አዲስ አበባ፦ የእንስሳት መድኃኒት ለማምረት በመቶ ሚሊዮን ብር የተገነባው ፋብሪካ በኤሌክትሪክ ችግር ምክንያት ለአራት ወራት ያለሥራ መቆሙን የብሔራዊ እንስሳት ጤና ጥበቃ ኢንስቲትዩት አስታወቀ።
የኢንስቲትዩቱ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አወል አብዱልጀባል ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት የፋብሪካው ግንባታ በ2009 ዓ.ም. ተጀምሮ ከአራት ወራት በፊት ሙሉ ለሙሉ ቢጠናቀቅም በኤሌክትሪክ ችግር ምክንያት ወደ ሥራ መግባት አልቻለም ።
ፋብሪካውን ወደ ምርት ለማስገባት ግንባታ ከፈጸመው ድርጅት ጋር የሙከራ ስራዎች ተከናውነው መረካከብ እንዳልተቻለ የገለጹት ኃላፊው፤ከግብርና ሚኒስቴር፣ ከኢንስቲትዩቱ የቦርድ ኃላፊዎችና ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት እንዲሁም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት ቢደረገም መፍትሄ አለመገኘቱን አብራርተዋል።
እንደ አቶ አወል ማብራሪያ ፋብሪካው አስራ ሁለት አይነት የእንስሳት መድሃኒት እንክብሎችን በማምረት የውጪ ምንዛሪን በማስቀረት 15 በመቶ ፍላጎትን በአገር ውስጥ ለመሸፈን በማስቻል ለግብርናው ዘርፍ ጥራቱን የጠበቀ መድኃኒት ለማቅረብ ትልቅ አቅም ያለው ቢሆንም የገጠመው የኤሌክትሪክ ችግር ወደኋላ አስቀርቶታል።
የአሮሚያ የኤሌክትሪክ አገልግሎት የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ጫላ ቦንሳ ለቅሬታው በሰጡት ምላሽ ኢንስቲትዩቱ ከአንድ ዓመት በፊት ተጨማሪ የኤሌክትሪክ ማሻሻያ ቢጠይቅም አፋጣኝ ምላሽ እንዳልተሰጠው በመጠቆም፤ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በክልል ቅርንጫፍ መሥሪያ ቤቶች አዲስ አወቃቀር በመዘርጋቱ፣ ለአዲሱ ተቋም መረጃው በቶሎ አለመድረሱና ከደረሰም በኋላ በአስቸኳይ ሥራ መጠመዳቸውን፤ ኢንስቲትዩቱ እንዲያቀርብ የተጠየቀውን ትራንስፎርመር ካቀረበና ሌሎች ሊሟሉ የሚገባቸው ቅድመ ሁኔታዎች ከተሟሉ በአንድና በሁለት ሳምንት ውስጥ ጥያቄው ምላሽ እንደሚያገኝ አስረድተዋል ።
ኢንስቲትዩቱ ከመድሃኒት ፋብሪካ ግንባታው ባሻገር ባለፉት ሰባት ዓመታት የእንስሳት በሽታ መከላከያ ክትባት አምርቶ ሲሸጥ እንደነበር የሚናገሩት ኃላፊው በዘንድሮው ሩብ ዓመት 76 ነጥብ 77 ሚሊዮን ዶዝ ክትባት በማምረት 44 ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ብር ለመሸጥ አቅዶ ከእቅዱ በላይ 103 ነጥብ 71 ሚሊየን ዶዝ በማምረት 54 ነጥብ 36 ሚሊዮን ብር ሽያጭ መፈጸሙን አብራርተዋል።
ክትባቱን በዋናነት ለክልሎች እንዲህም ለሃያ ስድስት አፍሪካ አገራት በጨረታ እንደሚያቀርብ የተናገሩት ኃላፊው፤ በሩብ ዓመቱ ለአፍሪካ አገራት ስድስት ነጥብ አምስት ሚሊየን ብር የሚያወጡ ክትባቶችን ለመሸጥ ቢያቅድም ማግኘት የተቻለው ግን 760 ሺ ብር ብቻ መሆኑን ተናግረዋል።
ሌላው ኢንስቲትዩቱ የሚያመርታቸውን 23 ዓይነት ክትባቶች ውጤታማነት በየወቅቱ ምርምር በማድረግ ከሁኔታዎች ጋር እንዲጣጣሙ ያደርጋል፤ በዘንድሮው ሩብ ዓመትም ሦስት የማሻሻያ እና ሦስት ሙሉ የክትባት ጥናት እያካሄደ እንደሚገኝ ኃላፊው ገልጸዋል።
አዲስ ዘመን ህዳር 17/2012
አጎናፍር ገዛኸኝ