የአማራ ክልል የንብ ሀብት ካላቸው የሀገሪቱ አካባቢዎች አንዱ መሆኑን ከክልሉ የእንስሳት ሀብት ልማት ማስፋፊያ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።ምሥራቅ ጎጃም ዞን አዋበል ወረዳ ደግሞ ከክልሉ ከፍተኛውን ድርሻ ትይዛለች።
የአዋበል ወረዳ የእንስሳት እርባታ ቡድን መሪ አቶ ቴዎድሮስ ዋለልኝ እንዳሉት፣ በወረዳዋ እስከ 12ሺ የሚገመት የንብ መንጋ ይገኛል።ከዚህ ውስጥ ማዘመን የተቻለው 22 በመቶውን ብቻ ነው።ቀሪው በባህላዊ አሰራር ነው የሚከናወነው። በመሆኑም የሚፈለገውን ያህል ተጠቃሚ መሆን አልተቻለም።
በወረዳው ያለው ሀብት ሙሉ በሙሉ በዘመናዊ የንብ ማነብ ተግባር ቢከናወን እና የአበባ ጊዜን ብቻ ጠብቆ ከማልማት መላቀቅ ከተቻለ ከፍተኛ የሆነ የማርና የሰም ምርት በማግኘት ከሰብል ምርት በተጨማሪ ገቢ በማግኘት ኑሮን መለወጥ ይቻላል።ለብዙ ወጣቶችም የሥራ ዕድል ይፈጠራል ይላሉ።
ክልሉ ሀብቱን በአግባቡ በማልማት ዘርፈ ብዙ ጥቅሞችን ለማግኘት በዓለምአቀፍ ሥነነፍሳት ሳይንስ ሥነምህዳር ምርምር ማዕከል(አይ ሲ አይ ፒ ኤ) ጋር ወጣቶችን በማሳተፍ የተጠናከረ ሥራ በትብብር በመስራት ላይ መሆኑን የክልሉ የእንስሳት ሀብት ልማት ማስፋፊያ ኤጀንሲ ምክትል ኃላፊ አቶ ፈንቴ ቢሻው ይገልጻሉ።
በባህላዊ የንብ ማነብ የትም መድረስ አለመቻሉ በተግባር መታየቱን በመጠቆምም፣ወጣቶችን በማደራጀት ከአጋር ድርጅቱ ጋር የተጀመረውን ዘመናዊ የማር ልማት ሥራን በማጠናከር ተጠቃሚነትን የማሳደግ ሥራ ትኩረት ተሰጥቶት በመከናወን ላይ መሆኑን ያስረዳሉ።
በዓለምአቀፍ ሥነነፍሳት ሳይንስ ሥነምህዳር ምርምር ማዕከል (አይ ሲ አይ ፒ ኢ) የወጣቶች የስራ እድል ፈጠራ በሀርና በንብ ልማት ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ አቶ ልዑልሰገድ በላይሁን እንደገለጹት፣ ማዕከሉ ግብርናውን ለማገዝ ከመንግሥት ጋር በመሆን ከሚያከናውናቸው የተለያዩ የድጋፍ ሥራዎች የንብ ማነብና የማር ልማት ሥራ አንዱ ሲሆን፣ በአማራ ክልል በምሥራቅና በምዕራብ ጎጃም እንዲሁም በአዊና በዋግህምራ ዞኖች 13 ወረዳዎች ውስጥ እየሰራ ይገኛል።የልማቱ ሥራም ወጣቶችን ማዕከል ያደረገ የሥራ ዕድል ፈጠራ ሥራ ነው።ከ10ሺ 300 በላይ አባላት ያሏቸው 800 ኢንተርፕራይዞች በንብ ማነብና ማር ልማት ላይ ተሰማርተው ተጠቃሚ በመሆን ላይ ይገኛሉ።
