ኢትዮጵያችን ድንቅ ምድር ናት:: የድንቅነቷ መነሻ ደግሞ ሕዝቧና አኗኗሩ ከዚህም ውስጥ የሕዝቦቿ ሥነ- ቃልም ነው:: የዛሬ ነገሬ ማጠንጠኛም እርሱ ነው:: እንደሚታወቀው ሥነ-ቃል ከትውልድ ወደትውልድ በአፍ የሚተላለፍ ሀብት ነው:: በአፍ ይተላለፍ እንጂ፤ አይዛነፍም አይዛባምም፤ ያድጋል እንጂ አይቋረጥም::
እንደ ኢትዮጵያ ዓይነት በሐውርታዊ (ህብረ-ብሔራዊ) የሆነች ሀገር ደግሞ በዚህ ሥነ-ቃል አጀብ የምትታወቅ የፋፋች፣ የደረጀችና ይህም የማይነጥፍባት ምድር ናት::
ሥነ-ቃሎቻችን ረዣዥም ከሆኑ ኤፒካዊና ገድል መሰል ከሆኑ ትረካዎች እስከ ሐረግ ዘለላ የሚደርሱ አጫጭር ተረትና ምሳሌዎች ድረስ የሚሄድ፣ በአፈ ታሪክ፣ በእንካ ሰላንቲያ፣ በእንቆቅልሽ፣ በእረኛ መዝሙር፣ በልጆች ጨዋታዎች፣ የሠርግ ጨዋታዎችና ጭፈራዎች የበለፀገ ነው:: ስለዚህ ክንውኑ ባለበት በዚያ ሥነ-ቃሉም አለ::
ቀደም ሲል ላነሳው እንደሞከርኩት፣ የወላይታውን ሰምተን ወደትግሬው፣ እሱን ሰምተን ሳንጨርስ ወደ ኦሮሞው፣ ወደአማራው፣ ወደ ዘይሴው፣ ወደሲዳማው፣ ወደኮንታው፣ ወደዳውሮው፣ ወደሶማሌው፣ ወደ በርታው፣ ወደካፋው፣ እና ስማቸውን ወዳልጠራኋቸው ወደ…ወደው ሁሉ ስንሄድ የምንሰማቸው ሥነ-ቃሎች አስደማሚዎች ናቸው::
እስቲ ከየዘውጉ አንዳንድ እየዘገንን እንጠቃቅሳቸውና ዘናም ዘራፍም እንበልባቸው:: አፍ ዘርም አለውና ሲዘራ በደረሰበት ይበቅላል ስር ይይዛል:: በተለይ ኩታ ገጠም በሆኑ አካባቢዎች የሚያድጉ ልጆች በአጎራባች ሥነ-ቃሎች የዳበረ ኪነጥበባዊ እሴት ያዳብራሉ:: ለምሳሌ፤ ኮተቤ አካባቢ ወይም ሰላሌ ፍቼ የሚያድጉ ልጆች በአማርኛ ተርተው በኦሮምኛ ረገዳ ይጨፍራሉ፤ ወይ የተገላቢጦሽ በአማርኛ እስክስታ መትተው በኦሮምኛ ተረት ያስጠነቅቃሉ:: ስለዚህ ስንደማመር ሲያምርብን፤ ገጽታችን ብቻ ሳይሆን ልባችን፤ አፋችን ብቻ ሳይሆን አእምሯችን ይበለፅጋል::
እስቲ ወደደቡብ ልውሰዳችሁና ከወላይታ ወንድሞቻችን ተረትና ምሳሌዎች ጋር ላጋባችሁ:: ወላይታ፡- ምን ይላል በተረትና ምሳሌው::
«ሰይጣን፣ ቂጣውን ከመሬት እንካ ብሎ ወተቱን ከሰማይ ላምጣ ይላል::»
