የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወ/ሪት ብርቱካን ሚዴቅሳ የሲዳማ ህዝበ ውሳኔ ድምጽ ሰጪዎች ምዝገባ መጠናቀቅን አስመልክቶ ትናንት በሀዋሳ በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት ፤ በህዝበ ውሳኔው ድምጽ ለመስጠት ከጥቅምት 27 ቀን 2012 እስከ ህዳር 6 ቀን 2012 ዓ.ም ድረስ በተካሄደው ምዝገባ ከሁለት ነጥብ ሦስት ሚሊዮን በላይ መራጮች ተመዝግበዋል፡፡ የድምጽ ሰጪዎች ምዝገባ ሂደት ሙሉ በሙሉ ሰላማዊ በሆነ መንገድ የተጠናቀቀ ሲሆን፤ የዞኑና የክልሉ የጸጥታ አካላት፣ የፌዴራል ፖሊስ እንዲሁም የመከላከያ ሰራዊት ለሂደቱ ሰላማዊነት ከፍተኛ ትብብር አድርገዋል፡፡
የሲዳማ ዞን ህዝብ የክልልነት ጥያቄ እልባት የሚሰጠው ይህ ህዝበ ውሳኔም በነገው እለት ይካሄዳል፡፡ ለህዝበ ውሳኔው የሚደረገው አስፈላጊው ዝግጅት ተጠናቅቋል፤ህዝቡም ለዓመታት ሲጠብቀው የቆየው ቀን በመድረሱ በህዝበ ውሳኔው ድምጹን ለመስጠት እየተጠባበቀ ይገኛል።
የሲዳማ ዞን የደቡብ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል ከመመስረቱ በፊት በነበረው የሽግግር መንግሥት ቻርተር ከሀገሪቱ ክልሎች አንዱ እንደነበር ይታወቃል። የኢፌዴሪ ህገ መንግሥት ሲጸድቅ በሽግግሩ ወቅት ሲዳማ ዞንን ጨምሮ በደቡብ የነበሩት አምስት ክልሎች በጋራ የደቡብ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልልን መስርተዋል፡፡ በህገመንግሥቱ አንቀጽ 47/2 እንደተደነገገው በዘጠኙ ክልሎች ውስጥ የተካተቱ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች በማንኛውም ጊዜ የራሳቸውን ክልል የማቋቋም መብት እንዳላቸው ተደንግጓል፡፡
የሲዳማ ዞን ህዝብም ህገ መንግሥቱን መሰረት አድርጎ ነው ለዓመታት ክልል የመሆን ጥያቄን ሲያነሳ የቆየው፡፡ ይሁንና ክልል የመሆን መብት በግልጽ ተደንግጎ እያለ ዞኑ ክልል እንዳይሆን ተደርጓል፤ህዝቡ ጥያቄውን ለማሰማት አደባባይ ሲወጣም በግፍ ተገድሏል፡፡ በሀዋሳ ሎቄ አካባቢ ይህን ጥያቄ ይዘው በወጡ የሲዳማ ብሄረሰብ አባላት ላይ የተካሄደው ግድያ ለዚህ ማሳያ ነው፡፡
ህዝቡ ጥያቄውን በዚህ የለውጥ ወቅትም አንስቷል፡፡ መንግሥትም ጉዳዩን በሚገባ እንዲያጤኑት ሲያስገነዝብ ቆይቷል፡፡ይሁንና ጥያቄው መቅረቡን በመቀጠሉ ጥያቄው በምርጫ ቦርድ በኩል እንዲፈጸም አቅጣጫ አስቀምጧል፤ ይሁንና ይህ አቅጣጫ ተቀምጦ እያለም አንዳንድ ወገኖች የህዝቡን ጥያቄ ላልተፈለገ ዓላማ ለማዋል መፈለጋቸውን ተከትሎ ጥያቄውን በጉልበት ለማስፈጸም በተደረገ ሙኩራም የሰው ህይወት ማለፉ ይታወቃል፡፡
