አዲስ አበባ፡- የኢትዮጵያ መንግሥትና አሊባባ ግሩፕ በኤሌክትሮኒክ የታገዘ አለም አቀፍ የንግድ ማእከል ለመገንባት የመግባቢያ ሰነድ ተፈራረሙ:: ማእከሉ በኢትዮጵያ የሚገኙ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ወደቻይና እና ወደተቀረው ዓለም ድንበር ተሻጋሪ ግብይቶች ሲፈፅሙ በቴክኖሎጂ የታገዘ የሎጀስቲክ አገልግሎትና የሰለጠነ ባለሙያ የሚያገኙበት እንደሆነም ተጠቁሟል፡፡
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ጌታሁን መኩሪያና የአሊባባ ግሩፕ የወቅቱ ሊቀመንበር ኢሪክ ጂንክ ማእከሉን ለመገንባት በሚያስችሉት ሦስት የመግባቢያ ሰነዶች ላይ ትናንት በአይ.ሲ.ቲ ፓርክ ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡
የስምምነት ሰነዱ በተፈረመበት ወቅት ንግግር ያደረጉት የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ የንግድ ማእከሉ የኢትዮጵያ ዲጂታል ኢኮኖሚና ልማት ወሳኝ አካል መሆኑን ጠቁመዋል:: የሞባይል ግንኙነትን ጨምሮ የሮቦት፣የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ፣የኢንተርኔትና ስሪ ዲ ፕሪንቲንግ የዲጂታል ቴክኖሎጂ በልዩ ልዩ መስኮች እያደገ መምጣቱንም ጠቅሰው፤ በእነዚህ ቴክኖሎጂዎች አማካኝነት ሰዎች በስራ፣ በአኗኗር፣ ከሰዎች ጋር ባላቸው ግንኙነትና በሚያካሂዷቸው የንግድ ልውውጦች ትላልቅ ለውጦችን እያስመዘገቡ መምጣታቸውን ገልፀዋል፡፡
በታሪክ ሂደት ውስጥ ቴክኖሎጂ ለአስተማማኝ የኢኮኖሚ እድገት ብሎም ለሀገራትና ህዝቦቻቸው ብልፅግና ትልቅ ሃይል እንደነበርም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስታውሰው፤ፈጣን የቴክኖሎጂ ለውጥ ለሀገራትና ህዝቦቻቸው የራሱ ፈተና እንዳለውም ጠቅሰዋል፡፡ይህ በመሆኑም የቴክኖሎጂ ሽግግር ጊዜ እንደሚፈልግ አስታውቀዋል፡፡
ዓለም በአሁኑ ወቅት በሰፊ የለውጥ ሂደት ውስጥና የአራተኛው የኢንዱስትሪ አብዮት እየተዋወቀ በሚገኝበት ጊዜ ውስጥ መሆኗንም የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ያለትክክለኛ ፖሊሲ በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት ከዚህ የቴክኖሎጂ ዘመን በስፋት ተጠቃሚ ሊሆኑ እንደማይችሉ አስገንዝበዋል፡፡
