አዲስ አበባ:-ኢትዮጵያ በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብ ወይም ንብረት ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መደገፍ ወንጀሎችን በመከላከልና በመቆጣጠር ረገድ መሻሻል አሳይታለች በሚል ከዓለም አቀፉ የፋይናንስ ድርጊት ግብረ-ኃይል ጥቁር መዝገብ መውጣቷ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ትሩፋት እንዳለው የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች አስታወቁ።
ከጥቁር መዝገቡ መውጣት ስለሚሠጠው ትሩፋት አዲስ ዘመን ያነጋገራቸው የምጣኔ ሀብት ባለሙያው አቶ ዘመዴነህ ንጋቱ እንደገለፁት፣ አንድ አገር በጥቁር መዝገቡ ውስጥ ከተካተተ ከዓለም አቀፍ ባንኮች ጋር በትብብር ለመሥራት ይቸገራል። ባለሀብቶች በኢንቨስትመንት ለመሰማራት እምነት አይኖራቸውም። ቱሪስቶች ገንዘባቸውን እንደፈለጉ መገልገል ይሳናቸዋል።
ከጥቁር መዝገቡ መውጣት በተለይ ለአገራት ኢኮኖሚ መነቃቃት ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለው ያስገነዘቡት አቶ ዘመዴነህ፣ ‹‹ውሳኔውም ለአገር ውስጥም ሆነ ለውጭ ኢንቨስተሮች መልካም የሚባል ዜና ነው፣ በተለይ የአገሪቱ ባንኮች ከድንበር ተሸጋሪ ባንኮች ጋር ያላቸውን ግንኙነት በመቀየር አጋርነታቸውን እንዲያጎለብቱ ያደርጋል›› ብለዋል።
አቶ ዘመዴነህ ከጥቁር መዝገብ መውጣት ማለት ለአንዴና መጨረሻ ጊዜ ሁሉም ፋይል ተዘጋ ማለት አለመሆኑን በመረዳት የሚመለከታቸው አካላት ወንጀሉን የመከላከሉንና የመቆጣጠሩን ተግባርም ማጠናከር እንደሚገባቸውም አስገንዝበዋል። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ መምህር ረዳት ፕሮፌሰር ብርሃኑ ደኑ በበኩላቸው፣ የፋይናንስ ደህንነትን ማረጋገጥ አለመቻል የሚፈጥረው ከባድ ራስ ምታት ከአገር እስከ ህዝብ አለፍ ሲልም እስከ ግለሰብ እንደሚዘልቅ ጠቁመዋል።
ከጥቁር መዝገብ መውጣትም ሌሎች አገራት በኢትዮጵያ ላይ የሚያደርጉትን ቁጥጥርና ክትትል እንዲያነሱ በማድረግ የአገርን መልካም ስም የማጉላት በተለይ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው የላቀ መሆኑን የገለፁት ረዳት ፕሮፌሰሩ፣ መሰል መልካም ውጤቶችን ማስቀጠል የሚፈጥረውን አዎንታዊ ትሩፋት ለመቋደስ ለአገር ውስጥ የቤት ሥራዎችም ትኩረት መስጠት የግድ መሆኑን አስገንዝበዋል።
የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ዶክተር ቆስጠንጢኖስ በርሄም ምንም እንኳን በመንግሥት ከፍተኛ ጥረት ሕገ ወጥነቱ በተደጋጋሚ ሲጋለጥ ቢስተልም በአሁን ወቅት የሚስተዋለው ከፍተኛ የኮንትሮባንድ በተለይ የገንዘብ ዝውውር ወንጀሉን የመከላከሉን ተግባር መጠናከር እንዳለበት አስገንዘበዋል።
ምክረ ሐሳቦችን በማውጣት የአገራትን ሁኔታ በየጊዜው የሚገመግመውንና ወንጀሉን በመከላከል ረገድ ደካማ የሆኑትን በጥቁር መዝገቡ የሚያካትተው ዓለም አቀፉ የፋይናንስ ድርጊት ግብረ-ኃይል የተቋቋመው እ.ኤ.አ በ1989 የቡድን ሰባት አባል አገራት በፈረንሳይ ፓሪስ ጉባኤያቸውን ባካሄዱበት ወቅት መሆኑን መረጃዎች ይጠቁማሉ።
አዲስ ዘመን ህዳር 9/2012
ታምራት ተስፋዬ