አዲስ አበባ፡- ባለሃብቶች ለወጣቶች ሰፊ የሥራ እድል መፍጠር የሚያስችሉ ትላልቅ ፕሮጀክቶችን በቅንጅት ለመገንባት የሚያስችል ምክክር እያደረጉ መሆናቸው ተገለጸ።
የአማራና ኦሮሚያ ባለሃብቶች ልዩ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ ፍሬዓለም ሽባባው ከአዲስ ዘመን ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳስታወቁት፣ በአገሪቱ የሚገኙ ባለሃብቶች በአንድ ላይ ተቀናጅተው የጋራ አቅም በመፍጠር የአገሪቱን ወጣቶች የሥራ አጥነት ችግር መቅረፍ የሚያስችሉ ትላልቅ ፕሮጀክቶች ለመገንባት ውይይቶች መካሄድ ጀምረዋል።
በአማራና በኦሮሞ ባለሃብቶች መካከል ውይይቶች እንደተደረጉም የገለጹት ወይዘሮ ፍሬዓለም፣ የሀገሪቱ ወጣቶች በሰፊው በስራ ላይ አለመሰማራታቸው የሰላምና የጸጥታ ችግሮችን በማባባስ በኩል ከፍተኛ አስተዋጽኦ ስላለው እነዚህን ወጣቶች ሥራ ማስያዝ አገራዊ ሰላምና መግባባትን መፍጠር ያስችላል ብለዋል።
ባለሃብቶች በተናጠል ሥራ ለመፍጠር የሚ ያደርጓቸው እንቅስቃሴዎች ካለው የሥራ አጥ ቁጥር አንጻር እዚህ ግባ የሚባል አይሆንም ያሉት ወይዘሮ ፍሬዓለም፣ ስለዚህ የሀገሪቱ ባለሃብቶች በጋራ መክረው የሥራ አጥ ወጣቶችን የሥራ እድል የሚፈጥሩ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን ለመገንባት በመመካከር ላይ መሆናቸውን አመልክተዋል።
ሀገሪቱ ከኢትዮጵያ ወጣቶች ባለፈ ለአፍሪካ ወጣቶች የሚበቃ የሥራ እድል መፍጠር የሚያስችል ሀብት ቢኖራትም በተለያዩ ቦታዎች የሚስተዋሉት የሰላም እጦቶች ባለሃብቱ ገብቶ መስራት እንዳይችል ስጋት የሚፈጥሩ ከመሆናቸውም በላይ አዳዲስ ባለሀብቶች መምጣት እንዳይችሉ ያደርጋሉ ብለዋል።
ወይዘሮ ፍሬዓለም አያይዘውም ይሄን አገራዊ መጥፎ ስዕል ማስወገድና መቀየር እንዲቻል ከወጣቶች ጋር በተለይም ከአማራና ከኦሮሞ ወጣቶች ጋር ሰፊ ውይይት የተደረገ ሲሆን በየአካባቢው የሚገኙ ወጣቶችን በመምከር፣ የባለሀብቱን ደህንነት በመጠበቅ፣ ለወጣቶች ሰፊ የሥራ አማራጮችን ይዞ የሚመጣውን ሀገራዊ የኢንቨስትመንት ሃይል በመጠበቅ የሥራ እድሉ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ከወጣቶቹ ጋር መተማመን ላይ መድረሳቸውን አስረድተዋል።
እንደ ወይዘሮ ፍሬዓለም ገለጻ ፣የአገራዊ ባለሃብቱ የምክክር ሂደቱን አጠናቅቆ ወደሥራ መግባት እስኪችል ድረስ የሰላሙ ሁኔታ አስተማማኝ ደረጃ ላይ ይደርሳል የሚል እምነት አላቸው። በዚህ የተነሳም የባለሃብቶቹን ኮሚቴ በተቋም ደረጃ በማሳደግ ለወጣቶች የሥራ እድል ጥያቄ አስተማማኝ ምላሽ መስጠት በሚያስችል ጠንካራ ቁመና እንዲኖረው ይደረጋል።
የአገራዊ ባለሃብቶች ንቅናቄ አካል የሆነው የአማራና የኦሮሞ ባለሃብት ውይይቶች የሀገሪቱ ወጣቶች ፍትሃዊ በሆነ መንገድ የሥራ እድል ተጠቃሚዎች መሆን እንዲችሉ ከቅጥር ጀምሮ ክትትልና እኩል ተጠቃሚ የሚያደርግ እንዲሆን ስምምነት ላይ መድረሳቸው በቀጣይ በጋራ ለሚመሰርቱት ግዙፍ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክት የአሰራር መሰረትን የሚጥል እንደሆነ ወይዘሮ ፍሬዓለም አስረድተዋል።
አዲስ ዘመን ህዳር 18/2012
ሙሐመድ ሁሴን