አዲስ አበባ፤ የአዋሽ-ወልዲያ የባቡር መስመር ኤሌክትሪክ ዝርጋታ ሥራ አለመጀመርን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደማያውቀው ገለጸ ።
በምክር ቤቱ የከተማ ልማት፣ ኮንስትራክሽንና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ አሸናፊ ጋኢሚ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት ቋሚ ኮሚቴው ያለው ሪፖርት የባቡር መስመሩ አጠቃላይ ሥራ አፈጻጸም 97 በመቶ መድረሱን ነው።
እንደ አቶ አሸናፊ ገለጻ የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን የላከላቸው የዘንድሮ የሩብ ዓመት ሪፖርት የሚያመለክተው የኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታውና ሌሎች ስራዎች እየተጠናቀቁ መሆኑንና አገልግሎት ለመጀመርም መስመሮቹን በመሞከር ላይ መሆኑን ነው።
‹‹ኮርፖሬሽኑ በሪፖርቱ የኤሌክትሪክ ሃይል አቅርቦት ችግር እንደገጠመው አልገለጸም›› ያሉት ሰብሳቢው “ በኮርፖሬሽኑና በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይል መካከል አለመግባባት መኖሩን መረጃ የለንም። ስራው እስከ አሁን የተጓተተበትን ምክንያት አጣርተን ችግሩን በመፍታት የማስተካከያ እርምጃ እንወስዳለን›› ብለዋል።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይልን የሚቆጣጠረው የተፈጥሮ ሀብት፣ መስኖና ኢነርጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ ፈቲያ የሱፍ፤ በበኩላቸው የአዋሽ-ወልዲያ የባቡር መስመር ኤሌክትሪክ ዝርጋታ ችግር መኖሩን እንደማያውቁና ተቋሙም የኤሌክትሪክ ዝርጋታ ለማድረግ በእቅዱ ማካተ ቱንም ያመለክታሉ።
ሰብሳቢዋ እንደገለጹት በተቋማት መካከል ተቀናጅቶ ለመስራት በጋራ አያቅዱም፤ አይፈጽሙም፤ ይህ መሆኑ ደግሞ ለዚህ መሰል ችግር ዳርጓል፤ ችግሩን ለመቅረፍ ተቋማት በጋራ አቅደው መፈጸም ይኖርባቸዋል።
አዲስ ዘመን ጋዜጣ በጥቅምት 12 ቀን 2012 ዓ.ም ዕትሙ ላይ ኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ምክትል ዋና ስራ አስፈፃሚና የባቡር ኔትወርክ ዘርፍ ኃላፊ ከሆኑት አቶ የኋላሸት ጀመረ ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ በ2010 ዓ.ም የኤሌክትሪክ ኃይል ቀርቦላቸው የሙከራ ሥራ መጀመር እንደነበረባቸው መግለጻቸው ይታወሳል።
በወቅቱ ኃላፊው እንዳሉት ኤሌክትሪክ ኃይል ባለመቅረቡ አንድ ነጥብ ሰባት ቢሊዮን ብር የወጣበት ፕሮጀክት ያለምንም ሥራ መቀመጡንና ችግሩንም ከጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት እስከ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማሳወቃቸውን፤ የኤሌክትሪክ መስመር ተዘርግቶ ኃይል ላለመቅረቡ ኃላፊነቱን መውሰድ ያለበትም ኮርፖሬሽኑ መሆኑን ተናግረው ነበር።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኮሙኒኬሽን ኃላፊ አቶ ሞገስ መኮንን በበኩላቸው በወቅቱ በሰጡት ምላሽ ‹‹ኮርፖሬሽኑ ውል ሳይገባና ክፍያ ሳይፈጽም የኤሌክትሪክ መስመር አይዘረጋም›› ብለው ነበር።
ተቋማቱ ተስማምተው ውል ገብተው ክፍያ ፈፅመው መስመሩን ለመዘርጋት 18 ወራት እንደሚወስድ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል መግለጹ ይታወሳል።
አዲስ ዘመን ህዳር 17/2012
አጎናፍር ገዛኸኝ