አዲስ አበባ፡- በአርሲ ዩኒቨርሲቲ የመማር ማስተማሩ ሂደት ሰላማዊ ሆኖ መቀጠሉንና የዩኒቨር ሲቲው የአካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት አስታወቁ። ሰላሙን አጠናክሮ ማስቀጠል የሚያስ ችሉ ውይይቶቹ በዩኒቨርሲቲው የተለያዩ ካምፓሶች እየተካሄዱ መሆናቸውን ገለፁ።
ምክትል ፕሬዚዳንቱ ዶክተር ቃሲም ኪሞ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደተናገሩት፤ በዩኒቨርሲቲው አራቱም ካምፓሶች ቀደም ሲልም ሆነ ካለፈው ሳምንት አንስቶ የመማር ማስተማሩ ተግባር ሰላማዊ በሆነ መንገድ እየተካሄደ ይገኛል። ከመማር ማስተማሩ ጎን ለጎን ውይይቶች እየተካሄዱ ናቸው::
በወልዲያ በተፈጠረው ችግር ህይወቱን ያጣው የአሰላ አካባቢ ልጅ መሆኑን ጠቅሰው፣ ይህን ተከትሎም ለአንድ ቀን ችግር ተከስቶ እንደነበረ ተናግረዋል። ከዚያን ቀን በስተቀር ምንም አይነት ችግር እንደሌለ አስታውቀው፣ ተማሪዎችም ትምህርታቸውን በአግባቡ እየተከታተሉ መሆናቸውን ገልፀዋል፤ ከዚሁ ጎን ለጎንም ሰላሙን ዘላቁ በማድረግ ላይ ከተማሪዎች ጋር ውይይቶች እየተካሄዱ መሆናቸውን ተናግረዋል። ምንም አይነት ሥጋት እንዳይኖር በመታሰቡም ትናንት ጠዋት በየካምፓሶቹ በተናበበ መልኩ የፍተሻ ሥራ መካሄዱንም ገልፀዋል።
ዶክተር ቃሲም፣ ‹‹በእኛ ዩኒቨርሲቲ ትምህርት አልተቋረጠም። ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሥራው ቀጥሏል። በበቆጂ ካምፓስ ትናንት ከዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ጋር ውይይት ተካሂዷል። ሰላማዊው የመማር ማስተማር ሥራ ይበልጥ እንዲጠናከር በየትምህርት ክፍሉ የተማሪዎች ውይይቱ እንዲቀጥል ይደረጋል።›› ብለዋል።
‹‹እስከ አሁን ከቁጥጥር ውጭ የሆነ ነገር አላጋጠመም።›› ያሉት ምክትል ፕሬዚዳንቱ፣ ከዞኑም ሆነ ከከተማ አስተዳደሩ እንዲሁም ከከንቲባ ጽህፈት ቤት ጋርም በመናበብ እየተሠራ መሆኑንና ይህም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።
ዶክተር ቃሲም፣ ‹‹አስቸጋሪ ሁኔታዎች ቢያጋጥሙም፣ ተማሪዎች የመጡት ለትምህርት እስከሆነ ድረስ ዓላማቸውን ከግብ ለማድረስ መማር ይጠበቅባዋል፤ ማንኛውንም አይነት ችግር ማሸነፍ የሚችሉት ሲማሩ ነውና በተቻላቸው ሁሉ ትኩረታቸውን ለትምህርታቸው ቢያደርጉ ይመረጣል።›› ብለዋል።
አዲስ ዘመን ህዳር 9/2012
አስቴር ኤልያስ