አዲስ አበባ፡- የብልጽግና ፓርቲ ሰው ተኮር በመሆኑ ከጨፍላቂነት ይልቅ አቃፊነቱ የጎላ መሆኑን የኢሕአዴግ ሊቀ መንበር ዶክተር አብይ አህመድ ገለፁ።
የአዴፓ 39ኛ ዓመት የምሥረታ በዓልን አስመልክቶ ትናንት በአዲስ አበባ በተዘጋጀ መድረክ ላይ ዶክተር አብይ እንደተናገሩት፣ የብልጽግና ፓርቲ ሰው ተኮር በመሆኑ ከአግላይነትና ከጨፍላቂነት የተላቀቀና አካታች ነው።
ምሁራንንና አርብቶ አደርን ያላካተተ ፓርቲ ጨፍላቂ ሳይባል አካታቹ ጨፍላቂ ሊባል የሚቻልበት አመንክዮ አለመኖሩን የተናገሩት ዶክተር አብይ የሲዳማ ሕዝብ ራሱን ለማስተዳደር እንዲወስን የፈቀደ ፓርቲ ጨፍላቂ ሊሆን እንደማይችልም አመልክተዋል። አዲሱ ፓርቲ ጨፍላቂ ቢሆን ኖሮ ለሕዝበ ውሳኔ ዕድል ሊሰጥ አይችልም ነበር ብለዋል።
በዚህ ወቅት በተጨባጭ ችግር ቢያጋጥምም ኢትዮጵያን ሊያፈርስ የሚችል ኃይል ግን ተፈጥሮ እንደማያውቅና ወደፊትም ሊፈጠር እንደማይችል የተናሩት ዶ/ር አብይ በፍቅርና ይቅርታ በጋራ ለጋራ ሀገር ግንባታ መቆም ችግሮችን ለመፍታት እንደሚያግዝ አመላክተዋል።
የኢሕአዴግ ውሕደትና የአዴፓ 39ኛ ዓመት የምሥረታ በዓል ለአዴፓ ትርጉሙ ከፍ ያለ መሆኑን የገለጹት የአዴፓ ሊቀ መንበር አቶ ደመቀ መኮንን በበኩላቸው «በመጣንበት መንገድ ያጎደልናቸውን ሞልተን የተሻለች ሀገር ለመፍጠር አዲሱ የብልጽግና ፓርቲ መልካም አጋጣሚ ይዞ መጥቷል» ብለዋል።
«አሁን የምንፈጥረው ፓርቲ በሦስት ትውልድ ቅብብሎሽ የመጣ ነው፤ ስለዚህ ቀጣዩ ትውልድ ያለፉ መልካም ሥራዎችን እንደወረት ወስዶ አገርን በጋራ ለመለወጥ ይሠራል» ያሉት አቶ ደመቀ «ሁል ጊዜም ከመልካሙ ነገር እንነሳለን እንጂ አፍርሰን ከባዶ አንገነባም፤ ይህ የትም አያደርሰንም» ማለታቸውን የዘገበው የአማራ መገናኛ ብዙኃን ድርጅት ነው።
አዲስ ዘመን ህዳር 15/2012
በጋዜጣው ሪፖርተር