በዚህ ተረት እና ምሳሌ ውስጥ የተመሳሰሉት ሰውና ሰይጣን በቂጣውና በወተቱ የተመሰለው ጥያቄና መልስ ነው:: አንዳንድ ሰው ከባዱን ነገር ፊትህ ያቀርብና ቀላሉና አክብዶ ይነግርሃል:: ሻይውን አቅርቦ ስኳሩን፤ ሥጋው ሰጥቶ ቢላዋውን ይከለክልህና ወይ አትጠጣው ወይ አትበላው፤ በርቀት እያየህ ይስቅብሃል:: የአንዳንድ ሰዎች ግንኙነት፣ በስጋት ታጥሮ በፍርሃት የሚፈታ ነው፤ የሚሆንብህ:: ያኔ ነው፤ ሰይጣን በሰው ፈንታ ሆነ፤ ወይስ ሰው በሰይጣን ፈንታ የምትለው::
ከወላይታ፣ አንድ ሌላ ልጨምርላችሁ:: «ፈጣሪ፣ ለዶሮ፣ ላያፈጥበት ቀይ ዓይን፣ ለውሻ ላይስቅበት፣ ነጭ ጥርስ ሰጠው::» እንዲህ ማለት ለትልቅ ስፍራ ትልቅ አጥፊ መመደብ ወይም በተገላቢጦሽ፣ ምንም የማይችልን ሰው የማይገባውን ስፍራ በመስጠት የማይገባ ሥራን መስራት ማለት ነው:: አንዳንድ ሰዎች የተሰጣቸውን ስፍራ ሳይወክሉና ሳያክሉ በመቅረታቸው ቀልለው ሲዋረዱ ወይም ሲሳለቁባቸው አይተናል:: ልክ እንደዚሁ ያልተሳቀበት ነጭ ጥርስ ለስፍራው ያልተገባ ልብስን ያክላል::
ወደ ሲዳማ ልውሰዳችሁና ትንሽ ደግሞ እንነጋገር:: ሲዳማ፣ እንዲህ ይላል፤ «የሚያስቀምጣት የሚያስመልሳትን እንዴት አደርሽ አለቻት» ይላሉ:: የባሰባት የተሻለ ችውን አጽናናቻት እንደማለት ነው::
ብዙ የተጎዳችው ሰዎች በመትረፏ የተገረሙባት ሴት ትንሽ ወለም ያላትን ወይ ድንገት ያስመለሳትን ሰው ከጠየቀቻት ሁለት ብልሃት አለው:: አንድም፣ የራሷን ህመም መርሳት ፈልጋለች፤ አለዚያም ማረሳሳት ፈልጋለች ማለት ነው:: ሕይወት በዚህ አስቂኝ ጥልፍልፍ ውስጥ ነው፤ የምታሳልፈው:: በሌላ አባባል አንዳንድ ድካማቸው ከሰው ድካም፤ እጦታቸው ከሰው እጦት፣ መከራቸው ከሰው መከራ የባሰባቸው ሰዎች ያነሰ ችግር ያለባቸውን አግንነው ሲናገሩ እንዲህም ይባላል::
ሲዳማ፣ እንዲህም ይላል፤ «ወፍ በሰማይ ብትበር ተመልሳ ወደመሬት መምጣቷ አይቀርም::» እንዲህም ሲሉ የሰውም ሆነ የፍጥረታት ማረፊያ መሬት መሆኑን ለማሳየት ብቻ አይደለም:: ሰዎች በኑሯው ምንም ያህል ቢደላቸው፣ በሥልጣን ማማ ላይ በምንም ያህል ከፍታ፣ ቢወጡ መውረድ፣ ቢቀመጡ መነሳትና በዚያው አለመቅረት፤ እንዳለ የሄደ መመለሱና የወጣ ማሽቆልቆሉ ያለ ነው፤ ለማለት ነው:: ሥልጣንም ሥራን እንጂ ሰውን ሆኖ አይቀርም:: ሰው አላፊ ጠፊና ተረሺ ነው::
