አዲስ አበባ፦ የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎት በሚፈለገው ደረጃ ውጤታማ አለመሆኑን የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ገለጸ፡፡ የማህበረሰብ ንቅናቄን በመፍጠር ግንዛቤው ከፍ እንዲል እንደሚሰራም ጠቁሟል።
በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የእናቶችና የህጻናት ጤና ዳይሬክቶሬት የቤተሰብ እቅድ ከፍተኛ ኤክስፐርት አቶ ግርማ ገመቹ ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንዳሉት፡የቤተሰብ እቅድ አገልግሎቱን ተደራሽ ለማድረግ የተሰሩ ስራዎች ውጤታማ ቢሆኑም በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተለያዩ ፖለቲከኞች ጉዳዩን አጀንዳ በማድረግ ህብተረተሰቡን ማደናገራቸው ስራው በሚፈለገው ልክ ውጤታማ እንዳይሆን አድርጎታል።
እንደ አቶ ግርማ ገለጻ እ.አ.አ. በ 2011 የኢትዮጵያ የጤና ዳሰሳ የጥናት ውጤት መሰረት ትዳር ከመሰረቱ 100 ሴቶች ውስጥ የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎት ተጠቃሚ የነበሩት 15 በመቶ ብቻ ነበሩ፤ ይህ ቁጥር እ.አ.አ. በ 2016 ወደ 36 በመቶ ከፍ ያለ ሲሆን፤ በ 2019 ደግሞ 42 በመቶ ደርሷል።
አቶ ግርማ ቁጥሩ ከዓመት ዓመት እድገት እያሳየ ቢሆንም ከፖለቲከኞች ውትወታ ባሻገር የግንዛቤ እጥረት የጎንዮሽ ጉዳቶች ፣የአካባቢ ተጽዕኖ ውጤቱ በተሰራው ልክ ከፍ ላለማለቱ ምክንያቶች ናቸው ብለዋል።
ጤና ሚኒስቴር የቤተሰብ እቅድ አገልግሎት ላይ ለሚሰማሩ ባለሙያዎች በቂ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ከማድረግ ጀምሮ በጤና ተቋማት ግብዓቶች በዓይነትና በብዛት እንዲኖሩ በማድረግ በኩልም ሰፊ ተግባር እያከናወነ በመሆኑ አንድ ሰው ወደ ጤና ተቋም መጥቶ የሚፈልገውን አገልግሎት በቀልጣፋ ሁኔታ እንዲያገኝ ለማድረግ መቻሉንም አቶ ግርማ ተናግረዋል።
የማህበረሰብ ንቅናቄን በመፍጠር አንድ ሰው ስለ ቤተሰብ እቅድ ምን ማወቅ አለበት የሚለውን ፕሮግራም በማዘጋጀት ለሀይማኖት አባቶች፣ ለጎሳ መሪዎች፣ ለሴቶችና ወጣቶች፣ ለጤና ቢሮና ለሴክተር ኃላፊዎች የውይይት መድረክ በማዘጋጀት ግንዛቤው ከፍ እንዲል እንደሚሰራም ጠቁመዋል።
የቤተሰብ እቅድ አገልግሎት በተለይም የእስልምና ዕምነት ተከታዮችን ያካተተ እንዲሆን በሌሎች አገሮች ውጤት ያመጡ ተሞክሮዎችን ወደ አገራችን ተጨባጭ ሁኔታ በመቀየር ተግባራዊ ማድረግም ሌላው ሥራ መሆኑን ጠቁመው፣ በዚህም የዕምነቱ ተከታዮችን ተጠቃሚ የማድረግ ስራው ከፍተኛ ውጤት እያሳየ መሆኑን ጠቅሰዋል።
