– የድምፅ ሰጪዎች ምዝገባ በሰላም ተጠናቋል
– ከሁለት ነጥብ ሦስት ሚሊየን በላይ ድምፅ ሰጪዎች ተመዝግበዋል
– የድምፅ አሰጣጥ ሂደቱ ፍፁም ሰላማዊ እንዲሆን በትኩረት ይሠራል
ሐዋሳ፡- የሲዳማ ህዝበ ውሳኔ ድምፅ ሰጪዎች ምዝገባ በሰላም መጠናቀቁን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ። በህዝበ ውሳኔው ድምጽ ለመስጠት ከሁለት ነጥብ ሦስት ሚሊየን በላይ ድምጽ ሰጪዎች መመዝገባቸውንና በነገው ዕለት የሚካሄደው የድምጽ አሰጣጥ ሂደትም ፍፁም ሰላማዊ እንዲሆን በትኩረት እንደሚሠራም ገለፀ።
ከጥቅምት 27 እስከ ህዳር 6/ 2012 ዓ.ም ሲካሄድ የቆየው የሲዳማ ህዝበ ውሳኔ መጠናቀቁን አስመልክቶ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ዋና ሰብሳቢ ወይዘሪት ብርቱካን ሚዴቅሳ ትናንት በሐዋሳ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት፤ ከስድስት ሺ በላይ የምርጫ አስፈፃሚዎች በአንድ ሺ 692 የምርጫ ጣቢያዎች ተሰማርተዋል፤ 15 የወረዳ ማስተባበሪያ ጣቢያዎችና የዞን ማስተባበሪያው የመራጮች ምዝገባ ሥራቸውን አከናውነዋል።
የመራጮች ምዝገባ ሂደት ሙሉ በሙሉ ሰላማዊ ሆኖ መጠናቀቁን የተናገሩት ሰብሳቢዋ፤ ሂደቱ ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የዞኑና የክልሉ የፀጥታ አካላት፣ የፌዴራል ፖሊስና የመከላከያ ሠራዊት ከፍተኛ ትብብር ማድረጋቸውን ዋና ሰብሳቢዋ ገልፀዋል።
እንደ ዋና ሰብሳቢዋ ማብራሪያ፤ ቦርዱ የተለያዩ መንገዶችን በመጠቀም መረጃ በመሰብሰብ፣ የመስክ ጉብኝት በማድረግ፣ አቤቱታ ካላቸውና ከቦርዱ ጋር መወያየት ከሚፈልጉ አካላት ጋር በመወያየት እንዲሁም የፀጥታ ችግሮችን በጋራ የሚያይ መድረክ በማቋቋም የምዝገባ ሂደቱ የተሳካ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ሠርቷል። አቤቱታና ጥቆማ ያላቸው አካላት ቅሬታና አቤቱታ የሚያቀርቡበት የቀጥታ ስልክ ጥሪ መስመር በማሳወቅ የሚቀርቡ ቅሬታዎችንና አቤቱታዎችን በማጣራት የማስተካከያ ሥራዎች ተሠርተዋል። ይህም የምዝገባው ሂደት ሰላማዊና የተቀላጠፈ እንዲሆን አስችሏል።
እንደ ወይዘሪት ብርቱካን ገለፃ፤ ለቦርዱ በደረሰው ሪፖርትና በተደረጉ የመስክ ጉብኝቶች ከተመለከቱትና የማስተካከያ እርምጃ ከተወሰደባቸው ክፍተቶች መካከል በአንዳንድ የምርጫ ጣቢያዎችና በ200 ሜትር ርቀት ውስጥ መገኘት የማይገባቸው ሰዎች እንዲሁም የተከለከሉ ምልክቶች ታይተው ነበር። ይህንንም ከሚመለከታቸው የዞኑ አመራሮች ጋር በመነጋገር መገኘት የማይገባቸው አካላት በአካባቢው እንዳይገኙና ምልክቶቹ ላይ መወሰድ ያለባቸው ማስተካከያዎች እንዲወሰዱ ተደርጓል።
