ከጥቂት ዓመታት በፊት ከጅማ አካባቢ መጥታ ኑሮዋን በአዲስ አበባ ያደረገችው ወጣት ፋሪዳ መጋል ከቁጠባ ጋር ከተዋወቀች ቆይታለች፡፡ትውውቋም ጅማ በነበረችበት ወቅት ሲሆን፣ ያንን የቁጠባ ባህሏን ኑሮን ለማሸነፍና ወላጆቿን ለመርዳት ስትል በመጣችበት አዲስ አበባም ቀጥላለች፡፡
በአሁኑ ወቅትም በአንድ የህንፃ ግንባታ ውስጥ በለሳኝነት እየሰራች ያለችው ወጣት ፋሪዳ፣በየወሩ እስከ ስድስት ሺህ ብር ገቢ ታገኛለች፡፡ከወጪዎቿ ከሚተርፋት ገንዘብ ላይ ሁለት ሺህ ያህሉንም ትቆጥባለች፡፡ የኑሮ ውድነቱ ቢሻሻልና የሸቀጦች ዋጋ ቢቀንስ አሁን ከምትቆጥበው በላይ ገንዘብ የመቆጠብ ፍላጎት አላት::ልክ እንደ እርሷ ሁሉ ሌሎችም ቢቆጥቡ ተጠቃሚ ሊሆኑ እንደሚችሉም ትመክራለች::
ወጣት ማቲዎስ መኩሪያ በአዲስ አበባ ከተማ የአንድ የህንፃ ግንባታ ድርጅት የጉልበት ሰራተኛ ነው::ከሚያገኘው ገንዘብ በመቆጠብ ተጠቃሚ ለመሆን ከፍተኛ ፍላጎት አለው::በወር የሚያገኘው ገቢ ግን ከእለት ጉርሱ እና ለትራንስፖርት ከሚያወጣው ከፍተኛ ወጪ የሚያልፍ አለመሆኑ እንዲሁም እየጨመረ የመጣው የኑሮ ውድነት ይህን ፍላጎቱን እንዳያሟላ እንዳደረገው ይናገራል::በወር የሚያገኘው ገቢ ከወጪው ጋር ተመጣጣኝ ከሆነና ከዚህ የሚተርፍ ገንዘብ ካገኘ መቆጠብ እንደሚጀመር ይጠቁማል::
በፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት የማይክሮ ኢኮኖሚ ዘርፍ ተመራማሪ አቶ አህመድ በሽር እንደሚሉት፤ግለሰቦች የሚቆጥቡት ገንዘብ እያጡ መምጣታቸው በቁጠባ ላይ ከፍተኛ ክፍተት ፈጥሯል::ይህም ግለሰቦች የሚያገኙት ገንዘብ ቁጠባን በትልቁ ሊወስን እንደሚችል ያሳያል::ግለሰቦች የሚያገኙትን ገንዘብ የዋጋ ንረቱ የሚወስደው ከሆነና በኑሮ ውድነት ምክንያት ገንዘቡ አቅሙን እያጣ ከመጣ በፊት ሲቆጥቡ የነበሩትን ገንዘብ አሁን መቆጠብ አይችሉም::
‹‹የዋጋ ንረቱ እየጨመረ በሄደ ቁጥር ግለሰቦች ገንዘብ በባንክ ከማስቀመጥ ይልቅ በንብረት መያዝ ምርጫቸው ያደርጋሉ::››ያሉት አቶ መሀመድ፣ ይህም ወደባንኮች የሚገባውን የገንዘብ መጠን እንደሚቀንሰው ያስረዳሉ::
አቶ መሀመድ፣‹‹መንግሥት በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ላይ የማይክሮ ኢኮኖሚ ማስተካከያ በማድረግ የዋጋ ንረቱን መቀነስ ይኖርበታል::››ሲሉ በመጥቀስ፤ የማይክሮ ኢኮኖሚ የዋጋ ንረትን ማስተካከል ጠቀሜታው በርካታ መሆኑንም ያመለክታሉ:: በዋናነት መንግሥት ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያውን በፍጥነት ተግባራዊ ካደረገና ማሻሻያው በታለመው ልክ ከተሰራበት ቁጠባው እያጋጠመው ያለውን ችግር መፍታት እንደሚቻል ይገልጻሉ::
እንደ እርሳቸው ገለጻ፤ገንዘብ በባንክ ሲቆጠብ ገንዘቡ ወደ አንድ ማእከል ስለሚመጣ ባንኮች የበለጠ አዋጭ የሆኑ ፕሮጀክቶችን በመገምገም ለግለሰቦች ይሰጣሉ:: ይሁንና በግለሰብ ደረጃ ገንዘቡ ሥራ ላይ ሲውል ለሀገር ከፍተኛ ጥቅም ሊያስገኙ በሚችሉ ፕሮጀክቶች ላይ ላይሆን ይችላል:: ይህም የዋጋ ንረት በቁጠባ ላይ ትልቅ አሉታዊ ተፅእኖ እንዳለው የሚያሳይና ሊስተካከል የሚገባው ጉዳይ መሆኑን የሚጠቁም ነው::
አዲስ ዘመን ህዳር 16/2012
አስናቀ ፀጋዬ