በምድር ላይ ታላላቅ የሚባሉ ደራሲያን፣ የጦር ጄኔራሎች፣ ሰዓሊያን፣ አትሌቶች፣ ሰባኪያን፣ ወዘተ…መጥተው ሄደዋል:: ተደንቀው ዝናቸው ገንኖ አልቀረም ወርደዋል፤ ከስረዋል፤ ተረስተዋል፤ ረግበዋል:: ሕይወትም በዚህነት የተሞላች ነች፤ ማለት ነው:: ዳቦ ሆድን እንጂ አእምሮን አይሞላምና ተረትና ምሳሌዎቻችን ረዥሙን አጭር፤ ዝርዝሩን ምጥን አድርገው፣ ያቀርቡልናል::
እነዚህን መሰል ቃላዊ ሥነ-ጽሑፎች በውስጣቸው ያጨቋቸው እውነቶች በአለፍ ገደም የሚተዉ አይደሉም:: የሕይወት አካል ሆነው ይኖራሉ፤ ይዳብራሉ፤ ያዳብራሉ፤ ያድጋሉም፤ እንጂ::
ኦሮሞ ወገኖቻችን ደግሞ ከተረትና ምሳሌዎቻቸው ፈገግ በሚያደርገው ልጀምርላችሁ::
«ሱሪ አውሶ አትቀመጥበት አለ፤ አሉ::»
አንዳንድ ሰው የሚያደርገውን አድርጎ፤ ያደረገላቸውን ሰዎች በሰው ፊት ማሳቀቅ የሚወድ አለ:: ልክ መኪና አውሶ ነዳጅ አትስጥ እንደማለት ያለ፤ ብዕር አውሶ ቀለምን አትጨርስ የሚል አንድምታ ያለው ንግግር ከገልቱ ዕቃ አዋሾች የሚያጋጥም ሁነት ነው:: ይሄኔ ነው፤ ያበደርሽኝን ሽሮ በላሁት፤ ያዋስኩሽን ወርቅ እንዳትረሺው ማለት:: የሰው ልጅ ሰውን ያህል ነገር ለክፉ ቀን እንደሚደራረስ ይረሳና ሲያልፍ ለሚረሳ ሲቆይ ለሚሻግት እህል ራሱን በሰጪነት ይቆልላል:: እናቴ ለሰው እንጀራ ስትሰጥ ላንተ ብዬ አልጋገርኩትም፤ ደግሞ ለሞተ እህል ትላለች::
እውነት ነው፤ እንጀራው ከጤፍነት ወደዱቄትነት ሲሄድ ከኑሮ ዕድሜው ላይ ቀንሷል፤ ከዱቄትነት ወደ እንጀራነት ሲሄድ ግን አንድም፣ ወደ ሆድ መቃብር ደጅ ደርሷል፤ አለዚያም ባይበላ ወደ ትቢያነት ሊጣል ተዘጋጅቷል፤ ማለት ይቻላል:: በሌላ አባባል፤ ካልበሉት ሊሻግት፤ ካልተጓረሱት ሊበሰብስ ደጅ ላይ ነው፤ ማለት ነው:: ስለዚህ የሞተ እንጀራ ማለት ካልተበላ ያበቃለት ማለትም ነው :: (ቪቫ የእኔ እናት፤ አመሰግናለሁ!!– በጥልቀት ሳይማሩ ሕይወትን በውሉ የሚያካፍሉ እናቶች የተባረኩ ናቸው)
እና «ሱሪ አውሶ አትቀመጥበት» ማለት፣ እንጀራ አጉርሶ አትዋጠው ማለትም ነው:: ክፉ አዋሽ ሰው እንዲህ ነው!! (ወንዙን አላልኩም አደራ!!)
