. አገራትን ዘላቂ ወዳጅና ዘላቂ ጠላት በሚል አይፈርጅም፤ .የኃይል ሚዛንን ከአገር ጥቅምና ሉዓላዊነት አንጻር ይመለከታል፤ .የዜጎችን ክብር ከብሔራዊ ክብር ጋር ያስተሳስራል፤
አዲስ አበባ፡- የመደመር እሳቤ የውጭ ግንኙነት እሳቤ አገራትን ዘላቂ ወዳጅና ዘላቂ ጠላት ብሎ የመፈረጅ የተንሸዋረረ እይታን የሚቀይር መሆኑ ተገለጸ፡፡ የኃይል ሚዛንን ማስጠበቅ የሚቻለውም የኃያላንን ጎራ በመቀላቀል ሳይሆን ከብሔራዊ ጥቅምና ሉዓላዊነት አንጻር ሲቃኝ፤ የዜጎችም ክብር ከብሔራዊ ክብር ጋር ሲተሳሰር እንደሆነም ተጠቅሷል፡፡
በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ተንታኝ አቶ መሐመድ ራፊ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት በመደመር እሳቤ ሲቃኝ ለብዙ ዘመናት በዓለማችን የቆየውን ጠላትና ወዳጅ ብሎ የመከፋፈል አስተሳሰብ መለወጥ እንዳለበት ያምናል። ከፍረጃ ይልቅ በትብብር መስኮች የእድገት አጋሮች አድርጎ መስራት ላይ ያተኩራል። የኃይል ሚዛንን በተመለከተም ብሔራዊ ጥቅምንና ክብርን ብሎም ሉዓላዊነትን መሰረት ያደረገ አቅጣጫን የሚከተል ሲሆን፤ የአገራዊ ክብር መገለጫ አንዱ ዜጎች እንደመሆናቸው አገራዊ ክብርን ከዜጎች ክብር ጋር አቆራኝቶ ይመለከታል።
እንደ አቶ መሐመድ ገለጻ፤ አገርን እንደ አገር በጠላትነት የመፈረጅ፤ ቀጠናንም በተመሳሳይ የስጋት ቀጠና አድርጎ የመውሰድ የተንሸዋረረ ዕይታ ለብዙ ዘመናት ነበር። የመደመር እሳቤ ግን ይህ መቀረፍ እንዳለበት ያምናል። ምክንያቱም አገራት ጠላት ብቻ አይደሉም፤ ይልቁንም የትብብር መስኮች የእድገት አጋሮች ናቸው። ይህ ማለት ግን በአገር ውስጥም ከአገር ውጪም ብሔራዊ አንድነትን፤ ብሔራዊ ጥቅምና ክብርን የሚገዳደሩ ጉዳዮች የሉም ማለት አይደለም።
ለምሳሌ፣ ሽብርተኝነት፣ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውርና ሕገወጥ የመሳሪያ ዝውውር ኢትዮጵያ ይሄን የሚያደርግ የብቻዬ ጠላት እገሌ ነው ብላ የምትልበት ሳይሆን የሁሉም አገራት የደህንነት ስጋቶች ናቸው። በመሆኑም የመደመር እሳቤው ዋልታ ረገጥ የሆኑ ምሉዕ ዕይታ የሌላቸው አመለካከቶችን መቅረፍ ሲሆን፤ በተጨባጭ ዘላቂ ወዳጅም ሆነ ዘላቂ ጠላት በሌለበት ዓለም ላይ አገራትን በእንደዚህ አይነት መልኩ መፈረጁ እንደማያዋጣ ያስቀምጣል።
አቶ መሐመድ አያይዘው እንደገለጹት፤ የኃይል ሚዛንና የዜጎች ክብር ሌላው የመደመር እሳቤ ትኩረት ናቸው። ለምሳሌ፣ የኃይል ሚዛን እይታው ከቀዛቃዘው ዓለም ጦርነት የተለየ ሲሆን፤ ሁለት ኃያላን አገራት ባሉበት ወቅት የሚደረግ የጎራ የኃይል አጠባበቅ ሂደት ነበር። አሁን ላይ ግን በርካታ ኃያላን ባሉበት ቀጠና ዓለም ስለምትገልጽ ከየትኛው አገር ጋር ነው የኃይል ሚዛን የምንጠብቀው ቢባል ምላሽ አይገኝም። ይልቁንም ሰላም ወዳድነታችን፣ መግባባትና ትብብርን ማዕከል ማድረጋችን እንደተጠበቀ ሆኖ፤ የትኛውንም አይነት ስጋት ሊመክት የሚችል፤ የትኛውንም አይነት ጠላት ሊመልስ የሚችል ጠንካራ መከላከያ ግን ሊኖረን ይገባል ብሎ መደመር ያስቀምጣል።
ስለዚህ በመደመር እሳቤ የኃይል ሚዛን የኃያላንን ጎራ አሰላለፍ ተከትሎ የሚጠበቅ ሳይሆን፤ ከብሄራዊ ጥቅም፣ ክብርና ሉዓላዊነት አንጻር ሊከሰቱ የሚችሉ ችግሮችን በምን አይነት መልኩ መፍታትና መግታት አለብን የሚለው ላይ እንደሚያተኩር አቶ መሃመድ ጠቁመዋል።
እንደ አቶ መሐመድ ገለጻ፤ የዜጎች ክብር አንዱ የመደመር የውጭ ግንኙነት እሳቤ አስኳል ሲሆን፤ የዜጎችን ክብር ከብሔራዊ ክብር ጋራ አስተሳስሮም ይመለከታል። ምክንያቱም የምትታሰበው ታፍራና ተከብራ የምትኖር ኢትዮጵያ በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ የዜጎቿ፣ የብሔር ብሔረሰቦቿ፣ እንዲሁም የግለሰቦችና ቡድኖች ነጸብራቅ ናት። ስለዚህ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ያሉ ዜጎች ያላቸው ክብር እና የመብታቸው መከበር ነው በዓለምአቀፍ ደረጃ ኢትዮጵያ የምትፈልገውን ብሔራዊ ክብር ሊያስገኝላት የሚችለው።
ስለዚህ መደመር የዜጎች ክብርም በዛ መልኩ በትኩረት ሊሰራበት ይገባል ብሎ ያስቀምጣል።በመደመር እሳቤ ኢትዮጵያ ወዳጅም ጠላትም የለም ብላ ስታስቀምጥ፣ ከየትኛውም አገር ጋር ብሔራዊ ክብሯንና ሉዓላዊነቷን ሊያስከብር፤ የዜጎቿን ክብር ሊያስጠብቅ በሚያስችል የትብብርና ፉክክር ማዕቀፍ ውስጥ የምትጓዝበት፤ ለጎረቤት አገራት ቅድሚያ ሰጥታም ከዋልታ ረገጥ እሳቤ በመላቀቅ በሙሉ ዕይታ ብሔራዊ ጥቅሟን በማይነካ መልኩ የጋራ ተጠቃሚነትን መሰረት ያደረገ አጋርነትን ፈጥራ የምትሰራበት እሳቤ እንደሆነም አቶ መሃመድ ተናግረዋል።
አዲስ ዘመን ኅዳር 8/2012
ወንድወሰን ሽመልስ