በሀገራችን የገጠር ከተሞች ተማሪዎች ከብቶች እየጠበቁ እንደሚያጠኑ ይታወቃል። በአንዳንድ የገጠር ከተሞች በየቤታቸው መብራት የሌላቸው ተማሪዎች በመንገድ ዳር መብራት እንደሚያጠኑም ይታወቃል። በሀገራችን የመብራት መቆራረጥ ሲያጋጥም ተማሪዎች የተለያዩ አማራጮችን በመጠቀም የቤት ሥራዎቻቸውን ይሰራሉ።
ቤተሰቦቻቸው አስፈላጊውን የትምህርት መሣሪያ ሊያሟሉላቸው ያልቻሉ አንዳንድ ተማሪዎች ከጓደኞቻቸው በመዋዋስ ወይም ሌሎች መላዎችን በማፈላለግ እየተማሩ በትምህርታቸው ብርቱ የሚሆኑበት አጋጣሚ አለ።አንዳንዴ ደግሞ ሁሉም ነገር በቤተሰቦቻቸው የተሟላላቸው ተማሪዎች በትምህርታቸው ጥሩ ውጤት ያመጣሉ ተብሎ ሲጠበቅ ሰነፍ ሆነው ይገኛሉ። መብራት ቢጠፋ መላ ማፈላለግ ውስጥ የማይገቡም ጥቂት አይደሉም።
ኤንዲቲ የተሰኘው ድረ ገጽ ሰሞኑን ይዞት የወጣው ዘገባ ደግሞ ተማሪዎች ልሥራ ካሉ ምንም አይነት ችግር እንደማያግዳቸው የሚያመለክት ነው። አነስተኛ ኮምፒዩተር ወይም ታብሌት የሌለው አንድ ብራዚላዊ ታዳጊ ተማሪ ያደረገው ግን ለሰነፍ ተማሪዎች ትምህርት ይሰጣል።
ተማሪው የቤት ሥራ እንዲሰራ በመምህሮቹ ይታዘዛል። የቤት ሥራው ግን መሰራት ያለበት በኮምፒዩተር በመታገዝ ነው። እሱ ግን ኮምፒዩተር የለውም ። ይህ ብራዚላዊ ታዳጊ ተማሪ ግን አንድ መላ ይመጣለታል፤ በቀጥታ ቦርሳውን እንደያዘ በብራዚል ሬሲይፍ ከተማ ወደሚገኝ አንድ የኤሌክትሮኒክ መደብር ያመራል። በመደብሩ የተገኘው ግን እንደማንኛውም ሰው እቃዎችን ሊገዛ ወይም እቃዎችን እና ዋጋቸውን ሊያጠና አይደለም። በመደብሩ በሚገኘው ታብሌት ኮምፒዩተር የቤት ሥራውን ለመስራት ነው። የመደብሩን ባለቤት በማስፈቀድም ታብሌቱን ተጠቅሞ የቤት ሥራውን ይሰራል።ድርጅቱ ለካ ይህን ሁሉ በቪዲዮ ይቀርጸው ኖሯል።ይህ ምስልም በኦንላይን አማካይነት በመላው ዓለም ይሰራጫል። 12 ነጥብ 5 ሚሊዮን ጊዜም ለመታየት ይበቃል።
በቪዲዮው ታዳጊው የትምህርት ቦርሳውን በትከሻው ይዞ በኤሌክትሮኒክ መደብር ውስጥ ቆሞ ታብሌት እየተጠቀመ ማስታወሻዎችን ሲወስድ ይታያል።ታዳጊው ጉልሀርም አሥር ዓመቱ ሲሆን፣ የሳንቲያጎ ነዋሪም ነው። የመደብሩ ተቀጣሪ ጉልሀርምን ከመጋበዙ በፊት የቤት ሥራዎችን ለመስራት የሞባይል ስልኩን ይጠቀም ነበር።
ባለፉት ሳምንታት በትዊተር ገጾች ብቻ ብዙዎች የተማሪውን ምስል በመጋራት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፤ አንድ ግለሰብም የታዳጊውን ጥረት በማድነቅ ሦስት ታብሌት ኮምፒዩተሮችን ሊሰጡት ወስነዋል። ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል በርካታዎቹ ጉልሀርምን የጋብዘውን የመደብሩን ተቀጣሪ አመስግነዋል፤የተወሰኑት ደግሞ ትምህርት ቤቱ ተማሪዎች የሚጠቀሙበት በቂ ኮምፒዩተር ሊኖረው ይገባ ነበር ብለዋል።ጉልሀርም በአቢሊዮ ጎመሜስ ማኑሲፓል ትምህርት ቤት የአምስተኛ ክፍል ተማሪ ሲሆን፣ትምህርቱ ለ278 ተማሪዎች 12 ታብሌቶች ብቻ እንዳሉት ዘገባው አመላክቷል።
አዲስ ዘመን ህዳር 16 ቀን 2012 ዓ.ም