እንደ አቶ ልዑልሰገድ ማብራሪያ፣ማዕከሉ ‹‹የሺ ፕሮጀክት›› ለወጣቶቹ በዋናነት የሚያደርግላቸው ድጋፍ ዘመናዊ የንብ ማነብ ክህሎት እንዲኖራቸው የእናት ንብ ማባዛት፣ምርቱ ከተመረተ በኋላ ገበያ ላይ እንዴት ማቅረብ እንደሚቻል፣ በአጠቃላይ የንግድና የአስተዳደር ስልጠና እንዲያገኙ ይደረጋል።
ከስልጠናው በኋላም ለእያንዳንዱ ኢንተርፕራይዝ ሁለት የንብ ቀፎ እና በንብ ቆረጣ ወቅት የሚጠቀሙበት አልባሳት በመስጠት ሥራው እንዲጀመር ይደረጋል ያሉት አቶ ልዑልሰገድ፣ ላመረቱት ምርት ማቀነባበሪያ ማሽን እና ማሸጊያ እንዲሁም የመሸጫ ሱቅ በመገንባት ድጋፍ ይደረጋል።ምርቱ ገበያ ላይ እስኪቀርብም ተከታታይ ድጋፍ አይለያቸውም ይላሉ።
ማዕከሉ ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ እያደረገ ባለው ድጋፍ ተስፋ ሰጭ ውጤት እየታየ መሆኑን የሚገልጹት አቶ ልዑልሰገድ፣ እስከ ሁለት መቶ ሃምሳ ሺ ብር ብድር በመበደር ሥራቸውን ያሳደጉና ብድራቸውንም በወቅቱ በመመለስ ውጤታማ የሆኑ ኢንተርፕራይዞች መኖራቸውን ጠቁመዋል።ይህ ጥረታቸው ለማደግ ያላቸውን ፍላጎት እንደሚያሳይ ያመለክታሉ።
መንግሥት የንብ ማናቢያ ጣቢያ በማመቻቸትና ወጣቶችን በመመልመል፣ማዕከሉ ደግሞ የተለያዩ ድጋፎችን በመስጠት ለወጣቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር በሚደረገው ጥረት የሚያጋጥመውንም ተግዳሮት ተከታትሎ በመፍታት የተሻለ ሥራ እየተሰራ መሆኑንም አቶ ልዑልሰገድ ጠቅሰው፣ ተግዳሮቶቹ ውጤታማ ለመሆን ከመጓጓት የሚመነጩና አልፎ አልፎም በኢንተርፕራይዞች መካከል የሚከሰቱ መሆናቸውን ይጠቅሳሉ።
በምሥራቅ ጎጃም አዋበል ወረዳ ሉማሜ ከተማ በተካሄደው የማር ምርት ማስተዋወቂያ ፌስቲቫል ላይ ምርቶቻቸውን ካቀረቡት 62 ኢንተርፕራይዞች መካከል ኪሮስና ጓደኞቹ አናቢዎች ማህበር ሰብሳቢ ወጣት ኪሮስ ቢተው በሰጠው አስተያየት እርሱና አባላቱ ስለማር አመራረት ግንዛቤ አልነበራቸውም።ስልጠናውን አግኝተው ወደ ሥራ ከገቡ በኋላ ጥቅሙ እንደገባቸው እና ጠንክረው በመስራት ለመለወጥ ዝግጁ መሆናቸውን ያስረዳል።
የወጣቶቹን እንቅስቃሴ አስመልክቶ በወረዳው በተዘጋጀ ውይይት ላይ ከተሳተፉት መካከልም በወረዳው የዳበና ቀበሌ አስተዳዳሪ አቶ ሞገስ አድማስ የኢንተርፕራይዞቹን እንቅስቃሴ የተመለከቱ ወጣቶች ለመደራጀት ፍላጎት እያሳዩ መሆናቸውን በመጠቆም ወረዳው ለሌሎችም ያለውን ተሞክሮ በማካፈል የሥራ ዕድል ፈጠራው ሊጠናከር እንደሚገባ አመልክተዋል። ኢንተርፕራይዞቹን የበለጠ በማበረታታት ለስኬት እንዲበቁ በማድረግ በኩል ከአመራሩ የበለጠ ድጋፍ እንደሚጠበቅም ሀሳብ ሰጥተዋል።
አዲስ ዘመን ህዳር 18/2012
ለምለም መንግሥቱ