አዲስ አበባ፡- በሰው፣ በአካባቢና በእንስሳት ላይ ጉዳት የሚያደርስ ከተለያዩ ተቋማት የተሰበሰበና በአዳሚ ቱሉ ጸረ ተባይ ፋብሪካ የተመረተ 400 ቶን ዲዲቲ በመጋዘን ተከማችቶ እንደሚገኝ የኬሚካል ኢንዱስትሪ ኮርፖሬሽን አስታወቀ።
የኮርፖሬሽኑ ከፍተኛ የአካባቢ ጥበቃ ባለሙያ አቶ ምስጋናው ቀለመወርቅ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት የወባ ትንኝ ለማጥፋት በሚል በአገር ውስጥ የተመረተና
ከውጭ የገባ እንዲሁም ከተለዩ ተቋማት የተሰበሰበ 400 ቶን ዲዲቲ በመጋዘን ተከማችቶ ይገኛል። ኬሚካሉ በዓለም አቀፍ ደረጃ ጥቅም ላይ እንዳይውል በመከልከሉ በፋብሪካው መመረቱን አቁሟል። በመጋዘናችን ተከማችቶ የሚገኘውና በሌሎች ተቋማት ያለው ኬሚካል ጉዳት እንዳያደርስም ማስወገድ ይገባል።
ኬሚካሉን በአገር ወስጥ ማስወገድ አይቻልም ያሉት ባለሙያው፤ በኢትዮጵያ ያለውን ዲዲቲ ከኬሚካል አስወጋጅ ድርጅት ጋር በመጋቢት ወር 2013 ዓ.ም በውጭ አገር ለማስወገድ ጥረት እንደሚደረግ፤ ከፍተኛ ወጪም እንደሚያስወጣ ተናግረዋል።
እንደ ባለሙያው ማብራሪያ የኬሚካል ኢንዱስትሪዎች ጠቃሚ የመሆናቸውን ያህል የሚጠቀሙባቸውን ኬሚካሎች በአግባቡ ካላስወገዱ ጉዳት አላቸው። ኬሚካሉን ለማስወገድ የሚመለከታቸው አካላት በቅንጅት መስራት ይኖርባቸዋል። መንግሥትም ይህ ተጣጥሞ እንዲሄድ አቅጣጫ ማስቀመጥና ማስተባበር ይኖርበታል።
ባለሙያው አገሪቱ ከግብርና ወደ ኢንዱስት ሪያላይዜሽን ለመሸጋገር እየሰራች መሆኑን፣ ስራውን ተግባራዊ ለማድረግ ቀጣይነት ያለው ልማትን መተግበር እንደሚያስፈልግ፣ ይህን እውን ለማድረግ በማህበረሰቡ ተቀባይነት ያለው፣ ኢኮኖሚው አዋጭ የሆነ፣ በፖለቲካዊ አንድምታው ተቀባይነት ያለውና አረንጓዴ ልማትን መሰረት ያደረገ ሥራ መከናወን እንዳለበት ተናግረዋል።
ኮርፖሬሽኑ ፋብሪካዎቹ ዓለም አቀፍ መስፈርት አሟልተው እንዲሰሩ ጥረት እየተደረገ መሆኑን፣ ያረጁት በአዲስ መልክ እንዲጠገኑ፣ ከፋብሪካዎቹ የሚወጣው ጠጣር፣ ፈሳሽና አየር በአካባቢ፣ በሰውና በእንስሳት ላይ ጉዳት እንዳያደርሱ የመከላከል ስራዎች እየሰሩ መሆናቸውን ባለሙያው ተናግረዋል፡፡
ኮርፖሬሽኑ የሙገር ሲሚንቶ፣ የአዳሚ ቱሉ ጸረ ተባይ ፋብሪካ፣ የአዋሽ መልካሳ ኬሚካል ፋብሪካ፣ የባቱ የኮስቲክ ሶዳ ፋብሪካና የጎማዛፍ ልማት ፕሮጀክትን ያስተዳድራል።
አዲስ ዘመን ህዳር 17/2012
አጎናፍር ገዛኸኝ