እኤአ በ2020 ስድስት ሚሊየን የሚጠጉ አዲስ የቤተሰብ እቅድ ተጠቃሚዎችን ለማፍራት እየተሰራ መሆኑን የገለጹት ያሉት አቶ ግርማ፣ እዚህ ላይ ለመድረስም ቀደም ሲል ሲሰራባቸው የቆዩ አካሄዶችን አጠናክሮ በመቀጠል፣ አዳዲስ ስራዎችንም ለመፍጠር ጥረት ይደረጋል ብለዋል።
ከዚሁ ጉዳይ ጋር በተያያዘ በወለጋ ዩኒቨርሲቲ መምህርና በኢኮኖሚክስ የትምህርት ክፍል ረዳት ፕሮፌሰር ዶክተር ዘላለም እጅጉ እንደሚሉት፣የህዝብ ቁጥር ሀብት ሊሆን የሚችለው እንደ አገራቱ የተፈጥሮ ሀብትና የእድገት ደረጃ ነው።የህዝብ ቁጥር ሲጨምር የሚወለዱት ልጆች መጠለያ፣ ምግብ ፣ልብስ፣ ትምህርት በኋላም ውጤታማ የሚያደርግ ሥራ ይፈልጋሉ፤ እንደ አገር ይህንን ማድረግ የሚከብድ በመሆኑ በተለይም ለእኛ የህዝብ ቁጥር መጨመር ስጋት እንጂ ጥቅም የለውም ።
እንደ ዶክተር ዘላለም ገለጻ ኢትዮጵያ ከፍተኛ የሆነ የህዝብ ቁጥር ቢኖራትም ወደ መልካም አጋጣሚ ቀይሮ መጠቀም ላይ ብዙ አልተሰራም።የህዝብ ቁጥር እድገታችንን አልተቆጣጠርነውም፣ በአሁኑ ወቅት በየዓመቱ ከአንድ ነጥብ ስድስት እስከ ሁለት ሚሊዮን ስራ ፈላጊ ወደ ኢኮኖሚው ይገባል፤ ይህንን ያህል ሰው የሚችል የስራ እድል ግን እየተፈጠረ አይደለም፤ ከዚህ አንጸር የህዝብ ቁጥራችን ስጋት እንጂ መልካም አጋጣሚ መሆን አልቻለም።
ዶክተር ዘላለም በጤናው ሴክተር በተለይም ለእናቶችና ህጻናት ጤና ከፍተኛ የሆነ ትኩረት ተሰጥቶ በመሰራቱ አሁን ላይ የሞት መጠኑን መቀነስ ቢቻልም፤ የውልደት መጠንን ግን መቆጣጠር ባለመቻሉ ከፍተኛ የሆነ ስራ ማከናወን ያስፈልጋል ብለዋል።
ይህንን ለማድረግ ደግሞ የተለያዩ የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎቶችን ለተጠቃሚው በማስተዋወቅ እና ንቅናቄን በመፍጠር መስራት ከማስፈለጉም በላይ እያደገና እየጨመረ የመጣውን የህዝብ ቁጥር ወደ ሥራ የሚያስገባ ፖሊሲ መቅረጽ በጣም ወሳኝና አስፈላጊ መሆኑን ይናገራሉ።
እንደ ዶክተር ዘላለም ማብራሪያ እስከ አሁን ትኩረቱ የእናቶችና ህጻናትን ሞት መቀነስ ላይ ስለነበር የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎት ሥራው የተዘነጋ መስሏል፤ እዚህ ላይ እነ ቻይናና ቬትናምን ሌሎች አገሮችም እንዴት ቢሰሩ ነው የህዝብ ቁጥራቸውም መመጠን የቻሉት የሚለውን ማየት ያስፈልጋል፤ ምናልባት እነዚህ ልምዶች ከባድ ውሳኔን የሚጠይቁ ቢሆኑም እንኳን ትኩረት አድርጎ መስራቱ ወደፊት ሊከሰት ከሚችለው ችግር እንደሚያድን ይናገራሉ።
ዶክተር ዘላለም የተለያዩ አይነት የቤተሰብ መመጠኛ ዘዴዎችን በመጠቀም የውልደት መጠንን መቀነስ ውጤቱ የሚታየው ከአስርና ሀያ ዓመታት በኋላ ቢሆንም መጀመር ያለበት ግን አሁን መሆኑን፤ በሌላ በኩል ደግሞ አሁን ላለው ሰው ሰፊ የሥራ እድል ሊፈጥሩ የተዘጋጁ ትልልቅ ፕሮግራሞችን ወደ ሥራ በማስገባት መጠቀም እንደሚያስፈልግ ያስረዳሉ።
አዲስ ዘመን ህዳር 17/2012
እፀገነት አክሊሉ