መንግሥት በወቅቱ የተፈጠረውን ግጭት በማስቆም እና በኃይል ጥያቄን ለማስፈጸም መሞከር ኢ ህገመንግሥታዊ መሆኑን ከማስገንዘብ ጎን ለጎን ህዝበ ውሳኔው በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ መሰረት እንዲፈጸም ሲሠራ ቆይቷል፡፡ በዚህም መሰረት ህዝበ ውሳኔው ተአማኒነት ባለው መልኩ ያለምንም ችግር እንዲካሄድ ለማድረግ የምርጫ አስፈጻሚዎች ምልመላ ተካሂዶ ስልጠናም ተሰጥቷል፡፡ የምርጫ ታዛቢዎችም ተመልመለው ተሰማርተዋል፡፡ የመራጮች ምዝገባም በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ተፈጽሟል፡፡
የሲዳማ ህዝብ የክልል እንሁን ጥያቄ የትናንት አይደለም፡፡ ሲንከባለል ከርሞ አሁን ላለንበት የለውጥ ወቅት ደርሷል፡፡ መንግሥት በርካታ ሊከናወኑ የሚገባቸው ተግባሮች እያሉ ህዝበ ውሳኔውን ከቀዳሚዎቹ ተግባሮቹ አንዱ አድርጎ መሥራቱ ለህዝብ ጥያቄ ምላሽ በመስጠት በኩል የማያወላዳ አቋም እንዳለው ያመለክታል፡፡
ህዝበ ውሳኔን ያህል ጉዳይ ያለበቂ ዝግጅት ሊካሄድ እንደማይችል ይታወቃል፡፡ መንግሥት ከዚህ አንጻር ጊዜ ወስዶ መሥራቱን እንደ ትልቅ ስኬት መውሰድ ይገባል፡፡ ሀገሪቱ ከሰላም እና ደህንነት አኳያ ውጥረት ውስጥ ባለችበት በዚህ ወቅት ይህ ህዝበ ውሳኔ ያለምንም እንከን እንዲካሄድ በመንግሥት በኩል የተያዘው ቁርጠኝነት አድናቆት ሊቸረው ይገባል፡፡
የህዝበ ውሳኔው ውጤት ምንም ይሁን ምን የለውጡ ትሩፋት ተደርጎም መወሰድ ይኖርበታል፡፡ ከለውጡ በፊት የነበረው መንግሥት እንደ ጥያቄም ሳይቆጥረው የቆየውን ጉዳይ ለውጡ ፈትቶታል፤ይህም ለውጡ የማይፈታው ችግር እንደሌለ ጭምር ያመለክታል፡፡
የሲዳማ ዞን የሥራ ኃላፊዎች የሲዳማ ህዝብ ክልል ሲሆን በአቃፊነቱ እንደሚቀጥል በሁሉም መስክ በክልሉ ከሚኖሩ የተለያዩ ህዝቦች ጋር ሁሉ አብሮ መሥራቱን እንደሚቀጥል ሲያረጋግጡ በቆዩት መሰረት ነገ የሚካሄደው ህዝበ ውሳኔ በስኬት እንዲጠናቀቅ አብረው መሥራታቸውን ማጠናከር ይኖርባቸዋል፡፡ የሲዳማ ህዝብም ሆነ ሌሎች በክልሉ የሚኖሩ ህዝቦችም ለህዝበ ውሳኔው ስኬታማነት የበኩላቸውን በማድረግ ይህን የለውጥ ትሩፋት ማጣጣም አለባቸው፡፡ ሌሎች ባለድርሻ አካላትም እስከ አሁን ሲያደርጉት የቆዩትን ርብርብ በማጠናከር ህዝበ ውሳኔው በሰላማዊ መንገድ እንዲጠናቀቅ ማድረግ ይገባቸዋል፡፡
አዲስ ዘመን ህዳር 9/2012