‹‹የሞባይል ስልኬ በተደጋጋሚ ይጠራል፤ ፀሎት ላይ ስለሆንኩ ረበሸኝ። ልቤ ሁለት ቦታ ተከፈለ፣ አንዴ ጸሎቴን አንዴ ደግሞ ስልኩ የማን ይሆን ስል ግራ ተጋባሁ። የስልኩ ረፍት ማጣት እኔንም እረፍት እንዲሰጠኝ ከኪሴ አውጥቼ ተመለከትኩት፤ ‹ውይ ልጆቼ ናቸው፤ ምን ሆኑ› ስል በድንጋጤ ጸሎቴን በማቋረጥ አነሳሁት። ‹ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ግጭት ተፈጥሮ መሄጃ አጥተን ነው፤ ግራ ገባን፤ ምን እናድርግ› ሲሉ ነገሩኝ። እኔም ‹ኑ ችግሩ እስኪያልፍ እኔ ጋር ትሆናላችሁ› አልኳቸው ›› ይላሉ አቶ ፍቃዱ ሽፈራው።
አቶ ፍቃዱ የእንጅባራ ከተማ ነዋሪ ናቸው። በእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ ከአንድ ሳምንት በፊት ባጋጠመ ችግር ተማሪዎች ከግቢው ወጥተው ቀደም ሲል ከተዋወቋቸው ቤተሰቦች ጋር በመ ደዋወል በማህበረሰቡ ውስጥ ተጠግተው ችግሩን ማሳለፋቸውን ይናገራሉ። በዩኒቨርሲቲው ችግር ባጋጠመበት ወቅት ተማሪዎቹ በጭንቀት ተሞልተው እንደደወሉላቸው የሚገልፁት አቶ ፍቃዱ ተማሪዎቹ ከየትኛውም ብሄር ይምጡ ከየት፤ ኢትዮጵያዊ እስከሆኑ ድረስ ከአንድ ኢትዮጵያዊ ወላጅ የሚጠበቀውን ድጋፍ ማድረግ ግድ እንደሆነ ያስገነዝባሉ።
በወግ ተስፋዬ የእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ትምህርት የሁለተኛ ዓመት ተማሪ ነው። ባለፈው ሳምንት እሁድ ቀን ከምሽቱ አንድ ሰዓት ገደማ ምክንያቱ ባልታወቀ ሁኔታ በተማሪዎች መካከል ግጭቱ ተነሳ። በኋላም ተማሪዎች ከግቢው ወጥተው እየሄዱ በነበረበት ወቅት እኛም ቀደም ሲል ከአቶ ፍቃዱ ቤተሰብ ጋር ትውውቅ ስለነበረንና የምንሄድበትም ቦታ ስላልነበረን በጭንቀት ውስጥ ሆነን ደወልንላቸው። እርሳቸውም በሁኔታው በጣም ደንግጠው ‹‹አይዟችሁ ልጆቼ ኑ፤ እስኪረጋጋ እኔ ጋር ትቆያላችሁ›› በማለት ለስልካችን ምላሽ ሰጡን እኛም ሳናመነታ ሄድን፤ በፍቅር ተቀበሉን፤ ለአንድ ሳምንት ያህልም ከቤተሰቦቻቸው ጋር በመሆን በፍቅር አረጋግተውናል።
ተማሪ ጉልላት ካስዬ በዩኒቨርሲቲው የስነ ልቦና ጥናት ትምህርት ክፍል የሁለተኛ ዓመት ተማሪ ሲሆን የእንጅባራ ህዝብ በግጭቱ ወቅት ያደረገው ድጋፍ ከንግግር በላይ ነው ይላል። ማህበረሰቡ ሰላም ወዳድ፤ ችግር ሲፈጠር የሚያረጋጋ እንጂ የሚያባብስ ባለመሆኑ ችግሩ በአጭር ጊዜ ሊፈታ መቻሉን ያስታውሳል።
‹‹ህዝቡ ከተማሪዎች ጋር አብሮ የሚቸገር ነበር። እያንዳንዱ ተማሪ ከህዝቡ ጋር ቅርበት ነበረው። ችግር ሲከሰትም ህዝቡ ተማሪዎችን በማረጋጋት ችግሩ እስኪያልፍ በጉያው ይዞን ቆይቷል። ሲረጋጋም ግቢው ድረስ በመውሰድ ትምህርት መጀመራችንን አረጋግጦ ከዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ ጋር ተወያይቶ አስገብቶናል። ማህበረሰቡ ሰላም ወዳድ በመሆኑ የተፈጠረውን ችግር ለመቆጣጠር ያደረገው ሥራ ከፍተኛ ነው፤ ሊመሰገንም ይገባል።›› ብሏል ተማሪ ጉልላት።
