አዲስ አበባ፡- አገሪቱ የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦትንና ዘመናዊ የመፀዳጃ ቤቶች አገልግሎት ተደራሽነትን ለማረጋገጥ በውሃው ዘርፍ የሰለጠነ ባለሙያ በብዛት እንደሚያስፈልግ ተገለፀ።
የኢትዮጵያ ውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በጃፓን ዓለም አቀፍ ተራድኦ ድርጅት ድጋፍ ኢትዮጵያን ጨምሮ ለናይጄሪያና ለማላዊ የውሃ ዘርፍ ባለሙያዎች የተዘጋጀው ስልጠና በተጀመረበት ወቅት የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ኢንጂነር ስለሺ በቀለ እንደገለፁት፤ የኢትዮጵያ መንግሥት ብሔራዊ የልማት ግቦቹን ለማሳካት የተለያዩ ስትራቴጂዎችን ነድፎ እየተገበረ ይገኛል። ከስትራቴጂዎቹ አንዱም የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦትንና ዘመናዊ የመፀዳጃ አገልገሎትን በሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ማቅረብ ነው።
ይህን ለማሳካትም አገሪቱ በውሃው ዘርፍ የሰለጠነና በቂ ክህሎት ያለው የሰው ኃይል በሁሉም ደረጃ እንደሚያስፈልጋት ጠቅሰው፣ መንግሥት ይህን ፍላጎት ለመሟላት እንዲቻል ለውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ኃላፊነት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑን ገልፀዋል። ኢንስቲትዩቱም በስልጠና፣ በጥናትና ምርምር በቴክኖሎጂ ሽግግር መካከለኛ ባለሙያዎችን በማፈራት እየሠራ መሆኑን ተናግረው፣ እስከ አሁንም የአፍሪካ አገሮች ሰልጠኞችን ጨምሮ ከ1ሺ200 በላይ ሰልጠኞችን ማስመረቁን ጠቅሰዋል።
መንግሥት ኢንስቲትዩቱን በ2025 የምስራቅ አፍሪካ የውሃው ዘርፍ የልህቀት ማዕከል ለማድረግ እየሠራ መሆኑን ተናግረው፣ ‹‹እውቀታችንን በማቀናጀት በአፍሪካ የውሃ ዋስትናን ለማሳካት እንሥራ›› ሲሉም ሚኒስትሩ አስገንዝበዋል። የኢንስቲትዩቱ ዳይሬክተሩ አቶ ታመነ ኃይሉ በሥልጠናው ከናይጄሪያ፣ ማላዊ እንዲሁም ከኢትዮጵያ የተለያዩ ክልሎችና ከግል ዘርፍ የተውጣጡ 17 ባለሙያዎች እንደሚሳተፉ ጠቅሰው፣ የጃፓን መንግሥት ቴክኒካል ድጋፍ ማድረጉን ጠቁመዋል።
እስከ አሁን ከየክልሉ ተውጣጥተው ስልጠናዎችን በተከታተሉ መካከለኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ ባለሙያዎች በዘርፉ ጥሩ ለውጥ እየመጣ መሆኑን በመስክ ጉብኝት ማረጋገጥ መቻሉን ተናግረዋል። ሰልጠናው 70 በመቶ ተግባር ተኮር ቀሪው ደግሞ በንድፈ ሐሳብ ላይ የተመሠረተ መሆኑን አስታውቀዋል።
አዲስ ዘመን ህዳር 9/2012
ኃይለማርያም ወንድሙ