የብሄራዊ ሜትሮሎጂ መረጃዎች አስቀድሞ በጠቆሙት መሰረት በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ እየጣለ ይገኛል። ዝናቡ በደረሰ ሰብል ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሊያስከትል እንደሚችል የግብርና ሚኒስቴርም የብሄራዊ ሜትሮሎጂ ኤጀንሲም በተደጋጋሚ አስታውቀዋል። አርሶ አደሩ፣ የግብርና ባለሙያዎች፣ ተማሪዎች ፣የመከላከያ ሰራዊት አባላት እና ሌሎችም ዝናቡ በሰብል ላይ ጉዳት ከማድረሱ በፊት ሰብል ለመሰብሰብ በሚደረገው ርብርብ ውስጥ እንዲሳተፉ ሲጠየቅ ቆይቷል።
መረጃዎቹን መሰረት በማድረግም በአንዳንድ አካባቢዎችም ሰብል የመሰብሰብ ስራው በተጠናከረ መልኩ እየተካሄደ ይገኛል። በቅርብ ጊዜ የወጡ የግብርና ሚኒስቴር መረጃዎች እንዳመለከቱትም የሰብሉ 40 በመቶ ተሰብስቧል። ከመረጃው መረዳት የሚቻለው አብዛኛው ሰብል አለመሰብሰቡን ነው። በመሆኑም ለሰብል ስብሰባው ትኩረት በመስጠት መስራት አሁንም የባለድርሻ አካላትንና የመላውን ህብረተሰብ ርብርብ ይጠይቃል።
እየጣለ ያለው ዝናብ በደረሱ ሰብሎች ላይ ጉዳት እንዳያደርስ የሚደረገው ርብርብ እንዳለ ሆኖ፣ ዝናቡ ለእንስሳትና ለሌሎች ቋሚ ሰብሎች መልካም አጋጣሚ መሆኑንም መረዳት ይገባል። ከጸሀይ ይልቅ ከዝናብ ይተርፋል ይባላልና በአሁኑ ወቅት የሚጥለው ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ የቱንም ያህል የከፋ ቢሆን ለእንስሳትና ለቋሚ ተክሎች ግን ትልቅ ጠቀሜታ ይኖረዋል። በእርግጥም ከዚህ ዝናብ በእጅጉ መጠቀም እንችላለን።
እንስሳት የሚጠጡት ውሃ፣ የሚግጡት ሳር እንደልብ ሊያገኙ ይችላሉ። ቋሚ ተክሎች ይበልጥ ያድጋሉ፤ ያፈራሉ። በመሆኑም ዝናቡን ለእነዚህ በሚመች መልኩ እያቆሩም ቢሆን ለመጠቀም መስራት ያስፈልጋል።
ይህ ዝናብ በተለይ ባለፈው የክረምት ወቅት ሀገራችን ዓለምን ጭምር ባስደመመ መልኩ ለተከለቻቸው በቢሊዮን ለሚቆጠሩ ችግኞች ይበልጥ መጽደቅ ትልቅ አጋጣሚ ተደርጎ መወሰድ ይኖርበታል። በሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ የደን ልማትም እንደ ሰብል ልማቱ ዝናብን መሰረት በማድረግ ነው የሚካሄደው። እየጣለ ያለው ዝናብም ለእዚህ ዝናብን መሰረት ላደረገው የደን ልማታችን ከፍተኛ ጠቄሜታ ይኖረዋል።
እንደሚታወቀው ኢትዮጵያ ባለፈው የክረምት ወቅት 4 ቢሊየን ችግኞችን ለመትከል አቅዳ አሳክታለች። የዚህ አቅድ አካል በሆነውና ሐምሌ 22 ቀን 2011 ብቻ በአንድ ጀምበር 200 ሚሊየን ችግኞችን ለመትከል አቅዳ 335 ሚሊየን ችግኞችን ተክላለች።
በዚህ የችግኝ ተከላም መላ ኢትዮጵያውያን ከህጻን እስከ አዋቂ የተሳተፉ ሲሆን፣ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰቡ እና የዓለም አቀፍ ተቋማት ሰራተኞች ጭምር ተሳትፈዋል። በአንድ ቀን 200 ሚሊየን ችግኞችን ለመትከል ታቅዶበት በነበረበው የአረንጓዴ አሻራ ቀን በተካሄደው የችግኝ ተከላም ሀገሪቱ በህንድ ተይዞ የቆየውን በአንድ ቀን ችግኞች የተተከሉበትን ክብረ ወሰን መስበር ችላለች።
እነዚህ ችግኞች እንዲጸድቁ እንክብካቤ ለማድረግ በተከላው የተሳተፉ ሁሉ ቃል መግባታቸው ይታወሳል። እንደ አካባቢ የአየር ንብረትና ደን ኮሚሽን ያሉ አንዳንድ ተቋማትም የክረምቱ ወቅት ሳይልፍ ጀምሮ ችግኞቹ የተተከሉበት ስፍራ ድረስ በመሄድ እንክብካቤ በማድረግ ቃላቸውን መጠበቅ መጀመራቸው ይታወቃል። የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትርም በአዲስ አበባ ከአንዴም ሁለቴ ችግኞችን ውሃ ሲያጠጡ ታይተዋል። በግለሰብ ደረጃም ጥረት የሚያደርጉ ስለመኖራቸው መረጃዎች ይጠቁማሉ።
እንደሚታወቀው በመኖሪያ ቤት አቅራቢያ እንዲሁም በከተሞች የተተከሉትን ችግኞች አልፎም ቢሆን ውሃ ማጠጣት ይቻል ይሆናል። ለተቀሩት ችግኞች ግን ይህን ማድረግ አይቻልም፤ አይጠበቅምም። ለእነዚህ ችግኞች ማድረግ የሚቻለው ከእንስሳት እና ከሰው ንክኪ መጠበቅ እንዲሁም ዝናብ በሚጥልበት ወቅት መንከባከብ ብቻ ነው። አሁን እየጣለ ያለውን ዝናብ ግን በሚገባ በመጠቀም ችግኞቹ እንዲጸድቁ መስራት ያስፈልጋል። ዝናቡ ለእነዚህ ችግኞች ወቅቱን ያልጠበቀ ሳይሆን የጠበቀ ነው። በዚህ ዝናብ ችግኞቹ በጋውን በጥሩ ሁኔታ መሻገር የሚችሉበትን ሁኔታ መፍጠር ይቻላል።
ህዝቡ በችግኝ ተካለው እንደተረባረበው ሁሉ ይህን መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ችግኞቹን መኮትኮት፣ አካባቢያቸውን ማጽዳትና ከእንስሳትና ሰው ንክኪ መጠበቅ ይኖርበታል። የአካባቢ አየር ንብረትና ደን ኮሚሽን ባለሙያዎች ከዚህ አኳያ ሙያዊ ድጋፍ ከማድረግ አንስቶ ህዝቡ ችግኞቹን እንዲንከባከብ በማድረግ መልካም አጋጣሚውን መጠቀም ይኖርበታል። እየጣለ ያለው ዝናብ በክረምቱ ወቅት ለተከልናቸው ችግኞች ወቅቱን ያልጠበቀ ሳይሆን ወቅቱን የጠበቀ ነው!! እንጠቅምበት!!
አዲስ ዘመን ህዳር 16/2012