ከአእላፍ ተረቶቻቸው ደግሞ ጥቂቱን ልጭለፍላችሁና፤ እንዲህም ይላሉ:: «ለእናት ኃይለ ቃል መመለስ ራስን መርገም ነው::» አንዳንድ ሰዎች፤ አንዱን ሲናገሩ ለሌላው መልእክት ማስተላለፋቸውን ይዘነጋሉ፤ ወይም ሆን ብለው መልእክት በማድረስ ሊተናኮሉ ያስባሉ:: በሁለቱም በኩል ካስተዋልነው የደፈርነው የማይደፈርን ነገር ነው::
እናት በመሠረቱ ልጅ ምን ቢያጠፋ ትዕግስቷ ወደር የለውም፤ ይሁንናም እናትን በኃይለ-ቃል መናገር በኢትዮጵያ ባህል ውሃን ሽቅብ ማፍሰስ ነው፤ ተብሎ ይታሰባል:: ከዚህ ሌላም፤ ለልጅ አሳዛኝ ዕጣ እንዲገጥመው ምክንያት ስለሚሆን (ወይም ይሆናል ተብሎ ስለሚታመን) እናትን መንካት ቤትን ማፍረስና የሕግና የሞራል ልዕልና በቤት ውስጥ ማጣትንና ከሁሉም በላይ የልጅን ዋልጌነት (ጋጠ-ወጥነት ) ስለሚያሳይ ነው፤ ተረቱ የተተረተው:: የእናት ክብር በአባት ይገለጻል፤ መደፈርም በአባት አያያዝ ይወሰናልና::
ለምሳሌ ያህል አንድ የቦረና ኦሮሞ ባል (አባ መና) ሚስቱን ቢመታ እና ሚስት ወደ ሽማግሌዎች ሄዳ ሸምግሉኝ ብላ ብትናገር፤ ጉዳዩን የያዙ አያንቱዎች፤
ይችን ሴት ወይ ሚስትህን ለምን መታሃት አይደለም የሚሉት:: «ይህችን የቦረና እናት ለምን እጅህን አሳረፍክባት?» ብለው ነው የሚጠይቁት:: ሴት ልጅ እናት ስትሆን የቀደመ ማንነቷ በአገር እናትነት ነው፤ የሚለወጠው:: ስለዚህ ነው እናት የምትከበረው:: ስለዚህ ነው፤ ልጅ እናቱን ሲዘልፍ ከተሰማ አባቱን አቃለለ፤ ቤተሰቡን አዋረደ ተብሎ የሚታሰበው:: ስለዚህ ቅጣቱ ከበድ ያለ ነው:: ያረገዘች፣ ያማጠች፣ የወለደችና በኋላም ጡቷን አጥብታ፣ በጀርባዋ አዝላ ተሸክማ ያሳደገችን እናት፣ ሲቻል መሸከም እንጂ ማዋረድ ያስረግማል ለማለት ነው:: ሀገርም እንደዚያው ናት፤ በአስደሰተችን ጊዜ ብቻ ሳይሆን በችግሯም ጊዜ ልንቆምላትና ላንተዋት ይገባል::
እስቲ ደግሞ ወደ ትግራይ ዘመዶቻችን ዘንድ ጎራ እንበል:: በትግርኛ፣ «መሳሙን ወድዳ፤ ፂሙን ጠልታ» ይላሉ:: ሰው ከወደደ ጉድለትንም ትቶ፣ ስህተትን አርሞ፣ ድክመትን ተቀብሎ እንጂ ንጹህ እስኪሆን፤ ፍጽምና ያለው ሰው እስኪሆን መጠበቅ አይገባም:: ማንም ቢሆን ሰው ነውና ከስህተት አይጠራም::
ወደ ሁለተኛው የትግርኛ ተረት ስናልፍ ደግሞ፣ «ዙሪያውን ከማንጓበብ አንገቱን መያዝ» ይላሉ:: የተጀመረውን ንግግር ዋነኛ ሃሳብ ማንሳት ትቶ ዙሪያው የሚዞር ሰው ነገር ያራዝማል እንጂ መፍትሄ አያመጣም ማለታቸው ነው::
