“አጋር ድርጅቶች” የሚለው ሃሳብ የፖለቲካ ጥገኛ ከመሆን ባለፈ የህዝቡን ሁለንተናዊ ጥቅም እንዳላስጠበቀና የህዝብንም ፍላጎት ማሟላት እንዳላስቻለ የአፋር ህዝብ ፓርቲ ገለፀ፡፡ ድርጅቶቹ የተባሉትን ብቻ የሚፈጽሙ፣ በስማ በለው ሲሰሩ የነበሩ መሆናቸውንና አካሄዱም ከመገለልና ከድህነት ውጭ አንዳችም ትርፍ እንዳልነበረው ጠቁሟል፡፡
የፓርቲው ሊቀመንበር ዶክተር ኮንቴ ሙሳ ከአዲስ ዘመን ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለፁት አጋር መሆኑ በራሱ ዜጎችን አንደኛና ሁለተኛ መደብ አድርጎ የከፋፈለ ነው፡፡የአፋርን ህዝብ ጥያቄ የሚያነሳ የፖለቲካ ማህበረሰብ በሀገር ደረጃ አልነበረም የሚሉት ዶክተር ኮንቴ ፓርቲያቸውም ይህንን ክፍተት ለመሙላት ከ15 ዓመታት በፊት መቋቋሙን ተናግረዋል፡፡
“ፓርቲው ሲመሰረትም ዓላማ አድርጎ የተነሳው ማህበራዊ ፍትህን ማስፈን ነው” ያሉት ዶክተር ኮንቴ የመገንጠልም ሆነ ፌዴራሊዝምን የመቃወም ዓላማ የለውም ብለዋል፡፡ የአፋር ህዝብ በህገመንግሥቱ ለክልሎች በተሰጠው መብት መሰረት ተጠቃሚነቱ ተግባራዊ ይሁን፣ የልማቱም ተቋዳሽ፣ የፖለቲካውም ተዋናይ ይሁን በሚል ሲንቀሳቀስ እንደቆየም ጠቁመዋል፡፡
ፓርቲያቸው የፓን አፍሪካኒዝም አቀንቃኝ መሆኑን የጠቆሙት ዶክተር ኮንቴ በመሆኑም አሁን ባለው አወቃቀር በአፋር ክልል ነዋሪ የሆነ ማንኛውንም ኢትዮጵያዊ ሁሉ አቅፎ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል ብለዋል፡፡ ፓርቲያቸው አንድነትንና ኢትዮጵያዊነትን የሚያቀነቅን በመሆኑ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ተዋህደው ጠንካራ ተወዳዳሪ ቢሆኑ የተሻለ በመሆኑ እንደሚደግፉም ተናግረዋል፡፡
“የሚያስማማን ሀሳብ ከመጣ ፓርቲያችን ለመዋሃድ ዝግጁ ነው” ያሉት ዶክተር ኮንቴ “ነገር ግን መወሃድ መዋጥ መሆን የለበትም” ብለዋል፡፡ ዶክተር ኮንቴ እንዳሉት ሀገር ቤት ገብተው እንዲታገሉ ተስፋ የሰጣቸው የተገኘው ተስፋ ሰጪ ለውጥ ነው፡፡ ነገር ግን በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚታየው ሁከትና ግርግር አለመብረዱ፣ መረጋጋት አለመፈጠሩ እና መንግሥትም መቆጣጠር አለመቻሉ በኑሮ ዋስትና እና ደህንነት ላይ ከፍተኛ ስጋት እየፈጠረ ነው፡፡
“መንግሥት ስለ ሆደሰፊነቱ እንጂ ስለጥፋቶችና ስለወሰዳቸው እርምጃዎች አይናገርም” የሚሉት ሊቀመንበሩ ሆደ ሰፊነቱና የሚወሰዱ እርምጃዎች አለመጣጣማቸው በመንግሥት ላይ ትችት እያስከተሉ ይገኛሉ ብለዋል፡፡ሆኖም ሆደ ሰፊነቱ ከህገመንግሥቱና ከህጋዊነቱ ሊመነጭ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
አዲስ ዘመን ኅዳር 8/2012
በጋዜጣው ሪፖርተር