በኤሌክትሮኒክ ለታገዘ ዓለም አቀፍ የንግድ መድረክ ሰፊ እድል እንዳለ ተናግረው፤በግሉ ሴክተር የሚመራ እንደመሆኑ መጠን በኢትዮጵያ የሚገኙ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ወደቻይና እና ወደተቀረው ዓለም ድንበር ተሻጋሪ ግብይቶች ሲፈፅሙ በቴክኖሎጂ የታገዘ የሎጀስቲክ አገልግሎትና የሰለጠነ ባለሙያ ለማግኘት እድል እንደሚፈጥርላቸውም አስታውቀዋል፡፡ ማእከሉ በዓለም አቀፍ ንግድ ማርሽ ቀያሪ ሊሆን እንደሚችልና ኢትዮጵያም በቀጣዮቹ አሥር ዓመታት የአፍሪካን ኢኮኖሚ ከሚመሩ አምስት ሀገራት ተርታ ለመመደብ የያዘችውን እቅድ የሚደግፍ መሆኑንም ገልፀዋል፡፡
እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለጻ፤ ማእከሉ የውጭ ሀገራት ደምበኞች በዲጂታል ኤሌክትሮኒክ ንግድ ምርቶችን፣ዳታዎችንና ገንዘቦችን በቀጥታ ለማግኘት ያስችላቸዋል፡፡ ከጉምሩክ ጋር በተያያዘ ያሉ የቁጥጥር ሂደቶችንም ያቀላል፡፡
የአሊባባ ግሩፕ መስራችና ባለቤት ጃክ ማ በበኩላቸው፤በኤሌክትሮኒክ የታገዘ ዓለም አቀፍ የንግድ ማእከል ግንባታ በኢትዮጵያ የዲጂታል ኢኮኖሚ ጅማሬ እንደሆነ ጠቅሰው፣ በቀጣይ አፍሪካውያን በኤሌክትሮኒክ ንግድ ከአውሮፓውያን፣አሜሪካውያንና ቻይናውያን እኩል ተፎካካሪ ለመሆን እንደሚያስችላቸው ገልጸዋል፡፡
በዚህ የዲጂታል ኢኮኖሚ አማካኝነት በአነስተኛ ቢዘነስ የተሰማሩ ኢትዮጵያውያን ወጣቶችና ስራ ፈጣሪዎች ዓለም አቀፍ ንግድ ለማካሄድ እንደሚረዳቸውም ገልጸዋል፡፡የኢትዮጵያ ስኬት ወጣት ኢትዮጵያውያንን ብቻ ሳይሆን የተቀሩ የአፍሪካ ሀገራትንም ከዲጂታል ኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንዲሆኑ እንደሚያነሳሳቸውም ተናግረዋል፡፡
በስራ ፈጠራና ኢኖቬሽን ዙሪያ ብዙ መሰራት እንዳለበትም ጃክ ማ ጠቁመው፤በዚህ ጉዳይ ላይ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ውይይት እንዳደረጉና በቀጣዩ ዓመት ወጣት የስራ ፈጠራ ባለቤቶችን ለማበረታታት የፈጠራ ስራ ሽልማት ፕሮግራም በኢትዮጵያ እንደሚካሄድ አስታውቀዋል፡፡
በአፍሪካ የስራ ፈጠራን ለመደገፍ የጃክ ማ ፋውንዴሽን ከ10 እስከ 100 ሺ የአሜሪካ ዶላር ድጋፍ እንደሚያደርግ ጠቅሰው፣ በአፍሪካ የስራ ፈጠራ፣የኢንተርኔት ልማትና ዲጂታል ኢኮኖሚ የበለጠ እንዲኖር ያልተቋረጠ ድጋፍ እንደሚያደርግም ተናግረዋል፡፡
ስምምነቱ ኢትዮጵያን ከአፍሪካ በኤሌክትሮኒክ የታገዘ ዓለም አቀፍ የንግድ መገናኛ ማእከል ያላት ሁለተኛዋ ሀገር የሚያደርጋት ሲሆን፣ከዚህ በፊት ሩዋንዳ ከአሊባባ ግሩፕ ጋር በመሆን ማእከሉን መክፈቷ ይታወሳል፡፡በአሊባባና በኢትዮጵያ መንግሥት መካከል የተመሰረተው አዲሱ አጋርነት በእስያ ቻይናና ማሌዢያ፣ በአውሮፓ ቤልጂየም እንዲሁም በአፍሪካ ሩዋንዳ ተመስርተው ስኬታማ ከሆኑት ማእከላት በመነሳት መሆኑን ከመረጃዎች ማወቅ ተችሏል፡፡
አዲስ ዘመን ህዳር 16/2012
አስናቀ ፀጋዬ