መንግሥትና ፓርቲ የተለያዩ አካላት መሆናቸው ይታወቃል። ሆኖም የገዢው ፓርቲና የመንግሥት የስልጣን መደበላለቅ እንዳለ በተደጋጋሚ ይነገራል። ለመሆኑ በሁለቱ መካከል ያለው ግንኙነትና ልዩነት ምንድነው?
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ መምህር ዶክተር ሲሳይ መንግስቴ እንደሚሉት፣ የዳበረ የዴሞክራሲ ባህልና የተስተካከለ የመንግሥት የአስተዳደር ስርዓት ባለባቸው አገራት በምርጫ ወቅት ከሚታይ የፓርቲና የመንግሥትን ሥራ መደባለቅ ውጭ ፓርቲና መንግሥት ተለያይተው ሥራቸውን የሚሰሩበት ሁኔታ አለ። በምርጫ ወቅት በዴሞክራሲ ባህል ያደገባቸው አገራት ጭምር የፓርቲንና የመንግሥት ሥራ በጥምረት የሚሰሩበት ሁኔታ ይታያል። ይህንንም በስልጣን ላይ ያለ ፓርቲ ልዩ ጥቅም ይሉታል። ለምሳሌም የአሜሪካ የገዥው ፓርቲ ባለስልጣናት በመንግሥት ስብሰባዎችም ሆነ ዝግጅቶች ላይ ቅስቀሳ የሚያደርጉበት ሁኔታ ይስተዋላል።
በአንጻሩ እንደ እኛ አገር ለዴሞክራሲ አዲስ በሆኑ አገራት ውስጥ ያሉ ፓርቲዎች በውስጣቸው ጭምር ዴሞክራሲያዊ የማይሆኑበት ሁኔታ ስላለ ወደ ስልጣን ሲወጡ ለስልጣናቸውና ለጥቅማቸው ቅድሚያ ስለሚሰጡ የመንግሥትና የፓርቲን ሥራ ቀላቅለው የሚሰሩበት ሁኔታ መኖሩን ይስረዳሉ። የኢህአዴግን ያለፉ 28 ዓመታት ልምድ ስናይ የመንግሥት ስልጣን ላይ ያሉት ብቻ ሳይሆኑ የዕለት ተዕለት የፓርቲ ሥራ የሚሰሩ ጭምር የመንግሥት ተሿሚና ሠራተኛ ሆነው በመንግሥት በጀትና ደመወዝ የፓርቲን ሥራ የሚሰሩበት ሁኔታ መኖሩን ይገልጻሉ።
አስፈጻሚው ሁሉንም ነገር ተቆጣጥሮ የሚሄድበት ሁኔታ ስላለ ገዥው ፓርቲ በህዝብ ሀብትና ጊዜ ጭምር እየተጠቀመ ይሰራል። እንዲሁም ብዙ ሰው ለጥቅም ብሎ የፓርቲው አባል ስለሚሆን የአባላት ቁጥር እየጨመረ ይሄዳል። ይህም በአገሪቷ ዴሞክራሲው እንዲቀጭጭ አድርጓል፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎች እየደከሙ ሲሄዱ በአንጻሩ ገዥው ፓርቲን ያፈረጥማል። በኢትዮጵያ የመንግሥት የአስተዳደር ስርዓት አለመገንባቱ፣ ዴሞክራሲ ተቋማት በአግባቡ ካለመጠናከራቸውና ነጻ ሆነው እንዲሰሩ ካለማድረጉ ጋር ተያይዞ ፓርቲንና መንግሥትን አንድ አድርጎ የመመልከት ሁኔታ መኖሩንም ዶክተር ሲሳይ ገልጸዋል።
“የፓርቲና የመንግሥት አደረጃጀት አንድ አድርጎ መመልከት ስህተት ነው “የሚሉት ዶክተር ሲሳይ የመንግሥት አካል የሆነው የፌዴራል ስርዓት የሚወሰነውና የሚተዳደርው በህገ መንግሥቱ መሰረት ሲሆን በአንጻሩ የፓርቲው ውህደት የሚወሰነው ግን በፓርቲው ህገ ደንብ መሰረት መሆኑን ያብራራሉ። የብሄራዊ ምርጫ ቦርድን ማቋቋሚያና የፓርቲዎችን መመዝገቢያ አዋጅ ተከትሎ ማንኛውም ገዥም ሆነ ተቃዋሚ ፓርቲ ቢፈልግ ሊዋሀድ ባይፈልግ መለያየት እንደሚችል መብት የሚሰጥ እንጂ የፓርቲ ውህደት ከፌዴራል ስርዓቱ ጋር መገናኘት እንደሌለበትም አመልክተዋል።
