አዲስ አበባ።- ሰላሟ የተረጋገጠ፣ አንድነቷ የተጠበቀና የበለጸገች ሙሉ አገር እውን ለማድረግ በአዲስ አበባ ያለውን ሰላማዊ እንቅስቃሴ ወደሌሎች ክልሎች ማስፋት እንደሚገባ የአዲስ አበባ ወጣቶች ማህበር ጠቆመ። ማህበሩ ለከተማዋ ወጣቶች ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ብሎም ለከተማዋ ሁለንተናዊ ሰላምና እድገት እየሰራ መሆኑን ገልጿል።
የማህበሩ ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት ወጣት ተከስተ አያሌው ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገረው፤ አገራዊ ለውጡን ተከትሎ እዚህም እዚያም የሚታዩ አለመረጋጋቶች ቢኖሩም አዲስ አበባ ዛሬም የተረጋጋና ሰላማዊ እንቅስቃሴ ያላት ከተማ ናት።
ይሁን እንጂ የአዲስ አበባ ሰላማዊ እንቅስቃሴ ብቻውን ትርጉም ስለሌለው ሰላሟ የተረጋገጠ፣ አንድነቷ የተጠበቀና የበለጸገች ሙሉ አገርን እውን ማድረግ ካስፈለገ በአዲስ አበባ ያለው ሰላማዊ እንቅስቃሴ ወደሌሎች አካባቢዎች እንዲሰፋ መስራት ይገባል።
ወጣት ተከስተ እንደሚለው፤ ሌሎች አካባቢዎች እየተረበሹ አዲስ አበባ ብቻዋን ሰላም ብትሆን ትርጉም የለውም። ስለዚህ ሙሉ የሆነች አገርን የምንሻ ከሆነ አዲስ አበባ ላይ ያለው ነገር ወደሌሎች ቦታዎች ሊሰፋና በመላው ኢትዮጵያ መድረስ አለበት። የዚህ ሥራም የአንድና ሁለት አካላት ሳይሆን የሁሉም ኃላፊነት መሆኑን ተገንዝቦ መስራት ያስፈልጋል። የአዲስ አበባ ወጣቶች ማህበር ችግሮች ከመከሰታቸው በፊት ወጣቶችን
ከእንደዚህ ዓይነት ነገሮች ወጣቱን እንዴት መታደግ ይገባል በሚለው ላይ በትኩረት እየሰራ ይገኛል።
ኅብረተሰቡ እንዴት በአንድ ላይ ተቻችሎ መኖር አለበት የሚለውን ከማሳየት፤ የከተማዋን ሰላም ከማረጋገጥ፤ የወጣቱን ጥያቄ ከመመለስና የከተማዋን ልማት ከማፋጠን አኳያ ከማህበሩ በላይ መንግሥት/የከተማ አስተዳደሩ ኃላፊነት እንዳለበት የሚናገረው ወጣት ተከስተ፤ የመገናኛ ብዙኃንም ተደራሽነታቸውን ተጠቅመው ሕዝቡ የኋላ ታሪኩን ለትምህርት በመተው አሁን ያለውን ሂደት እንዴት ማስቀጠል እንችላለን የሚለውን አቅጣጫ በማሳየት ላይ አተኩረው መስራት እንዳለባቸው ጠቁሟል።
እንደ ወጣት ተከስተ ማብራሪያ፤ በዋነኝነት ወጣቱ ያልሆነ ነገር ውስጥ እየገባ ያለው በማህበራዊ ሚዲያ በሚሰራጩ የውሸት ወሬዎች ነው። እነዚህን የውሸት ወሬዎች ከመቀበሉ በፊት እንዴት አድርገን ማጣራት መቻል አለብን፤ እውነታውስ የትኛው ነው የሚለው ላይ ተከታታይና ዘላቂነት ያለው ሥራ መስራት ያስፈልጋል። ለዚህም መንግሥትም ሆነ መገናኛ ብዙኃን ብሎም የሲቪክ ማህበራት ኃላፊነታቸውን መወጣት አለባቸው።
ማህበራቸውም ከወጣቶች ጋር የተለያዩ መድረኮችን በመፍጠር የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮችን እያከናወነና የወጣቶቹን ስሜትም እያዳመጠ እየሰራ እንደሚገኝ ወጣት ተከስተ ጠቁሟል።
በየመድረኮቹ ከወጣቶቹ ከሚነሱ ጥያቄዎች መካከልም፣ ‹‹ሌሎች ክልሎች ላይ እየተፈጠሩ ያሉ ችግሮች ወደ አዲስ አበባ ላለመምጣታቸው ዋስትናችን ምንድን ነው፤›› የሚሉት ተጠቃሽ ናቸው ያለው ወጣት ተከስተ ይህ ደግሞ ሙሉ አገርን ከመፍጠር አኳያ የአዲስ አበባ ብቻ ሰላማዊ መሆን ዋስትና ስለማይሆን ሌሎች አካባቢዎችም መሰል ሰላማዊ እንቅስቃሴ እንዲኖራቸው መስራት ይገባል ብሏል።
ለዚህ ደግሞ ችግሮች ሲነሱ ወደወጣቱ ከመጠቆም ይልቅ ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍሎች በትኩረት ሊሰሩ፤ ይህች አገር እንዳታድግና እንዳትለወጥ የሚፈልጉና ከወጣቱ ጀርባም ያሉ ኃይሎችም እጃቸውን ሊሰበስቡ ይገባል ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል።
አዲስ ዘመን ህዳር 15/2012
ወንድወሰን ሽመልስ