ዓለማችን በሰው ሰራሽና በተፈጥሮ አደጋዎች ምክንያት በየዓመቱ በርካታ ሰዎችን እና በቢሊየን ዶላር የሚገመት ንብረትን እንደምታጣ ቢቢሲ የጥናት ውጤቶችን መሰረት በማድረግ ያብራራል። ከዚህ ችግር አሳሳቢነት በመነሳት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በአጀንዳ 2030 ግቡ በዓለማችን የሚከሰቱ ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ አደጋዎችን በመቀነስ ቀጣይነት ያለው እድገት የማስመዝገብ ዓላማ ይዞ እየሰራ ነው። ይህ መርሀ ግብርም በአንዳንድ የአፍሪካ ሀገራት ተግባራዊ በመደረግ ላይ ይገኛል
አፍሪካዊቷ ሀገር ሴኔጋል በየወቅቱ በሚከሰቱ ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ አደጋዎች ምክንያት በርካታ ዜጎቿን አጥታለች። የማህበራዊ ህይወት መመሳቀልና የንብረት መውደም ከሚከሰትባቸው ግንባር ቀደም የአፍሪካ ሀገራት መካከል አንዷ እንደሆነች ይጠቀሳል። ዛሬ ግን የሚገጥሟትን አደጋዎች አስቀድማ ለመከላከልና ለመቆጣጠር በወሰደቻቸው እርምጃዎች ተጨባጭ ለውጥ እያስመዘገበች ትገኛለች።
በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎች ስትመሰቃቀል የኖረችው ሴኔጋል አደጋው በሀገሪቱ እያስከተለ ያለውን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ቀውስ ለመቆጣጠር እንዲያስችላት ለጉዳዩ ባለቤት መስጠት የመጀመሪያ ተግባሯ ነበር።በመሆኑም በቴክኖሎጂ የታገዘ የማህበረሰብ ጥበቃና ክትትል ተቋምን መሰረተች።እንደ ጎርፍ፣ የመሬት መንሸራተት፣ ርዕደ መሬት፣ ድርቅ፣ የእሳት አደጋ፣ የመኪና አደጋ፣ የአንበጣ ወረርሽኝ፣ የወንዞችና የውቅያኖስ መጠን መጨመር እና ሌሎች አደጋን የሚያስከትሉ ሁኔታዎችን ለየች። በመቀጠልም እያንዳንዱን አደጋ ለመቆጣጠርና ለመቀነስ የሚያስችል 3 ሺህ አባላት ያሉት የሰለጠነ የሰው ሃይል ከቴክኖሎጂ ጋር በማስተሳሰር ወደ ሥራ ገባች። አደጋዎችን የመከላከል አቅሟን ለማጎልበትም በአፍሪካ አደጋን የመከላከል ኢንሹራንስ ውስጥ ታቀፈች
አደጋዎችን የመከላከል ሃላፊነት ወስዶ የሚንቀሳቀሰው አዲሱ ተቋም ለእነዚህ የአደጋ ሥጋቶች አፋጣኝ ምላሽ በመስጠት በየዓመቱ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ሞት ለማስቀረት የሚያስችል ዕቅድ አውጥቶ ስራውን ተያያዘው። በሁሉም ዘርፍ የሚከሰቱ አደጋዎችን ለመቀነስ አንዳንዶቹንም ለማስቀረት እንደየሁኔታው አስፈላጊ የሚባሉ ቴክኖሎጂዎችን ጥቅም ላይ ማዋልም ተቻለ።
ለምሳሌ የሀገሪቱ የእሳት አደጋ ብርጌድ ካምፖቹን በማስፋት አደጋዎች የት ቦታ እንደተከሰቱ በሚጠቁም ምስል ማስተላለፊያ ካሜራዎች ታግዞ ቀደም ሲል በእሳት አደጋ ይደርስ የነበረውን ጥፋት በሚያስገርም ሁኔታ መቀነስ ቻለ። ጎርፍና ፣ የመሬት መንቀጥቀጥን ለመሳሰሉ አደጋዎችም የቅድመ ማስጠንቀቂያ አላርም በማሰማት ሰዎችን የማዳን ስራ መስራት ተቻለ፡፡ በተለያዩ የአደጋ ሥጋቶች ላይ ሁሉ ጥብቅ ቁጥጥርና ክትትል በማድረግም አበረታች ውጤቶች ተመዘገበ።
ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ሴኔጋል አደጋን አስቀድሞ የመከላከል እርምጃ ከመውሰዷ በፊት እ.ኤ.አ በ2015 ብቻ በዳካር ከተማ 2ሺ የእሳት አደጋዎች ተመዝግበዋል።በከባድ ዝናብና ጎርፍ የተጠቁ 80 ህንጻዎች ተደርምሰዋል።372 ህንጻዎችም ለአደጋ ተጋላጭ በመሆናቸው ከአገልግሎት ውጭ ለመሆን ተገደዋል። በተጠቀሰው ዓመት ብቻ 609 ዜጎቿን በሞት ስታጣ 21 ሺ 505 ሰዎችም ለተለያዩ ችግሮች ተዳርገዋል። ሴኔጋል የከተሞቿን መስፋፋትና እና ዕድገት ተከትሎ የመሰረተ ልማት ችግሮችም ጎልተው ይታዩባት ነበር።
አዲሱ ተቋም አጠቃላይ ችግሮችን ማዕከል በማድረግ ባደረገው እንቅስቃሴ ዛሬ ሴኔጋል እንደምሳሌ ለመጠቀስ በቅታለች።በተለይ የአደጋ ስጋት የነበሩት ህንጻዎቿም ትኩረት ተሰጥቷቸው በተሟላ ግብዓትና በጠንካራ መሰረት ላይ መታነጽ በመጀመራቸው ለውጥ ታይቶባቸዋል።በከተማና በገጠር ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውሶችን ሲያስከትሉ የነበሩ ክስተቶች ሁሉ ክትትልና ቁጥጥር ተደርጎባቸው መሻሻል ታይቶባቸዋል።እ.ኤ.አ ከ2015 እስከ 2030 ዓለማችን ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋዎችን በመከላከል ቀጣይነት ያለው ዕድገት ታስመዘግባለች የሚለውን የተባበሩት መንግስታት አጀንዳ 2030 በሥራ እየተረጎሙ ካሉ የአፍሪካ ሀገራት ሴኔጋል ግንባር ቀደም ተዋናይ እየሆነች መጥታለች።
በየጊዜው የሚገጥማትን ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ አደጋ ለመቋቋም ስትል የታቀፈችበት የአፍሪካ አደጋን የመከላከል ኢንሹራንስ በከፍተኛ ሁኔታ እንደጠቀማት ይነገራል።በአንድ ጊዜ ብቻ 23 ነጥብ 1 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር የካሳ ክፍያ በማግኘት ለችግሮቿ መፍቻነት ተጠቅማበታለች፡፡ በቅርቡም በሃይለኛ ዝናብ ምክንያት በሰብል ምርቷ ላይ ከፍተኛ አደጋ ደርሶ 22 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ካሳ ተቀብላለች። ከኢንሹራንስ የምታገኘውን በርካታ ገንዘብ በተለይም በተፈጥሮ አደጋ ጉዳት ለደረሰባቸው የህብረተሰብ ክፍሎች በማዋል የመልሶ ማቋቋም ስራን ትሰራበታለች።
የተባበሩት መንግስታት የአደጋና ስጋት መከላከል ጽሕፈት ቤት አጀንዳ 2030ን ተግባራዊ በማድረግ በአፍሪካ ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ አደጋን በመከላከልና በመቀነስ ቀጣይነት ያለው ዕድገት ለማስመዝገብ እየሠራ ነው።በአፍሪካ አህጉር ይህን መርሀ ግብር የሚደግፉት ዩናይቴድ ኪንግ ደም ፣ ጀርመን፣ ስውዲን፣ካናዳ፣ ፈረንሳይ፣ ሲውዘርላንድ አሜሪካ እና ሮክ ፌለር ፋውንዴሽን ሲሆኑ ከአፍሪካ ህብረትና ከኢንሹራንሶች ጋር በትብብር ይሠራሉ። በይበልጥም ለተፈጥሯዊ አደጋዎች እና በድንገት ለሚከሰቱ ወረርሽኞች አፋጣኝ ምላሽ በመስጠት የአህጉሪቱን ቀጣይ ዕድገት ለማረጋገጥ አጋርነታቸውን እያሳዩ ናቸው፡፡
ሴኔጋል እየወሰደች ያለችው ቅድመ አደጋን የመከላከል እርምጃ በርካታ የሀገሪቱ ዜጎችን ከሞት የመታደግ አቅም እንደፈጠረላትና ሌሎች የአፍሪካ ሀገራትም ሊከተሏት እንደሚገባ የጥናት ባለሙያዎች አስተያየታቸውን በመስጠት ላይ ይገኛሉ ፡፡
አዲስ ዘመን ኅዳር 18/2012
ኢያሱ መሰለ