የአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ አምስተኛ የምድብ ጨዋታ በሳምንቱ መጨረሻ ተካሂዶ ኢትዮጵያ በጋና በሜዳዋ 2-0 ተሸንፋ ወደ ካሜሩን የአፍሪካ ዋንጫ የማለፍ እድሏ «የማይቻል» በሚመስል መልኩ ሲጠብ ጥቋቁር ከዋክብት ደግሞ ወደ አፍሪካ ዋንጫው ለማለፍ ከጫፍ ደርሳለች። በጨዋታው እንደሚሰለፍ ተጠብቆ የነበረውና ሙሉውን ክፍለ ጊዜ በተጠባባቂ ወንበር ላይ ተቀምጦ ያሳለፈው አምበሉ አሳሞአ ጂያን ስለ ጨዋታው እና ተያያዥ ጉዳዮች ከሶከር ኢትዮጵያው ተሾመ ፋንታሁን ጋር ያደረገውን ቆይታ እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡
ሶከር ኢትዮጵያ፡- ጨዋታው እንዴት ነበር? ሜዳው፣ ደጋፊው በአጠቃላይ እንዴት አገኘኸን?
አሳሞአ ጂያን፡- በጣም ጥሩ ጨዋታ ነበር፡፡ ደጋፊው እንዳየኸው ግልብጥ ብሎ ቡድኑን ለመደግፍ መጥቷል። ይህ ከሜዳህ ውጪ ከባለሜዳ ጋር ስትጫወት ሁሌም ያለ ነው፡፡ ሜዳውም ትንሽ አስቸግሮን ነበር፤ የለመድነውን ረዥም ኳስ መጫወት አልቻልንም። ነገር ግን የምንፈልገውን ሦስት ነጥብ ይዘን ተመልሰናል፡፡ ነጥቡ በጣም ያስፈልገን ነበር። እሱን አሳክተናል። የኢትዮጵያ ቡድን ኳስ በመያዝ በጣም ጥሩ ናቸው፡፡ እኛ ደግሞ ልምድ አለን፤ ልምዳችንን ተጠቅመን አሸንፈናል። ዛሬ የነበረው ልዩነት የኛ ልምድ ነው፡፡
ሶከር ኢትዮጵያ፡- በጨዋታው ዋዜማ ለፕሬዚዳንታቸው ቡድኑን ወክለህ ቃል ስትገባ ነበር፣ ከልምምድ በኋላ በጋራ ስትዘምሩ ፊት አውራሪ ነበርክ። ዛሬም ወደ ስታዲየም ስትመጡ ቡድኑን እያነሳሳህ ስታዘምር ነበር፤ ነገር ግን ሙሉ ለሙሉ ከአሰላለፍ ውጪ ነበር። ምክንያቱ ህመም ወይስ?
አሳሞአ ጂያን፡- እንደቡድኑ አምበል እንዲሁም በቡድኑ ውስጥ ልምድ እንዳለው ተጫዋች ወጣቶቹን የመደገፍና የማበረታታት ኃላፊነት አለብኝ፡፡ ተጫዋቾቹ የተሰጣቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ የኔ እና አንድሬ (አዬው) ዓይነት ተጫዋቾች ልምድ ያስፈልጋቸዋል፡፡ ሁላችንም ረዥም ርቀት ተጉዘን ነው የመጣነው። ከኬንያ ዝግጅት አዲስ አበባ የገባነው ትናንትና ጠዋት ነው፡፡ ልምምድ ለመሥራት ወደ አዲስ አበባ ስንመጣም ሳናርፍ ነው የመጣነው፡፡ የአካል ድካም ስለነበረብን ልጆቹን በአዕምሮ ማዘጋጀት ያስፈልግ ነበር፡፡ በአዕምሮ ይበልጥ የተዘጋጀን ሆነን መቅረብ ያስፈልገን ነበር፤ ያን ደግሞ ማድረግ የኔ ኃላፊነት ነበር እሱን ነው ሳደርግ ያየኸኝ፡፡
ሶከር ኢትዮጵያ፡- ስለዚህ በቡድኑ ውስጥ የተያዝከው ለሥነ – ልቦና እንጂ ለመጫወት አልነበረም ማለት ነው?
አሳሞአ ጂያን፡- በፍጹም አይደለም፤ የአሰልጣኙ ውሳኔ ነው፡፡ እኔ በቡድኑ ውስጥ አለሁ። በቡድኑ ውስጥ እስካለሁ ድረስ ለመጫወት ዝግጁ ነኝ። ነገር ግን ማሰለፍ ወይም አለማሰለፍ የኔ ሳይሆን የአሰልጣኙ ውሳኔ ነው፡፡ ማን ይጫወት ወይም ማን ይቀመጥ የአሰልጣኛችን ውሳኔ ነው፡፡ በዛሬው ጨዋታ ለአሰልጣኙ ዕቅድ ከኔ ይልቅ ሌላ ተጫዋች ይበልጥ ያስፈልገው ነበር። ስለዚህም አልተጠ ቀመኝም፡፡ ከባለሜዳ ጋር እየተጫወትክ በመጀመሪያዎቹ ሃያ ደቂቃዎች ውስጥ ሁለት ጎል አግብተህ ከመራህ በኋላ ተጨማሪ አጥቂ ወደ ሜዳ የምታስገባው ምን ለመፍጠር ነው? አሰልጣኙ ታላቅ አሰልጣኝ ነው። ማድረግ የፈለገውን ነገር በፈለገው ሰዓት አሳክቷል፡፡ ወጣቶቹም ቢሆን የታዘዙትን ነገር በሰዓቱ አድርገዋል፡፡
ሶከር ኢትዮጵያ፡- የመጀመሪያዎቹን 20 ደቂቃዎች በሚገባ ከተጫወታችሁ በኋላ እንቅስቃሴያችሁ ወርዷል። እንደውም በሁለተኛው ግማሽ በሜዳ ላይ እንቅስቃሴም ተበልጣችሁ ነበር። ሙሉ በሙሉ ኳሱን ለኢትዮጵያ ቡድን ሰጥታችሁ ወደመከላከል ገባችሁ?