በዚህ አገባብ ብዙው የሀገራችን ችግር ተመሳሳይ ነው:: ሁላችንም ስለጨለማው ድቅድቅነት፣ ስለመከራው ኃያልነትና ስለማያልቀው ድካማችን ማውራትና በእርሱም ላይ ስለገጠሙን አሰቃቂ ልምዶች እናወራለን:: ስለችግሩ መፍትሔ የምንሰነዝረው ውጤታማ ሃሳብ ግን የለንም:: ስለዚህ ችግራችን ላይ እየዳከርን ነው:: ለዘመናት ወደኋላ ተመልሰን፣ ስለደረሰው በደል፣ እያወራን እናላዝናለን፤ ምዕት ዓመት የኋሊት ተጉዘን በደል ፈጻሚዎች መልስ በማይሰጡበት ሁኔታ ስለአስከፊነታቸው እንናገራለን:: በዚህም ተበደሉ የምንላቸውን ወገኖች ሆድ በማንጫጫት አዲስ ለቅሶ እናስቀምጥ ይሆናል እንጂ፤ ዛሬያቸውን አናሳምርላቸውም:: በእነርሱ ኀዘን የምንጠቀመው እኩይ ሰዎች ብቻ እንጂ፣ ብዙኃኑ የተበደሉ ወገኖች የልጅ ልጅ ልጆች አይደሉም:: አንዳንዱም የተረጋገጠ በደል ሳይኖር በፈጠራ ትርክት ነው፤ የወገን ልብ የሚያቆስለው:: ቢኖርም ለዚህ ዘመን ላፈይድ ነው፤ ጊዜና ጉልበት የሚያባክነው::
መከራና ምሬት መለያየትን ያባብስ ይሆናል እንጂ፤ ለአንድነት የሚጠቅመው አንዳችም ፋይዳ የለውም:: አሜሪካውያን ነጮች፣ ከቀይ ሕንዶች ጋር አሜሪካውያን ነጮች ከጥቁሮች ጋር መልካም ያለፈ ጊዜ አልነበራቸውም:: ይሁንናም ያለፈውን ጠባሳ እያከኩ አሜሪካ አሜሪካ እንዳትሆን ጉድጓድ አይቆፍሩም፤ ከነበደላቸው በደሉን መዝግበው ለታሪክ በመተው ዛሬን እየኖሩ ለነገ መልካምነት ይተጋሉ እንጂ:: እነዚህን የመልካምነት ብቻ ሳይሆን የክፉ ጊዜ መሪዎቻቸውን ጀግናዎቹና ታላላቆቹ አባቶቻችን ይላሉ እንጂ፣ «ባሪያ አሳዳሪዎቹ»፣ «ጥቁር ጠሎቹ»፣ «ቀይ ሕንድ አሳዳጆቹ» ጨቋኝ ገዢዎቻችን እያሉ አያላዝኑም:: ዛሬ እንደ ልቡ የሚንጎራደድባትን ሀገር ባልሰለጠነ ዘመን፤ ልባቸውን አሰልጥነው ሀገራቸውን ለማሰልጠን የጣሩና የጋሩ ድንቅ አባቶችን «አረመኔና ጡት-ቆራጭ» እያደረጉ በመሳል «ወዮ-ወዮ!» ማለት የሚያስደስታቸው ዘመን የሞተባቸው ሰዎች ግን አሉን፤ በአሳዛኝ መልኩ::
እኒህን መሰል ሰዎች ሲያወሩ ወደነጥቡ አይመጡም፤ ሲናገሩ ዙሪያውን ይዞራሉ እንጂ እምብርቱ ላይ አይመጡም፤ አላማቸው ጥላቻን መዝራት እንጂ ፍቅርን መነስነስና ሀገር መለወጥ አይደለም:: በግርግሩና በሽብሩ የሚያገኙትን ትርፍ ያስባሉ እንጂ፤ የከሰሱት አካል ተነስቶ እንደማይሟገታቸው ያውቃሉ::
ተረቶቻችን ህብረትን ሰባኪ፤ አንድነትን ዓላሚ፣ ሥነምግባርን ኮትኳች፣ ፍቅርን ዘሪ፤ ሰው መሆንን አድናቂ ነው፤ መሆን ያለባቸው:: ቀጥሎ ያሉትን ተረቶች ያገኘሁት ደግሞ ከሃዲያ ብሔረሰብ ነው:: ሐዲያዎች «የተባበረ በትር ከግንድ ይበረታል» ይላሉ:: በትር እያንዳንዱ ለብቻው ሲቆም በቀላሉ ሊሰበርና ሊሰነጠር እንደሚችል ያውቃሉ:: በአንድነት ሲታሰር ግን ከውበቱ ብርታቱ ያይላል:: ሀገርና ሕዝብም እንዲሁ ነው:: ሰው ሲተባበር ለጠላት መግቢያ በር ይከለክላል፤ ኃይለኛ ነኝ ያለ ወራሪ ይመከታልና ህብረት ይመረጣል::
