አዲስ አበባ፡- ወጣቶች ጥያቄዎቻቸው ምላሽ እንዲያገኙና አገርም ሰላም እንድትሆን ተናበው መስራት እንዳለባቸው የኦሮሚያና የአማራ ባለሀብቶች አሳሰቡ።
የኦሮሞና የአማራ ባለሀብቶች በሂልተን ሆቴል በጋራ ባዘጋጁት መድረክ ላይ አስተባባሪዋ ወይዘሮ ፍሬአለም ሽባባው እንደገለፁት ወጣቶች የእኩልነት፣ የነፃነትና ፍትሀዊ የሀብት ክፍፍልን የተመለከቱ ጥያቄዎችን ሲያቀርቡ በሰላማዊ መልኩ መሆን አለበት።
ከዚህ ውጪ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ሁላችንንም ችግር ውስጥ ይከተናል ያሉት ወይዘሮ ፍሬአለም አንዱ ችግር ሌላ ችግር እየወለደ ሕዝብንና አገርን አደጋ ላይ ይጥላል ብለዋል። በመሆኑም ወጣቶች ለሕዝብና ለአገር ሰላም ሲባል ማንኛውም ጥያቄዎች በሰላማዊ መንገድ ማቅረብና መደማመጥ እንዳለባቸው አሳስበዋል።
በቅርቡ በአገራችን በተከሰቱ ግጭቶች የሰው ሕይወት መጥፋቱን፣ ንብረት መውደሙንና ሕዝቡ መጨነቁን የገለጹት ወይዘሮ ፍሬአለም ከዚህ ችግር ለመውጣት ዋነኛው መፍትሄ ወጣቶች ማንኛውንም ጥያቄ ሲያቀርቡ በሰላማዊ መንገድ ተከትለው መሆን ነው ብለዋል።
የራሱ እኩልነት፣ ነፃነት፣ ዴሞክራሲ መብት እንዲከበርለት የሚፈልግ ሰው የሌላውንም መብት ማክበር እንዳለበት አመልክተው፣ ለዘላቂ የጋራ ሰላም ወጣቶች እርስ በእርስ በመከባበርና በመደማመጥ ችግሮቻቸው እንዲፈቱ ማድረግ አለባቸው ብለዋል።
ቀደም ሲል «አገራችንን ወደ ሰላም ለመመለስ» በሚል ሀሳብ የኦሮሚያና የአማራ የባለሀብቶች በመሰባሰብ በጋራ ባዘጋጁት መድረክ ላይ በአገሪቱ ወቅታዊ የሰላም ጉዳይ ላይ የኦሮሞና የአማራ ባለሀብቶችና አክቲቪስቶች በጋራ እንደሚሰሩ ስምምነት ላይ መድረሳቸው የሚታወስ ነው።
አዲስ ዘመን ህዳር 15/2012
ጌትነት ምህረቴ