አሳሞአ ጂያን፡- በፍጹም «መስጠት» በሚለው አልስማማም፡፡ የጨዋታ ዕቅዳችን የነበረው በቻልነው አቅም ጨዋታውን በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች መጨረስ ነበር፤ ተሳክቷል፡፡ በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ዓይነት ኳስን ይዞ ከሚጫወት ቡድን ጋር ስትጫወት የምትፈልገውን ነገር በሚገባ ማወቅ ይጠበቅብሃል፡፡ የኛም ዓላማ በቻልነው አቅም በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች አግብተን ወደመደበኛ ጨዋታ መመለስ ነበር፤ አሳክተናል፡፡ እንደማሰበው የናንተም ቡድን ልጆች በሚገባ ይተዋወቃሉ። ለረዥም ጊዜ አብረው እንደተጫወቱ ያስታውቃሉ፣ ኳሷን መያዝ ያውቁበታል፣ በታክቲክና በዕቅድ ግን እኛ የተሻልን ነበርን፡፡ በጨዋታው መጀመሪያ ሁለት ጎሎች አግብተን ሳንደክም ጨዋታውን ጨርሰን ወጥተናል፡፡
ሶከር ኢትዮጵያ፡- የብሔራዊ ቡድን ጨዋታ ካቆምክ በኋላ ነው የተመለስከው። አሁንስ በአፍሪካ ዋንጫው እናይሃለን?
አሳሞአ ጂያን፡- የተመለስኩበት ምክንያት የሃገር ጥሪ ነው። ሃገሬ በፈለገችኝ ጊዜ ሁሉ እምቢ ማለት አልችልም። አሰልጣኙ ግያን ምን ማድረግ እንደሚችል ያውቃል። ስለዚህም ጥሪ አደረገልኝ መጣሁ። እቆያለው ወይም አቆማለሁ አላውቅም። ወላድ በድባብ ትሂድ ጋና በጥበብ የተሞሉ አያሌ ታዳጊዎች አሏት።
ሶከር ኢትዮጵያ፡- ጋና፣ እንግሊዝ፣ አቡዳቢ፣ ቱርክ… ቀጣይስ ወዴት ነው?
አሳሞአ ጂያን፡- የኔ ሥራ መጫወት ነው። ማኔጀሬ ምን ሠርቶ ሊበላ ነው እኔ መጪውን ክለብ የማስበው? የት እንደምሄድ አላውቅም። ጠረጴዛ ላይ የሚቀርበውን ማየት ነው።
ሶከር ኢትዮጵያ፡- ኳስ ስለማቆም እያሰብክ ነው?
አሳሞአ ጂያን፡- በፍጹም! ዕድሜህ ሲገፋ አቅምህ ሲደክም ማሰብህ አይቀርም። ነገር ግን አሁን ኳስ ስለማቆም አላስብም።
ሶከር ኢትዮጵያ፡- ኢትዮጵያን እንዴት አገኘሃት?
አሳሞአ ጂያን፡- የመጀመሪያዬ አይደለም። በተደጋጋሚ በአዲስ አበባ በኩል አልፋለሁ። ቆኝጆ ሃገር ናት፤ በርግጥ ከሆቴል ውጪ ብዙ ተዟዙሬ አላየኋትም። ያየኋትን ያህል ግን ምርጥ ህዝብ ያላት ምርጥ ሃገር ናት።
ሶከር ኢትዮጵያ፡- ስለህዝቡ ካነሳህ አይቀር ደጋፊው በተነሳህ በተቀመጥክ ቁጥር ሲጮህልህ ነበር ምን ተሰማህ?
አሳሞአ ጂያን፡- የእውነት የሚገርም ፍቅር ነው ያየሁት። ከአየር መንገድ ጀምሮ፣ በሆቴል ከዚያም ትናንት እንደገና ዛሬም… በጣም አመሰግናለው። ልዩ ፍቅር ነው ያየሁት።
ሶከር ኢትዮጵያ፡- በ2010 የዓለም ዋንጫ ስላመከንከው የፍፁም ቅጣት ምት ሳላነሳብህ ብንለያይ ሰው ምን ይለኛል?
አሳሞአ ጂያን፡- የቱ ፍፁም ቅጣት ምት? እኔ ያኔ ነው የረሳሁት። እሱን ባልረሳ እስከአሁን መጫወት አልችልም ነበር። ወደፊት ነው እንጂ እንዴት ወደኋላ ተመልሼ እሱን ላስብ እችላለው? ከዚያ በኋላ ስንት ፍፁም ቅጣት ምት መትቼ አግብቻለው፤ ለምን እሱን አስባለው።
ሶከር ኢትዮጵያ፡- በመጨረሻ ለኢትዮጵ ያውያን የምታስተላልፈው መልዕክት?
አሳሞአ ጂያን፡- ለአቀባበላችሁ በጣም እናመሰግናለን!
ምንጭ፡ ሶከር ኢትዮጵያ