የአካባቢው እናቶች የተማሪዎቹ ሁኔታ ክፉኛ ረብሿቸዋል:: ምግብ አሻፈረኝ ማለታቸው እና እርስበእርስ መቀያየማቸውም ሀዘኔታ ፈጥሮባቸዋል:: እናቶቹ በእዚህ ሁኔታ ተረብሽው አላቆሙም፤ ተንበርክከው እያለቀሱ ተማሪዎቹ እንዲመገቡ እና እንዲታረቁም እንደለመኗቸው የወሎ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር አባተ ጌታሁን በዩኒቨርሲቲው በቅርቡ ለአንድ ቀን ያጋጠመውን አለመረጋጋት ለመፍታት በእናቶች በኩል የተከናወ ነውን ተግባር አስመልክቶ ይገልጻሉ::
የወሎ ዩኒቨርሲቲ አካባቢ እናቶች የኦሮሚያ ተወላጅ ተማሪዎች ከአማራዎቹ ጋር እስኪታረቁና ምግብም እስኪበሉ ድረስ ከተንበረከኩበት እንዳልተነሱ የሚናገሩት ፕሬዚዳንቱ፣ ይህን ያስተዋሉት ተማሪዎችም በእናት የሚጨክን ልጅ የለምና እርስ በእርስ መተቃቀፋቸውን እና መመገብ መጀመራቸውንም ይናገራሉ::
‹‹እንዲህ አይነቱ ባህላዊ እሴት ዛሬ እየተሸረሸረ ቢሆንም፤አጠንክረን ብንሰራበት ውጤታማ መሆን እንደሚቻል ያመለክታል ::›› ሲሉ የጠቀሱት ዶክተር አባተ፤‹‹በዩኒቨርሲቲያችን የተፈጠረው አለመረጋጋት ወደመረጋጋት እንዲመለስ ለማድረግ እናቶች በአገር በቀል እውቀት ተጠቅመው የፈፀሙት ተግባር ትልቅ ፋይዳ ነበረው::›› ይላሉ::
በዩኒቨርሲቲው በሰላም ዙሪያ በርካታ ስራዎችንና ጥናታዊ ፅሑፎች መስራታቸውንም ጠቅሰው፣ በዚህም ሰላም ሦስት ዋና ዋና ነገሮች እንዳሉት ማስተዋላቸውን ይገልጻሉ:: ‹‹ሰላም በዛፍ ይመሰላል::
ዛፍ ስር፣ግንድ፣ቅርንጫፍና ቅጠል አለው::የግጭት ትልቁ ችግር በሆነው ላይ የዩኒቨርሲቲ መምህርና ተመራማሪ ነን የምንል አካላት አጥብቀን ልንሰራ ይገባል::››ሲሉም ያስገነዝባሉ::
እንደ ዶክተር አባተ ገለፃ፤በዋናው የችግሩ ስር ላይ ምሁራን አጠንክረው ሊሰሩ ይገባል፤ቀጥሎም በግንዱ ላይ የሚታይ አውራ ችግር አለ፤ይህ ችግር ከስልጣን ጋር ተያይዞ አግላይነት አሊያም አቃፊነት በተለይ በብሄር፣በኃይማኖት፣በጎጥና በመሳሰለው ላይ ተንተርሶ የሚፈፀመው ነው::በዚህም ላይ እየተሰራ አይደለም::
የእነዚህ ችግሮች የመጨረሻ ወጤት መሰዳደብ፣ መወነጃጀልና መገዳደል ነው:: ይህን ለማስቀረት የችግሩ ስር በሆነው ጉዳይ ላይ ምሁሩ ጥናት አካሂዶ ለመንግሥት ማቅረብ ይኖርበታል::ባለሀብቱም ለጥናት አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረግ ይጠበቅበታል::በዚህ አይነት መልኩ ከተሰራ ሰላም ለማስፈን እምብዛም አይቸግርም:: በዚህ በኩል በወሎ ዩኒቨርሲቲ ሙከራዎች እየተደረጉ ናቸው::
