አዲስ አበባ፡- የማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ አገሪቱ የደረሰችበትን የለውጥና የእድገት ደረጃ የሚመጥን ሁለንተናዊ ተቋማዊ ሪፎርም ለማካሄድ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ እንደሚገኝ አስታወቀ።
የኤጀንሲው የኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሳፊ ገመዲ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፣ ኤጀንሲው በ2012 የበጀት ዓመት ከያዛቸው ዋና ዋና እቅዶች መካከል አንዱ የተቋሙን አወቃቀር በማዘመን የሥራ አፈፃፀሙን የሚያሳድግ ሁለንተናዊ የሆነ ተቋማዊ ሪፎርም ማካሄድ ነው። ለዚህም ተቋሙ የተሰጡትን ኃላፊነቶች ከማሳካት አንፃር መሰናክል የሆኑ የተቋሙ ችግሮች ተለይተው ተግባራዊ እንቅስቃሴዎች ተጀምረዋል። የተቋሙ ሥራ የሚመራበት አዋጅ ያሉበት ክፍተቶች ከባለድርሻ አካላት ጋር ተለይተው ውይይት ተደርጎባቸዋል።
ከዚህ በተጨማሪም በበጀት ዓመቱ የመረጃ አሰባሰብ ሽፋንንና ጥራትን ለማሳደግና የተቋሙን የመረጃ አያያዝ ለማዘመን እንደሚሰራም ዳይሬክተሩ ተናግረዋል። ለዚህም ይረዳ ዘንድ በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያው ሩብ ዓመት ስልጠና መሰጠቱንና የመረጃ ተጠቃሚዎች ተሳትፎና ግንኙነት ስትራቴጂን ለመቅረፅ ውይይቶች መደረጋቸውን አመልክተዋል።
እንደ አቶ ሳፊ ገለፃ፣ ኤጀንሲው መረጃን ሰብስቦና ተንትኖ ለተጠቃሚዎች የማቅረብ እና ብሔራዊ የስታቲስቲክስ ስርዓትን የማጠናከር ኃላፊነቶች ስለተሰጡት የ2011 እቅዶቹ እነዚህን ኃላፊነቶችን ማዕከል ያደረጉ ነበሩ። በዚህም መረጃን በመሰብሰብና ለተጠቃሚዎች በማቅረብ ረገድ የሰብል ምርት ትንበያ፣ የቤተሰብ ፍጆታና ኢኮኖሚ ደህንነት እንዲሁም የእቃና የአገልግሎት ችርቻሮ ዋጋ ጥናት መረጃዎች ተሰብስበዋል።
በግብርና ስታቲስቲክስ ዘርፍ ከኤጀንሲው እቅድ ባሻገር ከሌሎች መስሪያ ቤቶች ጋር በትብብር የተከናወኑ ስራዎች ነበሩ። በበጀት ዓመቱ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴርን የመረጃ አያያዝ ስርዓትን የማዘመን ሥራ ተከናውኗል። ከመረጃ መሰብሰብ በተጨማሪ መረጃዎቹ መገናኛ ብዙኃንን ጨምሮ በሌሎች አማራጮች ለተጠቃሚዎች እንዲደርሱ ተደርጓል።
በ2011 በጀት ዓመት ኤጀንሲው መንግሥት ከአምስት ዓመታት በፊት ከዓለም ባንክ ጋር በጋራ በጀመረው የ‹‹ስታቲስቲክስን ለውጤት›› መርሐ ግብር አማካኝነት ቴክኖሎጂና የሰው ኃይልን ጨምሮ የሌሎች ግብዓቶች አጠቃቀሙን የሚያሻሽሉ ተቋማዊ የአቅም ግንባታ ተግባራትን መከናወኑንና ኤጀንሲው ከመረጃ አሰባሰብና ስርጭት አንፃር የልኅቀት ማዕከል እንዲሆን በማሰብ የስልጠና ማዕከል መገንባቱን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።
ባለፈው ዓመት በአገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች የተከሰቱ የፀጥታ ችግሮች በኤጀንሲው እቅድ አፈፃፀም ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደራቸውን፤ ብዙ ተግባራትን በአንድ ጊዜ ማከናወንንና በስራ አፈፃፀም ወቅት ሊያገጥሙ የሚችሉ ችግሮችን ቀድሞ መተንበይ መቻልን ኤጀንሲው ከ2011 በጀት ዓመት የእቅድ አፈፃፀሙ ያገኛቸው ልምዶች እንደሆኑ ዳይሬክተሩ ጠቁመው፤ ኤጀንሲው በ2011 ዓ.ም ይካሄዳል ተብሎ እቅድ ተይዞለት ለነበረውና ለተራዘመው አራተኛው የሕዝብና ቤት ቆጠራ ተግባር መጠነ ሰፊ ዝግጅት ሲያደርግ እንደነበር አስታውሰዋል።
የማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ ከ50 ዓመታት በፊት የተቋቋመ መረጃ ሰብሳቢና አሰራጭ መንግሥታዊ ተቋም ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት በመላ አገሪቱ 25 ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች አሉት። ተጠሪነቱም ለብሔራዊ ፕላን ኮሚሽን ነው።
አዲስ ዘመን ህዳር 17/2012
አንተነህ ቸሬ