ምክንያቱም የፌዴራል ስርዓቱ ሊቀየር የሚችለው በህገ መንግሥቱ ውስጥ በተቀመጠው የማሻሻያ አንቀፅ መሰረት ነው። ለምሳሌ የፌዴራሊዝም ሥርዓቱን ማሻሻል ቢያስፈልግ የፌዴራሊዝም ግንዛቤና አተገባበር መስተካከል አለበት ተብሎ የሚታመንባቸው አንቀጾች ካሉ ተለይተው ህገ መንግሥቱ በሚፈቅደው መሰረት ነው።
እንደ ዶክተር ሲሳይ ገለጻ በሌሎች አገሮች እንደ ኢህአዴግ አይነት አደረጃጀት ብዙ የተለመደ አይደለም። በሌሎች አገራት ግንባሮች ብዙ ጊዜ ግንባር ተብለው የቆዩበት ሁኔታ የለም። ግንባር ብዙ ጊዜ የተለያየ ዓላማ ይዞ አንድ የጋራ ጠላትን በትጥቅ ትግል አሸንፎ ወደ ስልጣን የመውጣት ሁኔታዎች ጋር የተያያዘ ነው። ግንባሩ አሸንፎ ወደ ስልጣን ሲወጣ ውህደት ይፈጽማል ወይም ሊለያይ ይችላል እንጂ በሌሎች ዓለም አገራት እንደ ኢህአዴግ 28 ዓመታት የቆየ ግንባር የለም።
በሰለጠኑ አገራት የፓርቲና የመንግሥት የሥራ ክፍፍሉ የተለያየ መሆኑን የሚገልጹት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ምሁሩ ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና በበኩላቸው የመንግሥት ሥራ ህግ አውጭ፣ ህግ ተርጓሚና ህግ አስፈጻሚ ተብሎ የተለየ ኃላፊነትና ስልጣን ገደብ ያላቸው ናቸው። በአንጻሩ ይህ አሰራር በአገራችን የለም። የኢህአዴግ ማዕከላዊነት አሰራርም የፓርቲና የመንግሥት ሥራ እንዲደባለቅ አድርጓል።
ኢህአዴግ በዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት ሰበብ ከላይኛው ስልጣን እስከ ቀበሌ ድረስ በመንግሥት ተቋማት የሚመደበውና የሚቀጠረው የመንግሥት ሰራተኛ በችሎታና አገሩን በመውደዱ ሳይሆን ለፓርቲው ባለው ታማኝነት ነው። በዚህ ምክንያት የመንግሥትና የፓርቲ ሥራዎች መደበላለቅ ይስተዋላሉ። በአንጻሩ በሰለጠነው ዓለም ግን የተወሰኑ የመንግሥት ስልጣኖችና ኃላፊነቶች የገዥው ፓርቲ አባላት ሊሾምባቸው ይችላል እንጂ በሌሎቹ ኃላፊነቶችም ሆነ ሙያዎች ዜጎች በእውቀታቸውና በችሎታቸው የሚመረጡበትና የሚሰሩበት ሁኔታ መኖሩን ተናግረዋል።
ለምሳሌ በአሜሪካ አገር በመንግሥት ተቋማት በሹመት የሚመደቡት የገዥው ፓርቲ አባላት ከአራት ሺህ አይበልጡም። ቀሪው የመንግሥት ሠራተኛ ግን በብቃትና በችሎታው ተወዳድሮ የሚቀጠርና በኃላፊነት የሚመደብ መሆኑን በአብነት ጠቅሰዋል። በኢትዮጵያም መንግሥት ሲለወጥ የማይለወጡ ጠንካራ የመንግሥት ተቋማትና ሠራተኞች ሊኖሩ ይገባል ሲሉ ሀሳባቸውን ሰንዝረዋል።
ከኢህአዴግ ውህደት በኋላ አህዳዊ ስርዓት ሊፈጠር ይችላል የሚል ጥርጣሪ ያላቸው ሰዎች መኖራቸውን ፕሮፌሰር መረራ አውስተው ቀድመን እንዲህ ሊሆን ይችላል ብሎ መናገሩ ከዓለም አቀፍ ተሞክሮ አንጻር አብሮ የሚሄድ አይደለም ሲሉም ገልጸዋል።
ኢህአዴግ የፈለገውን ርዮተ ዓለም መከተሉ፣ ስሙን መለወጡና መዋሃዱ ከመንግሥት አደረጃጀት ጋር የሚያገናኘው ነገር የለም የሚሉት ፕሮፌሰሩ ዋናው ቁም ነገር ኢህአዴግ የዜጎች መብት ማስጠበቁ፣ ዴሞክራሲዊ ስርዓት ማስፈኑ፣ የተሳካ ምርጫ ማካሄዱና ለህዝብ ጥያቄዎች ተገቢውን ምላሽ መስጠቱ እንደሆነ ጠቁመዋል።
አዲስ ዘመን ኅዳር 8/2012
ጌትነት ምህረቴ