የመደወላቡ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር አቡበከር ከድር ‹‹ወሎ ውስጥ ለተጎዳ የኦሮሞ ተማሪ ባሌ ውስጥ ያለው የአማራ ተማሪ ተጠያቂ መሆን የለበትም›› ይላሉ:: የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ታዳጊ ወጣቶች መሆናቸውን ጠቅሰው፣የሚገጥማቸው የትኛውም አይነት የፖለቲካም ሆነ የማህበረሰብ ትምህርት በጠላትነት ሊያፈራርጃቸው የሚችል መሆን እንደሌለበትም ያስገነዝባሉ::
እንደ እሳቸው ገለጻ፤ተማሪዎችን ከስር ጀምሮ በቀናው መንገድ ኮትኩቶ ማሳደግ እንጂ ቂምና ቁርሾ ሊያተርፍ የሚችል ትርክትን መጋት አይገባም::አንድ አማራ ነኝ ወይም ኦሮሞ ነኝ የሚል ግለሰብ ላጠፋው ጥፋት እርሱ የበቀለበትን ማህበረሰብ ሁሉ ተጠያቂ ማድረግም ተገቢ አይደለም:: ይህን አበክሮ ለተማሪዎች ማስገንዘብ ይገባል::
ተከታታይነት ባለው መልኩ ውይይቶች፣ ሴሚናሮች፣ አስተማሪ የሆኑ ዝግጅቶች እንዲካሄዱ በማድረግ ችግሮችን መቀነስ እንደሚቻል ጠቅሰው፣በክረምቱ ወቅት ቢቻል የአንድ ወር ጊዜ ተወስዶ አስተማሪ ውይይቶችን በየዓመቱ ማድረግ መልካም መሆኑን ይጠቁማሉ::
‹‹ይህ ካልሆነ ግን ሁኔታው አስፈሪ ነው:: ተማሪዎችን ሰብስቦ ማናገር ወደማይቻልበት ደረጃ ደርሰናል::››
ያሉት ዶክተር አቡበከር፣የ18 እና የሃያ ዓመት ተማሪ በታሪክና በፖለቲካ ሳይንሱ የዶክትሬት ዲግሪ ካለው ምሁር በበለጠ ሁኔታ ሞጋች እየሆነ መምጣቱን ይገልጻሉ ::ይህን በተሻለና በዘመነ አመለካከት ለመተካት ተከታታይነት ያለው ሥራ እንደሚጠይቅ ይገልጻሉ::
የዶክተር አባተን ሀሳብ በማጠናከርም ምሁራን የተለያዩ አመለካከቶችን የሚቀይሩ ጥናታዊ ፅሁፎችን በማቅረብ ለተማሪዎች የማንቂያ ስራ ሊሰሩ ይገባል ይላሉ:: ዩኒቨርሲቲዎች የሚገኙባቸው ዞኖችና ህብረተሰብም ለዚህ ስራ መቃናት የየበኩላቸውን ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው ያመለክታሉ::
እንደ ዶክተር አቡበከር ገለጻ፤ተማሪው በአብዛኛው ሬድዮ አሊያም ቴሌቪዥን የሚመለከተው የስፖርት ፕሮግራም ሲኖር ነው፤ብዙ ጊዜውን የሚያጠፋው በማህበራዊ ትስስር ገፆች ላይ ሲሆን፣እነዚህ ደግሞ ከአዎንታዊ ጎናቸው አሉታዊ ጎናቸው ይበዛል:: በእነዚህ ገፆች ላይ ምሁራን ጥናታዊ ስራዎችን ቢሰሩ መልካም ነው:: በዩኒቨርሲቲዎች ቅጥር ግቢ ውስጥም ከተማሪዎ ቻቸው ጋር መደበኛ ባልሆነ መልኩ ስለ አገሪቱ በግልፅ የቤተሰብን ያህል ቀርበው ቢነጋገሩና የተሻለውን እንዲጨብጡ ቢያደርጉ ነጥሎ ማቀፍና መግፋት አይከሰትም::
የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የዩኒቨርሲቲዎቹ ተማሪዎች እንዲወያዩ በማድረግ ለማግባባት በተከናወነ ስራ ውጤት መገኘቱን በመጥ ቀስ፣ተማሪዎች ወደትምህርት ገበታቸው እየተመለሱ ስለመሆናቸው ለአዲስ ዘመን መግለጹ ይታወሳል:: ተጠርጣሪዎችንም በቁጥጥር ስር የማዋሉ ተግባር መቀጠሉን አስታውቋል::
አዲስ ዘመን ህዳር 16/2012
አስቴር ኤልያስ