‹‹ችግሩ ካጋጠመበት ጊዜ ጀምሮ ሁኔታው ተረጋግቶ ትምህርት እስኪጀምሩ ድረስ እኔ ጋር ብቻ ሳይሆን በበርካታ የከተማው ነዋሪ ቤት ውስጥ ተማሪዎች ችግሩን አሳልፈዋል። በኋላም ሁኔታው ሲረጋጋ ዩኒቨርሲቲው ድረስ ሄጄ መግባታቸውን እና ትምህርት መጀመራቸውን አረጋግጬ ተመልሻለሁ፤ ትምህርት ከተጀመረም በኋላ ከሌሎች የከተማው የህብረተሰብ ክፍል ጋር በመሆን ተማሪዎቹን የማረጋጋት ሥራ ሰርተናል።›› ሲሉ አቶ ፍቃዱ ሁኔታውን አስረድተዋል።
በዚህ ሰፊ ሥራ የንግዱ ማህበረሰብን ጨምሮ ሁሉም አካል የሚጠበቅበትን እያደረገ ይገኛል የሚሉት አቶ ፍቃዱ ወላጆችና የከተማው ህዝብ፣ ተማሪዎቹ ትምህርታቸውን እንዲማሩ ሁኔታው ሰላማዊ ሊሆንላቸው ይገባል የሚል ፅኑ አቋም አለው ብለዋል። ወጣቶቹ ከየትኛውም ፖለቲካ ርቀው እውቀትን ብቻ ማካበት አለባቸው። ይህ አስተሳሰብ በሁሉም ኢትዮጵያዊ ውስጥ መግባባት ላይ ሊደረስ ይገባል። ወጣቱ ነገ አገሩን በእውቀት እንዲመራት ዛሬ መማር አለበት ብለዋል- አቶ ፍቃዱ።
በዩኒቨርሲቲ ውስጥ ያለው ተማሪ የሚያሳየው የተለየ ባህሪና አስተሳሰብ ከየትም አላመጣውም፤ ከወላጅ፣ ከማህበረሰቡ እና ከአገሪቱ ፖለቲካ የተቀዳ ነው። በመሆኑም ወላጆች ተማሪዎች ከሚጠበቅባቸው ሚና አኳያ ፖለቲካው ለልጆቹ በልኩ ቢሆን የተሻለ እንደሆነም አቶ ፍቃዱ መክረዋል። በተለይ በተግባር ከሚሆነው ይበልጥ በወሬ የሚጠፋው እየበለጠ በመሆኑ ተማሪውም ሆነ ወላጅ እውነቱ የት ጋር ነው የሚለውን በሚገባ መለየት አለበት። ስለዚህ ብሔር መሰረት አድርጎ የሚናፈሰው ወሬ ትውልድ የሚያጠፋ በመሆኑ ሁሉም አካል ጥንቃቄ ሊያደርግ ይገባል ብለዋል።
ተማሪዎቹ ባስተላለፉት መልዕክት እናዳስ ታወቁት የአካባቢው ማህበረሰብ ለተማሪዎቹ ያደረገው ድጋፍ እና የሰራው የማረጋጋት ሥራ ለሌሎች አካባቢዎች ትልቅ ትምህርት ይሆናል። ማህበረሰቡ ችግሩ ከመከሰቱ አንድ ወር አስቀድሞ ተማሪዎች ከተማ ውስጥ ካሉ የተለያዩ ቤተሰቦች ጋር በፈጠረው ቤተሰባዊ ግንኙነት ምክር፣ ድጋፍ እና ተግሳፅ ያገኙ እንደነበር ያስታውሳሉ። በዚህም ሁኔታ ‹‹የሚመክረን አባት እና እናት ነበረን። እዚህ ዩኒቨርሲቲ ከገባን በኋላ ነው ከአቶ ፍቃዱ ጋር የተዋወቅነው፤›› ሲሉም ተናግረዋል።
አቶ ፍቃዱም ባስተላለፉት መልዕክት፤ በየትኛውም ክልል ባሉ ዩኒቨርሲቲዎች ዙሪያ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች ወጣቱ የአገር ተረካቢ መሆኑን መረዳት አለበት።በመሆኑም ለልጆቹ የሚመኘውን ሰላም እና ደህንነት በአቅራቢያው ባሉ ዩኒቨርሲቲዎች እየተማሩ ያሉ ወጣቶችን እንደራሱ ልጆች በመቁጠር አስፈላጊውን ድጋፍ ሊያደርግላቸው ይገባል ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል። ይህ ሲሆን ችግር ቢፈጠርም ጉዳቱ የከፋ አይሆንም ባይ ናቸው።
‹‹ሁላችንም ዩኒቨርሲቲ የሚማሩ ልጆች አሉን። ለልጆቻችን ሰላምና ምቾት እንደምንፈልገው ሁሉ ብዙ ርቀት ተጉዘው በእኛ አካባቢ ባሉ ዩኒቨርሲቲዎች ለመማር የመጡ ተማሪዎችን እንደራሳችን ልጆች ማየት እና ሰላማቸውን መጠበቅና ማስጠበቅ ይኖርብናል። በመሆኑም ችግር ተከሰተም አልተከሰተም ልጆቹ ተረጋግተው ትምህርታቸውን እንዲማሩ እገዛ ማድረግ ይገባናል›› ሲሉም አቶ ፍቃዱ አሳስበዋል።
አዲስ ዘመን ኅዳር 18/2012
ሀብታሙ ስጦታው