አዲስ አበባ:- የአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን በበጀት ዓመቱ ከ400 ሚሊዮን ብር በላይ በመመደብ በመዲናዋ እስከ 515 ኪሎ ሜትር የሚደርስ የአስፓልት መንገድን ጨምሮ የተለያየ መንገድ አይነት እየተጠገነ መሆኑን አስታወቀ::
በመንገዶች ባለሥልጣን የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ጥዑማይ ወልደገብርኤል በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደገለፁት፤በበጀት ዓመቱ ከሚጠገኑት መንገዶች መካከል 110 ኪሎ ሜትር የአስፋልት፣100 ኪሎ ሜትር የጠጠር፣225 ኪሎ ሜትር የተፋሰስ መስመሮች፣50 ኪሎ ሜትር የጌጠኛ ድንጋይ መንገዶችና 30 ኪሎ ሜትር የእግረኛ መንገዶች ናቸው::
የጥገና ሥራ ከሚከናወንባቸው የእግረኛ መንገዶች መካከል ከስድስት ኪሎ እስከ ሽሮ ሜዳ፣ከሂልተን ሆቴል እስከ ታላቁ ቤተ መንግሥት፣ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እስከ ብሔራዊ ቤተ መንግሥት፣ከቃሊቲ ቶታል እስከ ገላን ኮንዶሚኒየም፣ ከኮካ ኮላ እስከ መሳለሚያ እና ሌሎችም በርካታ አካባቢዎች እንደሚገኙበት ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል::
እንደ አቶ ጥዑማይ ገለፃ፤ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ የመንገድ ጥገና ሥራዎችን ውጤታማ ለማድረግና በአጭር ጊዜ ለማጠናቀቅ እየተንቀሳቀሰ ነው::የትራፊክ መጨናቀቅ ሳይኖር ለመጠገን በማሰብም በተለያዩ አካባቢዎች በምሽትና በሌሊት የጥገና ሥራው በመከናወን ላይ ይገኛል::አሽከርካሪዎች፣ እግረኞችና ትራፊክ ተቆጣጣሪዎች ትብብር እንዲያደርጉም ጥሪ ቀርቦላቸዋል::
የአስፓልት መንገድ ጥገናው በተለይ በክረምት ምክንያት የተጎዱ መንገዶችንና ቀደም ሲልም ችግር የነበረባቸውን መንገዶች በመጠገን የትራፊክ ፍሰቱ የተሳለጠ ለማድረግ፣ የትራፊክ መጨናነቁንና በሰዎችና በተሽከርካሪዎች ላይ የሚደርሱ አደጋዎችን ለመቀነስ አስተዋፅዖ እንዳለው አቶ ጥዑማይ አክለው ተናግረዋል:: ካለፈው ሐምሌ ወር ጀምሮ እስከ ጥቅምት መገባደጃም ድረስ 16 ኪሎ ሜትር የአስፓልት መንገድ መጠገኑንም ገልፀዋል::
አዲስ ዘመን ህዳር 16/2012
ኃይለማርያም ወንድሙ