የመራጮች ካርድ ወደ ቤት በመውሰድ ከፍተኛ የሕግ ጥሰት የፈፀሙ አንድ አስፈፃሚ ከሥራ እንዲሰናበቱ መደረጋቸውን ዋና ሰብሳቢዋ ጠቅሰው፣ የመራጮች መዝገብ ይዘው ከአካባቢው ለመሰወር የሞከሩ ሌላ አስፈፃሚም በቁጥጥር ሥር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸው መሆኑን ተናግረዋል።
ከሲቪል ማህበራት ለተወጣጡ 16 ቋሚና ተዘዋዋሪ ታዛቢዎች ስልጠና በመስጠትና ተዘዋውረው የመራጮች ምዝገባ ሂደትን እንዲታዘቡ መደረጉን የተናገሩት ዋና ሰብሳቢዋ፤ ነገ የሚካሄደውን የድምጽ አሰጣጥ ሂደት የሚታዘቡ 160 ገደማ ተቀማጭና ተዘዋዋሪ ታዛቢዎች በአሁኑ ወቅት ስልጠና እየወሰዱ መሆናቸውን አመልክተዋል። የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በህዝበ ውሳኔው ድምጽ አሰጣጥ ዙሪያ የሰዎች መብት አጠባበቅን ምን ይመስላል የሚለውን የሚታዘቡ ተጨማሪ ታዛቢዎችን እንደሚያሰማራም ተናግረዋል።
የመራጮች ምዝገባ ከተጠናቀቀ በኋላ የምርጫ ጣቢያዎቹ ለህዝብ ክፍት ሆነው የተመዘገቡት ሰዎች ማንነት ዝርዝር መረጃ ክፍት መደረጉን ጠቅሰው፣ ቅሬታ ያለው ቅሬታውን እንዲያቀርብ ቢደረግም የቀረበ ቅሬታ ግን አለመኖሩን ተናግረዋል። ዋና ሰብሳቢዋ ቦርዱ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን የድምጽ አሰጣጥ ሂደቱ ፍፁም ሰላማዊና የተቀላጠፈ እንዲሆን አበክሮ እንደሚሠራ አረጋግጠዋል። የመራጮች ምዝገባ የተሳካ እንዲሆን የበኩላቸውን የተወጡ አካላትም የድምጽ መስጫ ሂደትም ሰላማዊ እንዲሆን እንዲሠሩ ጥሪ አቅርበዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የሲዳማ ህዝበ ውሳኔ በሰላም እንዲጠናቀቅ አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉን የሲዳማ ዞን እና የሐዋሳ ከተማ አስተዳደር የሥራ ኃላፊዎች በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል። የሲደማ ዞን ሰላምና ፀጥታ መምሪያ ኃላፊ አቶ አለማየሁ ጢሞቴዎስ እንደተናገሩት፤ 10 ሺ ወጣቶች፣ 15ሺ ሚሊሻዎችና ከ300 እስከ 500 የመከላከያ አባላት እንዲሁም የዞንና የክልል የፀጥታ አካላትና የፌዴራል ፖሊስ አባላት የድምፅ አሰጣጡን ሰላማዊ እንዲሆን የድርሻቸውን ሊወጡ ተዘጋጅተዋል።
የከተማው የሰላምና ፀጥታ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ኮሎኔል ሮዳሞ በበኩላቸው የቅስቀሳና የመራጮች ምዝገባ በሰላም መጠናቀቁን ገልፀው፣ የድምፅ አሰጣጥ ሂደቱም ሰላማዊ እንዲሆን በቂ ዝግጅት መደረጉን አብራርተዋል።የሥራ ኃላፊዎች እንደተናገሩት፤ ድምፅ በሚሰጥበት በነገው ዕለት በሐዋሳ ከተማና በዞኑ የሚገኙ የመንግሥትና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች አገልግሎት አይሰጡም። ትምህርት ቤቶችም ይዘጋሉ። የጫት ንግድ ቤቶችና ሞተር ሳይክሎችም ጭምር አገልግሎት አይሰጡም።
አዲስ ዘመን ህዳር 9/2012
መላኩ ኤሮሴ