ሐዋሳ፡- በሐዋሳ ከተማ ባለፉት ሦስት ወራት የተዘረፉ ሁለት ነጥብ ሁለት ሚሊየን ብር የሚገመቱ የመብራት ገመዶችን መተካቱን የከተማዋ ማዘጋጃ ቤት ገለፀ።
የማዘጋጃ ቤቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ፍቅሩ ተስፋዬ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደገለፁት፤ በሐዋሳ ከተማ ከዚህ በፊት ታይቶ በማይታወቅ መልኩ በሦስት ወራት ሁለት ነጥብ ሁለት ሚሊየን ብር የሚገመቱ ከ380 በላይ የመንገድ ዳር የመብራት ምሰሶዎች የውስጥ ገመዶች ላይ ዘረፋ ተካሂዷል። ገመዶቹን የመተካት ሥራ በአስቸኳይ መተካት እንዳለበት በመታመኑ ካለፉት አራት ቀናት ወዲህ ገመዶቹን የመተካት ሥራ ሲሰራ ቆይቶ ትናንት ተጠናቋል።
ዘረፋው በአራት ክፍለ ከተሞች ውስጥ በሚገኙ በአራት ዋና ዋና መንገዶች ላይ የሚገኙ የመንገድ ዳር የመብራት ምሰሶዎች ገመዶች ላይ ያነጣጠረ እንደነበር የተናገሩት አቶ ፍቅሩ፣ ሕገወጦቹ ዘረፋውን በሁሉም ክፍለ ከተሞች ላይ በመፈፀም ከተማዋን ብርሃን የማሳጣት ዕቅድ እንደነበራቸው የተደረሰበት መሆኑን ገልፀ ዋል።
ዘረፋው የሲዳማ ህዝበ ውሳኔ እንደሚካሄድ ይፋ የተደረገበት ሰሞን መጀመሩን የሚጠቅሱት አቶ ፍቅሩ፣ ዘረፋውን ሲፈፅሙ የነበሩ አካላት በቁጥጥር ሥር ባይውሉ ኖሮ በከተማዋ በሙሉ የሚገኙ የመብራት ገመዶችን የመዝረፍ ዕቅድ እንዳላቸው አስረድተዋል፤ በዚህም ድርጊታቸው ከተማዋን ብርሃን አልባ በማድረግ ለወንጀል ፈፃሚዎች ምቹ ሁኔታ የመፍጠር ዓላማ እንደነበራቸውም ተናግረዋል።
እንደ አቶ ፍቅሩ ማብራሪያ፤ ገመዶቹን የመተካት ሥራ ከመሥራት ጎን ለጎን ከህዝብና ከፖሊስ ጋር በመሆን ይህንን ተግባር ሲፈፅም የነበረውን አራት አባላት ያሉት ቡድን በቁጥጥር ሥር በማዋል ምርመራ እየተካሄደባቸው ነው። ዘረፋውን ሲፈፅሙ የነበሩ አካላትም በሐዋሳ ከተማና በሌሎች ከተሞች ገመዶቹን ሲያከማቹ ከነበሩበት ቦታ የማስመለስ ሥራ ተሠርቷል። የከተማዋ ነዋሪ መሰል ችግሮችን የሚፈፅሙ አካላትን ለከተማ አስተዳደሩና ለፖሊስ በማሳወቅ የበኩሉን ሊወጣ እንደሚገባም አብራ ርተዋል።
አዲስ ዘመን ህዳር 9/2012
መላኩ ኤሮሴ