ኅዳር 10/2012 ዓ.ም የተካሄደውን የሲዳማ በክልልነት የመደራጀት ወይም በነባሩ ክልል የመቀጠል ሕዝበ ውሳኔ ውጤት ከትናንት በስቲያ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ይፋ አድርጓል። ይፋ በተደረገው ውጤት መሠረት በሕዝበ ውሳኔው ድምጽ ከሰጠው ሕዝብ 98 ነጥብ 51 በመቶ ሲዳማ ክልል ሆኖ እንዲደራጅ መርጧል። ይህም ሲዳማ ራሱን ችሎ ክልል ለማቋቋም የሚያስችል ውጤት ነው።
ውጤቱ ይፋ መደረጉን ተከትሎ የሲዳማ ሕዝብ ደስታውን በመግለጽ ላይ ይገኛል። ምንም እንኳ የዞኑ ኮማንድ ፖስት የሲዳማ ዞን ከሚያዘጋጀው የደስታ መግለጫ መርሃ ግብር ውጪ ደስታ መግለጽ የተከለከለ መሆኑን ቀደም ብሎ ያሳወቀ ቢሆንም ሲዳማዎች ደስታቸውን መቆጣጠር አልቻሉም። እንደ ተለመደው “ቄጤላ” በተሰኘው የሲዳማ ባህላዊ ጭፈራ ባይገልጹ እንኳ በተለያዩ ሁኔታዎች ደስታቸውን በመግለጽ ላይ ይገኛሉ።
በሸበዲኖ ወረዳ የአቤላ ሊዳ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ቦጋለ ቦንጃ የሲዳማን ክልል መሆን እጅግ ሲመኙ መቆየታቸውን ይናገራሉ። የራስን ዕድል በራስ ለመወሰን ሕዝበ ውሳኔ ሲዘጋጅም ምኞታቸውን እውን ለማድረግ ሻፌታን መርጠዋል። በተለይም ሲዳማ ሕጋዊና ሰላማዊ በሆነ መንገድ ክልል ለመሆን መብቃቱን በሕይወት እያሉ ማየታቸው እጅግ እንዳስደሰታቸው የሚናገሩት አቶ ቦጋለ የሕዝበ ውሳኔው ውጤት ለሳቸው የተለየ ትርጉም እንዳለው ተናግረዋል።
በተለይም የሲዳማ ስም ሊጠፋ መቃረቡ ሲያስቆጫቸው እንደነበር የሚናገሩት አቶ ቦጋለ፤ ሲዳማ በአጼ ኃይሌሥላሴ ዘመን ጠቅላይ ግዛት ነበር፤ በደርግ ዘመን ደግሞ ክፍለ ሀገር የነበረ ቢሆንም የብሔር ብሔረሰቦችን ራስን በራስ የማስተዳደርና የብሔሮች ማንነት እውቅና የሰጠው ሕገ መንግሥት ሥራ ላይ በዋለበት በኢህአዴግ ዘመን ግን በደቡብ ብሔሮችና ብሔረሰቦች ክልል ውስጥ እንዲገባ በመደረጉ ሲዳማ የሚለው ስም እየጠፋ መምጣቱን ያብራራሉ። የሲዳማን ክልል መሆንን አጥብቀው ሲሹ የነበሩትም ይህን ስም እንዲቆይ ስለሚፈልጉ እንደሆነ ያብራራሉ።
እንደ አቶ ቦጋለ ማብራሪያ ሲዳማ በክልልነት እንዲደራጅ ብዙ ዋጋ ከፍለዋል። የሲዳማን ስም ለማጥፋት መንግሥት የወሰነውን ውሳኔ በተለያዩ ጊዜያት ሲቃወሙ ቆይተዋል። መንግሥት ላይ ሲደረጉ የነበሩ ጫናዎችንም በመሪነት በማንቀሳቀስ ሲሳተፉ ነበር። የመንግሥትን እርምጃ በግልጽ በመቃወማቸውና የመንግሥትን ሃሳብ ለማስቀየር ጫና ለመፍጠር ሕዝብ በማስተባበራቸውም ብዙ በደሎች ደርሶባቸዋል። የእነዚያ ትግሎች ውጤት ዛሬ ሲዳማ በክልል እንዲደራጅ በማስቻሉ ደስተኛ ናቸው።
በሀዋሳ ከተማ የመናኸሪያ ክፍለ ከተማ ነዋሪው አቶ አምላክረዳው አስናቀም በተመሳሳይ ሲዳማ በክልልነት ለመደራጀት የሚያስችለው ከፍተኛ ድምጽ በማግኘቱ ደስተኛ መሆናቸውን ተናግረዋል። የሕዝበ ውሳኔው ውጤት በርካቶች ዋጋ የከፈሉለትና፤ የብዙ ውጣ ውረዶች መቋጫ ነው ብለዋል።
