አዲስ አበባ፡- የራሳቸውን ጥቅም በማስቀደም ቡናን ከገዙበት ዋጋ በታች በመሸጥ የኢትዮጵያ ቡና በዓለም አቀፍ ገበያ ዋጋው እንዲያሽቆለቁል እያደረጉ ያሉ አካላት ሊታገዱ መሆኑን ባላስልጣኑ አስታወቀ።
የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተርና የዘርፉ ኃላፊ አቶ ሻፊ ዑመር በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ የኢትዮጵያ ቡና ላለፉት አምስት ዓመታት በዓለም አቀፍ ገበያ ያለው ዋጋ እንዲያሽቆለቁል ካደረጉት አበይት ምክንያቶች መካከል፤ ጥቅማቸውን ወደ አገር ውስጥ በሚያስገቡት ምርት ለማካካስ ብለው ቡናን በርካሽ ዋጋ ለዓለም አቀፍ ገበያ የሚያቀርቡ አካላት ዋነኞቹ ናቸው። ችግሩን ለመፍታት በዚህ ህገ ወጥ ሥራ ውስጥ እየተሳተፉ ያሉ ቡና ላኪዎች እስከ መታገድ የሚያደርስ እርምጃ ይወሰድባቸዋል።
እንደ አቶ ሻፊ ገለጻ፤ የአገር ውስጥ የቡና ዋጋ ከፍ ቢልም በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለው ዋጋ ግን እየቀነሰ ይገኛል። የኢትዮጵያ ቡና ዓለም አቀፍ የቡና ዋጋ ማሽቆልቆሉ የግብይት ሥርዓቱ ላይ ችግር ፈጥሯል። ቡናን ከገዙበት ዋጋ በታች የሚሸጡ ህገ ወጥ ላኪዎች መበራከታቸው፤ የቡና ኮንሮባንድ መኖሩ፤ በቡና አቅርቦት ላይ ቡናን ወደ ውጭ በመላክ ‹‹ዶላር እናገኛለን የሚል እምነት›› አለመኖርና የአገር ውስጥ ፍላጎትና አቅርቦት አለመጣጣም የኢትዮጵያን ቡና ዋጋ በዓለም አቀፍ ገበያ እንዲቀንስ አድርጎታል። ይህንን ተከትሎም በዓለም አቀፍ ገበያ ዋጋውን ከፍ ማድረግ አልተቻለም።
ችግሩን ለመፍታት ከቡና ባለ ድርሻ አካላት ጋር በአጭርና ረጅም ጊዜ እቅድ በማውጣት ወደ ሥራ ተገብቷል ያሉት ኃላፊው፤ አርሶ አደሮች፣ አቅራቢዎችና ላኪዎችን ያካተተ ምክክር እየተደረገ መሆኑን ገልፀዋል።
በዋናነትም ወደ አገር ውስጥ በሚያስገቡት ምርት ለመጠቀም ቡናን በርካሽ ዋጋ የሚሸጡ፤ በአጠቃላይ በእንዲህ አይነቱ ተግባር ላይ የሚሳተፉ አካላትን ለመቆጣጠር በተዘጋጀው መመሪያ መሠረት እርምጃ እንደሚወሰድ፤ የጸረ ኮንትሮባድ ኮሚቴዎችን በማደራጀት ህገወጥ መጋዘኖችን የመለየት ሥራ እየተከናወነ መሆኑንና፤ ለችግሩ ዘላቂ መፍትሄ የአስተሳሰብ ለውጥ ማምጣት እንዲቻል ግንዛቤ የመስጠት ሥራ እየተከናወነ መሆኑን አብራርተዋል።
እንደ እርሳቸው ማብራሪያ፤ ግብይቱን ዘመናዊና ቀልጣፋ በማድረግ፤ ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥና የዓለም አቀፍ ዋጋው እየወረደ መምጣቱ በአገር ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ እንዳይፈጥር ባለሥልጣኑ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል።
የኢትዮጵያ ቡና ላኪዎች ማኅበር ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ግዛት ወርቁ በበኩላቸው፤ የዘንድሮውን በጀት ዓመት ጨምሮ ላለፉት አምስት ዓመታት የሚላከው የቡና መጠን ቢጨምርም፤ ከኢትዮጵያ ቡና የሚገዙ አገራት አማካይ የዋጋ መጠኑ በየዓመቱ በከፍተኛ ሁኔታ እየቀነሰ መሆኑን ተናግረዋል። ይህም አርሶ አደሩንና ቡና ላኪውን ማኅበረሰብ ስጋት ውስጥ ከትቷል።
በዘንድሮው ዓመት ባለፉት ሶስት ወራት ውስጥ 80ሺህ ቶን ቡና ለዓለም ገበያ ተሸጦ 231 ሚሊዮን ዶላር ተገኝቷል። ጀርመን 19ሺህ ቶን ቡና ግዥ በመፈጸም ቀዳሚ አገር ስትሆን፤ ሳዑዲ አረቢያ፣ ጃፓን፣ አሜሪካ፣ ቤልጂየም፤ ኮሪያ፣ ኢጣሊያና ሱዳን በቅደም ተከተላቸው የኢትዮጵያን ቡና በዓለም አቀፍ ገበያ የገዙ አገራት ናቸው። አገራቱ በየዓመቱ የሚገዙበት ዋጋ ግን እያሽቆለቆለ መሆኑን አቶ ግዛት ወርቁ ገልጸዋል።
አዲስ ዘመን ህዳር 12/2012
አዲሱ ገረመው