አዲስ አበባ፡- በፖለቲካ ፓርቲ የአመራርነት ቦታዎች ላይ ያለውን ዝቅተኛ የሴቶች ተሳትፎ ለማሳደግ በቀጣይ ምርጫ ብዛት ያላቸው ሴት እጩዎች እንደሚያቀርቡ አስተያየታቸውን የሰጡ የፓርቲ አመራሮች ገለፁ።
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ፓርቲ (ኢዜማ) የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ናትናኤል ፈለቀ እንደሚናገሩት፤ ኢዜማ ሴት አመራሮችን ለማሳተፍ የተጀመሩ ስራዎች አሉ። የመጀመሪያው ከፓርቲ አመሰራረቱ ጀምሮ ከእያንዳንዱ የምርጫ ወረዳዎች ተጨማሪ ሴቶችን እንዲልኩ ተደርጓል። በዚህም በብሄራዊ አስፈፃሚ ውስጥ አምስት ሴቶች ተመርጠው ገብተዋል። በቀጣይ ምርጫ የሴቶች ተሳትፎ ለማሳደግና ለማበረታታት ፓርቲው የራሱን ፖሊሲ አዘጋጅቷል። በአገር ደረጃ የስርዓተ ፆታ እኩልነትን እንዴት ማምጣት ይቻላል በሚልም ሴቶች ላይ ከሚሰሩ ድርጅቶች ጋር በትብብር እየተሰራ ይገኛል።
በአገሪቱ ሴቶችን በፖለቲካ ተሳታፊ የማድረጉ ስራ በጣም ደካማ መሆኑን የተናገሩት አቶ ናትናኤል፤ በአሁን ወቅት የመንግስት ካቢኔ ውስጥ ግማሽ ያክል ሴቶች ሲሆኑ በቀጣይነት በዚህ ሁኔታ የሚቀጥል ከሆነ የሴቶች ተሳትፎ እንደሚያድግ አመልክተዋል። ነገር ግን የፓርቲዎች አደረጃጀት ሴቶችን ያላሳተፈ ከሆነ ፍትሀዊና ዴሞክራሲያዊ የሆነ ሁኔታ አለ ማለት እንደማይቻል ገልፀዋል። ፓርቲው በቀጣይ ምርጫ በሚወዳደርባቸው አካባቢዎች የሴቶችን ተሳትፎ ለማሳደግ ጥረት እንደሚያደርግ አስረድተዋል።
የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ (አብን) ፓርቲ አደረጃጀት ኃላፊ አቶ ጋሻው መርሻ እንደሚናገሩት፤ አሁን ባሉት የፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ የሴት አመራር ሚና ዝቅተኛ ደረጃ ላይ ነው። በመንግስት መዋቅር ላይ የሴት ቁጥር ለማብዛት ተሞክሯል። በተፎካካሪ ፓርቲዎች ወስጥ ግን የሴቶች ተሳትፎ በጣም ጥቂት ነው። ለዚህ ደግሞ ፖለቲካው ሃይል የተቀላቀለበት እና ብዙ ፍትጊያ ውስጥ ያለ በመሆኑ ለሴቶች ምቹ ሁኔታ አልፈጠረም።
ፓርቲያቸው የሴቶች ተሳትፎ ለማሳደግ እንደ ጀማሪ ፓርቲ ጥሩ ሊባል በሚችል ሁኔታ እንቅስቃሴዎች እያደረገ እንደሚገኝ የገለፁት አቶ ጋሻው በዞን ደረጃ የሚገኙ የፓርቲው አመራሮች ውስጥ ጠንካራ ሴቶች ቢኖሩም አመርቂ ነው ማለት እንደማይቻል ጠቅሰዋል። በቀጣይ በሚደረገው ምርጫ ጥሩ የሚባል ተሳትፎና አቅም ያላቸውን ሴቶች በዕጩነት ለማቅረብ እንደታሰበ ጠቁመዋል። በእቅዱም ከ30 እስከ 40 በመቶ ሴቶችን በምርጫው ለማሳተፍ መታሰቡን አመልክተዋል።
የሴታዊት መስራችና አስተባባሪ ዶክተር ሲሂን ተፈራ እንደሚናገሩት፤ የፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ በተለይ በገዥው ፓርቲ ውስጥ ሴት አመራሮች ይገኛሉ። ነገር ግን በተፎካካሮ ፓርቲዎች ውስጥ ያን ያክል ሴቶች አይታዩም። ይህ ደግሞ የሴቶችችን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጎድቶታል። በአገሪቱ 51 በመቶ የሚሆነው ሴቶች ሲሆኑ እንወክላቸዋለን በሚሉት የፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ መሳተፍ ካልቻሉ ፓርቲዎቹ የሴቶችን ጥያቄ ምን ያክል አንፀባርቀዋል የሚለውን ነገር አጠራጣሪ ያደርገዋል።
አብዛኛው ተፎካካሪ ፓርቲ ሴቶች በፖለቲካ ፓርቲ ውስጥ የመሳተፍ ፍላጎት የላቸውም የሚል ምክንያት ያቀርባሉ የሚሉት ዶክተር ሲሂን፤ አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲዎች ደግሞ ብዙ ሴቶችን ሲያሳትፉ እንደማይታይና ክፍተቱ የቱጋር እንደሆነ በግልፅ እንደማይናገሩም አመልክተዋል። የፖለቲካ ፓርቲዎችና የምርጫ ህጉ የሴቶች ተሳትፎ ምን ያክል መሆን እንዳለበት አለማስቀመጡ ሴቶች እንደ ተራ አባል ለመመዝገብ ምንም አይነት ኮታ እንዳልተቀመጠላቸው ተናግረዋል። የፖለቲካ ፓርቲዎች ሴቶችን እንዲያሳትፉ ግዴታ የሚደረግበት አሰራር መፈጠር እንዳለበት አስረድተዋል።
አዲስ ዘመን ኅዳር 8/2012
መርድ ክፍሉ