ከዚህ ቀደም መንግሥት ሕዝበ ውሳኔ ለማዘጋጀት ፈቃደኝነቱን ሳይገልጽ በመቆየቱ ምክንያት የሲዳማ ሕዝብ በራሱ ክልል ሊያውጅ ዝግጅት አድርጎ እንደነበር የሚያነሱት አቶ አምላክረዳው፤ በዚያ መልኩ ሲዳማ ክልል አውጆ ቢሆን መዘዙ ብዙ ሊሆን እንደሚችል አብራርተዋል። አሁን ግን ሕጋዊና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ የመንግሥት አሠራርን ተከትሎ ሲዳማ ክልል ለመሆን የሚያስችለውን ድምጽ ማግኘቱ ትርጉሙ ላቅ ያለ መሆኑን ገልጸዋል።
«የሲዳማ ክልል በኢትዮጵያ ታሪክ በሕዝበ ውሳኔ በክልልነት የተደራጀ የመጀመሪያ ክልል ይሆናል» የሚሉት አቶ አምላክረዳው፤ ይህም የሲዳማ ሕዝብ በሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ መንገድ ያሳካው መሆኑ የሲዳማን ዴሞክራሲያዊነትና ትልቅነት አመላካች ነው ብለዋል።
በሸበዲኖ ወረዳ አቤላ ሊዳ ቀበሌ ነዋሪው አቶ ከፈለኝ ካያሞ በበኩላቸው የሲዳማ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን ጥያቄ 130 ዓመታት ገደማ ሲንከባለል የቆየ ነው። ይህ ጥያቄ በዘመናቸው ምላሽ አግኝቶ በማየታቸው እጅግ ደስተኛ መሆናቸውን ያነሳሉ። የዚህ ትውልድ አካል በመሆናቸው ኩራት እንደሚሰማቸው ይናገራሉ።
የሲዳማ በክልልነት መደራጀት ለሲዳማ ብቻ ሳይሆን በሲዳማ ውስጥ ለሚኖሩት ሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች ጥቅም አለው የሚሉት አቶ ከፈለኝ፤ ሲዳማ ከተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች ጋር መኖር የጀመረው ደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦች ክልል ከመፈጠሩ በፊት ጀምሮ መሆኑን በመግለጽ ሲዳማ ከደቡብ ክልል ተለይቶ የራሱን ክልል ማደራጀቱ ሲዳማ ከብሔሮች ጋር በሚኖረው መስተጋብር ላይ የሚኖረው አሉታዊ ጫና እንደማይኖር ገልጸዋል።
አቶ ከፈለኝ እንደሚሉት ሲዳማ ከሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች ጋር በተለያዩ መንገዶች ተሳስሯል። ትስስሩም አብሮ መቀጠሉ የሚያጠራጥር አይደለም። ሲዳማ ክልል መሆን በሲዳማና በሌሎች ብሔሮች መካከል ያለውን መተማመን የሚያጎለብት ነው።
የሲዳማ አርነት ንቅናቄ ሊቀመንበር በበኩላቸው እሳቸው እንደግለሰብ ፓርቲያቸውም እንደ ፓርቲ ሲዳማ በሕጋዊ መንገድ ክልል ለመሆን በሚያስችል ደረጃ ላይ በመድረሱ ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸዋል። ለሲዳማ እና በሲዳማ ለሚኖሩ ሌሎች ብሔር ብሔረሰቦችም እንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የሲዳማ ሕዝበ ውሳኔው ውጤት ለዘመናት ሲደረግ የነበረው የሲዳማ ሕዝብ በክልልነት የመደራጀት ጥያቄ የተቋጨበት ነው ያሉት አቶ ዱካሌ፤ በቀጣይ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ልማትን ለማረጋገጥ የሚደረገው እልህ አስጨራሽ ትግል የሚጀመርበት ነው ብለዋል።
አዲስ ዘመን ህዳር 15/2012
መላኩ ኤሮሴ