ከከምባታ ደግሞ አንድ ተረት ላክልላችሁ፤ ከምባታዎች እዚህ ከሐዲያዎችና ሃላባዎች ጋር ኩታ ገጠም መልክዓ-ምድራዊ አቀማመጥ ያላቸው፣ በደቡብ ክልል ውስጥ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ናቸው:: በአንደኛው ተረትና ምሳሌያቸው ላይ ሲተርቱ፤ «የማያድግ ልጅ፣ ወደ ኋላ ይድሃል» ይላሉ:: እንዲህ ሲሉ መራመድ ያልለመደ ልጅ በደረቱ እንኳን ቢሳብ ወደፊት እንጂ ወደኋላ አይሳብም፤ ቢድህም ወደፊት ወዳየው ነገር እንጂ ወደኋላ አይደለም:: ልጅ ወደኋላ ከዳኸ ችግር አምጪ ነው፤ ተብሎ ይታሰባል::
ልክ እንደዚሁ የኋላ ነገር እያነሳ፣ ወቀሳ የሚያበዛ ሰው ወደፊት ለመራመድ እንቅፋት ይፈጥራል፤ ባለትዳርም ቢሆን ለትዳሩ ስምረት ሳንካ ይፈጥራል:: ወታደርም ከሆነ የጦሩን ክንድ ይከፋፍላል፤ ሀገረ መንግሥት በመምራትም ላይ የሚሳተፍ ከሆነ ምድሪቱን የዕንባ እንጂ የሳቅ ምድር አያደርጋትም:: ስለዚህ ትዳርም፣ ድልም ሳቅም እርም ይሆናሉ:: ስለዚህ ስለዱሮ በማውራት ነገን አናበላሸው ለማለት ያግዛል::
አማርኛ ታዲያ በብልሃት ከእነዚህ ሁሉ ወገኖቹ ቋንቋዎች ድምጽም፣ ቃልም፣ ትርጉምም፣ አገባብም እየወሰደና ቃላዊ ሀብታቸውን እየተዋሰ የጋራ መግባቢያቸው በመሆን ለሲዳማው ህልም መፍቻ፣ ለሐዲያው ራእይ መሰነቂያ፣ ለኦሮሞው ግብ መምቻ፣ ለወላይትኛው ስንቅ መክተቻ፣ ለትግርኛው ማስታኮቻ በመሆን ራሱ በልጽጎ ሌሎችንም እያሳመረና እያዳመረ በመጓዝ ላይ ነው:: ኢትዮጵያን እንደሀገረ መንግሥት የሚመራ አካል የአማራ ብቻ ያልሆነውንን ይህን ቋንቋ የሥራና የአዋጅ እንዲሁም የትምህርት መሣሪያ በማድረግ ይጠቀምበታል::
በነገራችን ላይ ከላይ ከላይ ሲታይ፣ ለግብጻውያን ምንም ጥቅም የማይሰጠው የሚመስለውን፣ የአማርኛ ቋንቋ የሚያጠኑ ግብጻውያን በካይሮ ዩኒቨርሲቲ አማርኛን ከማስተማራቸውም ሌላ በካይሮ ሰዓት አቆጣጠር በየዕለቱ ከምሽቱ 2፡30 ጀምሮ የሚተላለፍ የአማርኛ ፕሮግራም ስርጭት ላለፉት 50 ዓመታት አላቸው:: ልብ በሉ፣ ግብጽና መንግሥቷ የእኛ ኢትዮጵያውያን ጉዳይ በፍቅር ስለሚያንሰፈስፋቸው ሳይሆን የዓባይ ጉዳይ ስለሚገዳቸው አማርኛን በደንብ እያጠኑትና በአማርኛ የፈለጉትን መልዕክት ወደሀገር ቤት እያስተላለፉበት ነው:: ስለዚህ ለሚወዱት ብቻ ሳይሆን የሚጠሉትንም ለማስጠላት ቋንቋ ይለመዳል:: የእነርሱ እንደተጠበቀ ሆኖ እኛ ግን በመዋዋስ ለማደግ፣ በመደመር ለመበልፀግ እንማማር፤ እንዋዋስ::
እንዲህ ባለ መልክ ውሰታችንን ለማድመቅና አብሮነታችንን ለማድነቅ ተረት እንዋዋሳለን:: እናንተም እንደተለመደው፣ እየተዋዋሳችሁ ቆዩኝ!!
መልካም የመዋዋስና የመደጋገፍ ሳምንት ይሁንላችሁ!!
አዲስ ዘመን ኅዳር 13/2012
በአገልጋይ ዮናታን አክሊሉ