የተፈጥሮ ግብርና ተፈጥሯዊ የሆኑ የአፈር ለምነት መጠበቂያ ስልቶችንና ለተባይ መከላከያ የሚውሉ የግብርና ግብዓቶችን በመጠቀም የሚተገበር የአመራረት ዘዴ መሆኑን በዘርፉ የተሰማሩ ምሁራን ይገልጻሉ፡፡
በተፈጥሮ ግብርና ዘዴ ከአላስፈላጊ ንጥረ ነገሮችና ኬሚካሎች ንክኪ የጸዱ ቁሳቁሶችን መጠቀም ግዴታ ከመሆኑም በአሻገር የአፈር ለምነት መጠበቂያና የተባይ መከላከያ ግብዓቶችን ለማግኘት አገር በቀል ዕውቀትን መጠቀም መለያው ነው፡፡ በተጨማሪም የአርሶ አደሩን ፈጠራዎች፣ ሳይንስ፣ የሥነ ምህዳር ሂደቶችንና የብዝሃ ህይዎትን ጥምረትና መስተጋብር የሚጠይቅ መሆኑን የዘላቂ ልማት መካነ ጥናት የተፈጥሮ ግብርና ከፍተኛ ባለሙያ ወይዘሮ አዜብ ወርቁ ያስረዳሉ፡፡
የተፈጥሮ ግብርና አፈርን ከመሸርሸር በመከላከልና ለምነቱን በመጠበቅና የአየር ንብረት ብክለትን በመቀነስ ጤናማ ሥነ ምህዳርን ለመፍጠር ጉልህ ሚና ይጫወታል፡፡ ከዚህም ባሻገር ምርትና ምርታማነትን በማሻሻልና የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ ዘላቂ ልማት እንዲመጣ በማድረግ በኩል ድርሻው ከፍተኛ ነው፡፡ ከዚህ የተነሳ በተፈጥሮ ግብርና ዘዴ የሚመረቱ ምርቶች ከኬሚካል የጸዱና ተፈጥሯዊ ይዞታቸውን የጠበቁ በመሆናቸው በዓለም ገበያ ላይ ተፈላጊ ከመሆናቸውም ባሻገር በዋጋ ደረጃም ከመደበኛው ግብርና ምርቶች የበለጠ የሚያስገኙ መሆናቸውን የግብርና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሳኒ ረዲ ይናገራሉ፡፡ በኢትዮጵያም ምንም እንኳን ዘርፉ በዝቅተኛ የእድገት ደረጃ ቢሆንም በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2015 ብቻ ወደ ውጭ ከተላኩ የተፈጥሮ ግብርና ምርቶች 181 ሚሊዮን ዩሮ ገቢ መገኘቱን ነው ሚኒስትር ዴኤታው የሚገልጹት፡፡
እንደ ሚኒስትር ዴኤታው ገለጻ አገሪቱ በተፈጥሮ ግብርና ዘርፍ ከፍተኛ የሆነ ዕምቅ ኃይል አላት፡፡ በዚህም የአንበሳውን ድርሻ የሚይዘውን የቡና ምርት ጨምሮ፣ ሰሊጥ፣ ማር፣ ቅመማ ቅመምና ሌሎችም የተፈጥሮ የግብርና ዘዴን ተከትለው የሚመረቱ ናቸው፡፡ የዓለም አቀፉ የተፈጥሮ ግብርና እአአ የ2018 መረጃም ለዚህ ጥሩ ማሳያ ይሆናል፡፡ በዚህ መረጃ መሰረት በኢትዮጵያ በተፈጥሮ ግብርና ሊለማ የሚችል 161ሺ113 ሄክታር የቡናና 24 ሺ936 ሄክታር በቅመማ ቅመም ሊለማ የሚችል የእርሻ መሬት አለ፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ከሁለት መቶ ሺ በላይ አርሶ አደሮችና የግለሰብ አምራቾች፣ 23 አቀናባሪዎችና አርባ ላኪዎች በተፈጥሮ ግብርና ላይ ተሰማርተው ይገኛሉ፡፡
ይሁን እንጂ አገሪቱ ካላት ግዙፍ ተፈጥሮ ግብርና ዕምቅ ሀብት አኳያ ማግኘት የሚገባትን ያህል እየተጠቀመች አለመሆኗን በግብርና ሚኒስቴር የዕፅዋት ጤናና ጥራት ቁጥጥር ዳይሬክተር ጀኔራል አቶ ወልደሃዋርያት አሰፋ ይገልጻሉ፡፡ ለዚህ ዋነኛ ምክንያቱ ደግሞ የተፈጥሮ ግብርና ሥርዓትን የሚመለከት አዋጅ 488/1998 ከአስራ ሦስት ዓመታት በፊት ጀምሮ የወጣ ቢሆንም አዋጁን ለማስፈጸም የሚያስችሉ ደንብና መመሪያዎች ባለመዘጋጀታቸው እስካሁን ድረስ ወደ ተግባር ባለመገባቱ ነው፡፡ ስለሆነም ደንብና መመሪያዎችን ለማውጣትና አዋጁን ሥራ ላይ በማዋል አገሪቱን ከዘርፉ ማግኘት የሚገባትን ያህል ተጠቃሚ ለማድረግ በግብርና ሚኒስቴርና በዘላቂ ልማት መካነ ጥናት የጋራ አዘጋጅነት ሰሞኑን በቢሾፍቱ ከተማ አገራዊ ጉባኤ ተካሂዷል፡፡
በጉባኤው ከግብርና ሚኒስቴር፣ የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ አመራሮች፣ የግሉ ዘርፍ፣ ከዩኒቨርሲቲዎችና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተውጣጡ ምሁራንና ተመራማሪዎችና ሌሎችም ባለ ድርሻ አካላት ሁለት ቀናትን የፈጀ ውይይትና ምክክር አድርገዋል፡፡ በዚህም ሁሉንም ባለ ድርሻ አካላት በማሳተፍ የተፈጥሮ ግብርናን በዘላቂነት ጥቅም ላይ ለማዋል በሚቻልበት መንገድ አዋጁን የማስፈጸሚያ ደንብና መመሪያዎች ዝግጅት ላይ በምሁራን ጥናታዊ ጽሁፎች ቀርበው ገንቢ ውይይት ከተደረገባቸው በኋላ ለመነሻ የሚሆኑ ሃሳቦች ተሰብስበውበታል፡፡
የተፈጥሮ ግብርና ያለበት ነባራዊ ሁኔታ፣ ያሉበት ተግዳሮቶች፣ በአግባቡ ቢተገበር ለአገሪቱ የሚኖረው ፋይዳ፣ የዘርፉ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ተሞክሮዎች፣ ቀደም ሲል ወጣውን አዋጅ ተግባር ላይ ለማዋል የሚያስችሉ የህግ ማዕቀፎችና አጠቃላይ የአሰራር ሥርዓቶችን በማዘጋጀት ላይ ዝርዝር ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡ ሁሉም በየደረጃው የሚገኘው አመራርና ባለሙያ ስለ ጉዳዩ በሚገባ እንዲያውቅና ህብረተሰቡንም እንዲያውቅ በማድረግ በተፈጥሮ ግብርና አተገባበር ዙሪያ የጋራ ግንዛቤ ለመፍጠር ለመጀመሪያ ጊዜ የተካሄደው አገራዊ ጉባኤ በሚፈለገው ደረጃ በውጤታማነት መጠናቀቁንም ከጉባኤው አዘጋጆች ለመረዳት ተችሏል፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 22/2011
በይበል ካሳ