አዲስ አበባ፡- የተሽከርካሪ ስርቆትና በጦር መሳሪያ የተደገፈ ዘረፋን ለማስቆም በተሰራ ሥራ የህዝቡን ስጋት መቀነስ መቻሉን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ገለጸ፡፡
የኮሚሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተሩ ኮማንደር ፋሲካው ፋንታ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፤ ባለፉት ሦስት ወራት ህዝቡ ከወንጀል ስጋት ነጻ ሆኖ እንዲንቀሳቀስ የተሽከርካሪ ስርቆትና በጦር መሳሪያ የተደገፈ ዘረፋን ጨምሮ በከተማው ለኅብረተሰቡ በአደገኛነት ከተለዩት 10 የተለያዩ ወንጀሎች ላይ ትኩረት ተደርጎ መሰራቱን ጠቁመዋል፡፡
የተሽከርካሪና የተሽከርካሪ ውስጥ ዕቃ ስርቆት፣ በጦር መሳሪያ የተደገፈ ዘረፋ፣ ለህብረተሰቡ ስጋት ተብለው ከተለዩት መካከል እንደሚመደቡም የጠቆሙት ዳይሬክተሩ፤ ኮሚሽኑ ከሌሎች የጸጥታ አካላትና ከህብረተሰቡ ጋር በመቀናጀት የቁጥጥር ሥራ መስራቱን ተናግረዋል፡፡
በቪትዝ መኪና የተደገፈ ቅሚያና የመሰረተ ልማት ስርቆት እየተፈጸመ እንደሚገኝ ያመለከቱት ኮማንደር ፋሲካው፤ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት ድርጊቱን ለማስቆም እየተሰራ እንደሚገኝ አመልክተዋል፡፡ የወንጀል ድርጊቱ በዋናነት ‹‹ከተማው ሰላም አይደለም›› የሚል መልዕክት ለማስተላለፍ እንደሚፈጸም ጠቁመዋል፡፡
ዳይሬክተሩ የመኪና አከራዮች ንብረቶቻቸውን ሲያከራዩ ለምን አላማ እንደሚውል፣ የተከራዮቹን ባህሪይና የስራቸውን ሁኔታ የማረገጋጥ ኃላፊነት እንዳለባቸውም አመልክተው፤ ሲያከራዩ የተዋዋሉበትን መረጃ በቅርባቸው ለሚገኙ ጣቢያዎች ቢያሳውቁ ወንጀሉ እንዳይፈጸም ለመከላከልና ቢፈጸምም ፈጥኖ ለማወቅ እንደሚያስችል ተናግረዋል።
ዳይሬክተሩ በሩብ ዓመቱ ከተመዘገበው የተሽከርካሪ ስርቆት አንዳንዶቹ ሰዋራ ስፍራ ተጥለው እየተገኙ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ ደብዛቸው የሚጠፉ መኪኖች ቢኖሩም ቁጥራቸው አነስተኛ መሆኑንና የተሰረቀውን ተሽከርካሪ ትክክለኛ ቁጥር ለመግለጽ እንደሚያስቸግር ተናግረዋል።
መኪናዎቹ ተሰረቁ ቢባልም አንዳንዶቹ ምንም ሳይነኩ፤ ቀሪዎቹ ቅሚያና ስርቆት ተፈጽሞባቸውና አካላቸው ተወስዶ ሰዋራ ስፍራ ተጥለው እንደሚገኙ የገለጹት ዳይሬክተሩ፤ ወንጀለኞቹ ተሽከርካሪዎች የሚሰርቁት የራሳቸውን ዓላማ ለማስፈጸም በመሆኑ በሚደረጉ የምርመራ ስራዎች ዓላማቸው ምን እንደሆነ ምላሽ እንደሚያገኝ ተናግረዋል።
እንደ ዳይሬክተሩ ማብራሪያ በሩብ ዓመቱ ህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ከፍተኛ እንቅስቃሴ ስለነበረው ኮሚሽኑ ከህዝቡ የሚደርሰውን ጥቆማ መሰረት በማድረግ ከብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ጋር በመተባበር 25 የተለያዩ ህገ ወጥ የጦር መሳሪያዎች፣ 83 ሽጉጦችና አራት ሺ 863 የሽጉጥ ጥይቶችና በርካታ ስለት መሳሪያዎችን በድንገተኛ ፍተሻና በጥቆማ በቁጥጥር ስር አውሏል።
ከብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎትና ከህብረተሰቡ ጋር በመቀናጀት ባደረገው ፍተሻና ቁጥጥር የተለያዩ አገራት ሃሰተኛ ገንዘብ፣ የገንዘብ ማተሚያ ማሽንና በወንጀል ተግባሩ የተሰማሩ የአገር ውስጥና የውጭ አገር ዜጎችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን የተናገሩት ዳይሬክተሩ፤ 398 ሺ 656 ዶላር ፣ አንድ ሺ 650 ዩሮ፣ 10 ሺ ናቅፋ፣ 400 ፓውንድ፣ አምስት ሺ 500 ሃሰተኛ ብርና 15 ግራም ወርቅ መያዛቸውንም አመልክተዋል።
ዳይሬክተሩ በሩብ ዓመቱ አምስት በጦር መሳሪያ የተደገፈ ዘረፋ መፈጸሙን ፤ ሁለቱ በሙከራ ደረጃ መክሸፋቸውን ፤ ወንጀሉ በፋይናንስ ተቋማት ላይ እንደተፈጸመና ወንጀል ፈጻሚዎቹ ከየተቋማቱ አንዳንድ ሠራተኞች ጋር እንደተመሳጠሩ በምርመራ መረጋገጡንና በህዝቡ ትብብር መያዛቸውን ተናግረዋል።
ዳይሬክተሩ በመሰረተ ልማት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን አስመልክተውም፤ በርካታ የቴሌ፣ የመንገድ አካፋይ ብረቶች፣ የመብራት ኬብሎች፣ የውሃ መስመሮች፣ የቴሌ ቱቦ ክዳንና የቴሌ መስመር የተዘረጋበትን እንጨት ቆርጠው ሲወስዱ የነበሩ ወንጀል ፈጻሚዎች መያዛቸውንም አመልክተዋል።
ባለፈው ዓመት ከተጠረጠሩ 115 መካከል 103 የሚደርሱት ተይዘው ከአንድ ዓመት እስከ 10 ዓመት መቀጣታቸውንና አንዳንዶቹም ጉዳያቸው እየታየ እንደሚገኝና ያልተያዙ ተጠርጣሪዎችን አድኖ ለመያዝ እየተሰራ መሆኑንም አክለው ተናግረዋል።
ዳይሬክተሩ የኑሮ ውድነትን ለማባባስ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችን ለመከላከል ኮሚሽኑ መንቀሳቀሱን በመጠቆም፤ በተለያዩ የገበያ ቦታዎች ደላሎች በቀጥታ ከሻጮች ጋር በመመሳጠር ህጋዊ ነጋዴዎችን ከገበያ ለማስወጣት የሚያደርጉትን ተግባር የማስቆም ሥራ መሰራቱን እንዲሁም ለውጭ ገበያ መቅረብ የሚገባው የቡና ምርት በግለሰብ መጋዘን ተከማችቶ መያዙን ተናግረዋል።
90 በመቶ በወንጀል ድርጊቱ ተሳታፊዎችን እጅ ከፍንጅ የያዘው ኅብረተሰቡ ሲሆን፤ 10 በመቶውንም ህዝቡ ለኮሚሽኑ ባደረሰው ጥቆማ መያዙን ፤ ኅብረተሰቡ ትብብሩን አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ አቅርበዋል።
ዳይሬክተሩ በሞተር ብስክሌት ተደግፎ ይደረግ የነበረው ቅሚያና ዘረፋ ከፍተኛ ስጋት ፈጥሮ እንደነበረ አስታውሰው፤ ከተማ አስተዳደደሩ መመሪያ አውጥቶ በህጋዊ መንገድ የተመዘገቡ ብቻ እንዲንቀሳቀሱ በማድረጉ የወንጀል ድርጊቱን ማስቆም እንደተቻለ ተናግረዋል።
አዲስ ዘመን ህዳር 17/2012
ዘላለም ግዛው