቅ አስቸጋሪውን የክረምት ወራት እንኳን ያለ እረፍት በመሥራት አሁን ያለበት ደረጃ ላይ መድረሱን ገልጸዋል።
ፕሮጀክቱ ይዞ ከተነሳው ዓላማ አንጻር የሁሉንም ባለድርሻ አካላት ርብርብ የሚጠይቅ መሆኑን የተናገሩት አቶ ሲሳይ፣ ፋብሪካው እዚህ ደረጃ ላይ ደርሶ በስንዴ ምክንያት በሚፈለገው ወቅት ወደ ሥራ ሳይገባ ቢቀር ሊያስቆጭ እንደሚችል ተናግረዋል። በመሆኑም ፋብሪካው በተባለው ጊዜ ሥራውን እንዲጀምር የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥተው ስንዴው የሚቀርብበትን ሁኔታ እንዲያፋጥኑ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የአዲስ አበባ የዳቦ መጋገሪያ ፋብሪካ የመሰረት ድንጋይ የተጣለው ግንቦት 2011 ዓ.ም በአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ ነው። ዓላማውም በዝቅተኛ ገቢ ለሚተዳደሩ የህብረተሰብ ከፍሎች በተመጣጣኝ ዋጋና በሚፈለገው መጠን ዳቦን ለማቅረብ እንደነበር ይታወሳል።
አዲስ ዘመን ህዳር 18/2012
ኢያሱ መሰለ