አዲስ አበባ፡- ኢትዮጵያ የተሻሻለ ንጽህናን ጥራት ባለው መንገድ ለዜጎች በማዳረስ ረገድ ከዘላቂ የልማት ግቦች ርቃ እየተጓዘች መሆኗ ተገለጸ፡፡
ትናንትና በተጀመረውና ለሁለት ቀናት በሚቆየው ዓመታዊ የውሃ አቅርቦት፣ ሳኒቴሽን፣ ሃይጅን እና የውሃ ሃብት አስተዳደር የዘርፈ ብዙ ባለ ድርሻ አካላት ዓመታዊ የውይይት መድረክ ላይ የጤና ሚኒስቴር ሚንስትር ዴኤታ ዶክተር ሊያ ታደሰ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ ሜዳ ላይ መጸዳዳትን በመቀነስና አጠቃላይ የንጽህና አጠባበቅ ሽፋንን በማሳደግ ረገድ አበረታች ውጤቶችን ያስመዘገብች ቢሆንም አገልግሎቱን ጥራት ባለው መንገድ ማዳረስ ላይ ከልማት ግቦች ርቃ እየተጓዘች መሆኗን ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ ለአካል ጉዳተኝነትና ለሞት ከሚዳርጉ ሦስት ዋና ዋና ምክንያቶች መካከል የውሃ አቅርቦትና የንጽህና አጠባበቅ ችግር አንደኛው ሲሆን፤ በሌላ በኩልም ሃያ ሁለት በመቶ የሚሆኑ ከአምስት ዓመት በታች ያሉ የህጻናት ሞት መንስኤ የሆነው የተቅማጥ በሽታ የንጽህና ጉድለት መገለጫ መሆኑን ዶክተር ሊያ ጠቁመዋል ፡፡
የንጽህና አጠባበቅ ሽፋኑን በማሳደግ ረገድ ብዙ ሥራዎች በመሰራታቸው አበረታች ውጤት መመዝገቡን የጠቆሙት ሚንስትር ዴኤታዋ፤ አገልግሎቱን በጥራት በማዳረስና ቀጣይነቱን በማስጠበቅ ረገድ አሁንም ብዙ የሚቀሩ ነገሮች መኖራቸውን ጠቁመዋል፡፡
ዶክተር ሊያ ያጋጠሙ ችግሮችን ለመቅረፍና የዘላቂ ልማት ግቦችን ለማሳካት ሚንስቴር መስሪያ ቤቱ በተለይም የዘርፉ ዋነኛ ማነቆ የሆነውን ትክክለኛና ጥራት ያላቸው የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁሶች እጥረት ለመፍታት አቅርቦቱንና የገበያ ተደራሽነቱ ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ መሆኑን በተያዘው የበጀት ዓመትም በተመረጡ ሃምሳ የትራንስፎርሜሽን ወረዳዎች ቢያንስ አንድ የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁስ አቅርቦትና የገበያ ማዕከል ለመገንባት በዕቅድ መያዙን ገልጸዋል፡፡
የብሔራዊ አንድ ዋሽ መርሐ ግብርን በበላይነት የሚያስተባብረው የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጅነር ስለሺ በቀለ በበኩላቸው መርሐግብሩ በኢትዮጵያ መንግሥትና በልማት አጋሮች በውሃ አቅርቦት፣ ሳኒቴሽንና የአካባቢ ጤና አጠባበቅን ለማሻሻል ባለፉት አስር ዓመታት እየተተገበረ የሚገኝ ሲሆን፤ በመጀመሪያው ዙር ሦስት ነጥብ 91 ሚሊዮን ህዝብ በገጠርና ግማሽ ሚሊዮን የሚሆኑ በከተማ የሚኖሩ ህዝቦችን የተሻሻለ የውሃ አቅርቦት፣ ሳኒቴሽንና የአካባቢ ጤና አጠባበቅ አገልግሎት ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ጠቁመዋል፡፡
ሚኒስትሩ ጥራት ያለው የአገልግሎት ሽፋንን ከማሳደግና ከማስፋፋት አኳያ አሁንም ብዙ የሚቀሩ ሥራዎች መኖራቸውን ጠቁመው፤ ትኩረት ተሰጥቶ ካልተሰራ ሃገሪቱ ዘላቂ ልማት ግቦችን ለማሳካት የሚቸግራት መሆኑን የዘንድሮው ዓመታዊ የዘርፈ ብዙ ባለ ድርሻ አካላት ፎረም በዚህ ላይ አተኩሮ እንደሚወያይ አብራርተዋልⵆ
ውይይቱ የገጠሙ ተግዳሮቶችን ለመፍታት በሚያስችል መልኩ የሚካሄድ መሆኑን የተናገሩት ሚኒስትሩ፤ አገልግሎቱ በዝቅተኛ ደረጃ የሚገኝባቸውንና በከፍተኛ ደረጃ በድርቅና በምግብ እጥረት የሚጠቁ አካባቢዎች ላይ ትኩረት እንደሚያደርግ፤ በዘርፉ ያሉ ፈታኝ ሁኔታዎችን በመለየትና የወደፊት ስትራቴጅካዊ የመፍትሔ ዕቅዶችን በመንደፍ አገሪቱ የዘላቂ ልማት ግቦችን ለማሳካት ቅድሚያ ሰጥታ የምትሰራባቸውን ጉዳዮች የምትለይበትና አቅጣጫ የምታስቀምጥበት ይሆናል ብለዋል፡፡
የዘንድሮው ዓመታዊ የዘርፈ ብዙ ባለ ድርሻ አካላት ፎረም “ሁሉን አቀፍ የተቀናጀ፣ የተፋጠነና ጥራት ያለው የውሃ አቅርቦትና አስተዳደር ለዘላቂ ልማት ግቦች መሳካት” በሚል መሪ ቃል እንደሚካሄድ ታውቋል፡፡
አዲስ ዘመን ህዳር 17/2012
ይበል ካሳ