አዲስ አበባ፡- የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በሚዋሐደው ፓርቲ ሕገ ደንብ ላይ ትናንት ውይይት አድርጎ በማፅደቅ ለኢህአዴግ ምክር ቤት መምራቱን የኢህአዴግ ሊቀመንበር ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ አስታወቁ።
ሊቀመንበሩ እንዳሉት፤ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴው በሦስቱ ቀናት ስብሰባው በሦስት መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ በማፅደቅ ለኢህአዴግ ምክር ቤት መርቷል። በመጀመሪያ በጥልቅ ተወያይቶ ያፀደቀው የፓርቲውን ውህደት፤ አሳታፊነትና አካታችነት ሲሆን፣ ሁለተኛው ሁሉንም ማኅበረሰብ ወደፊት የሚያራምደውን የፓርቲውን ፕሮግራም ሦስተኛው ደግሞ ሕገ ደንቡን ነው።
የሦስቱም ቀናት ውይይት ግልፅና ደሞክራሲያዊ በሆነ መልኩ መካሄዱን ጠቅሰው፣ ውይይቱ አመራሮቹን ይበልጥ ያቀራረበ ሆኖ በመጠናቀቁን ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማቸውም በይፋዊ የፌስቡክ ገፃቸው አስፍረዋል።
በተያያዘ ዜናም የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ትናንት ባካሄደው የ3ኛ ቀን ውሎ ስብሰባም ብልፅግና ፓርቲ የሚለው ስያሜ ለውህዱ ፓርቲ እንዲሆን በሚል ለኢህአዴግ ምክር ቤት እንዲቀርብ ከስምምነት ላይ መድረሱን የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል አቶ ፍቃዱ ተሰማ አስታውቀዋል።
ለፓርቲው የሥራ ቋንቋነትም አማረኛ፣ አፋን ኦሮሞ፣ ሱማልኛ፣ ትግርኛ እና አፋርኛ ቋንቋዎች የተመረጡ ሲሆን፣ ፓርቲው በአገሪቱ ለሚገኙ ቋንቋዎች በሙሉ እውቅና መስጠቱም ተገልጿል። ፓርቲው ፕሬዚዳንት እና ምክትል ፕሬዚዳንት ይኖሩታልም ተብሏል። በክልሎችም የክልል ስያሜዎችን እንደያዘ የብልፅግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ይኖራል ተብሏል።
አዲስ ዘመን ህዳር 9/2012
በጋዜጣው ሪፓርተር