በአሁኑ ወቅት በሀገራችን ዴሞክራሲን እንገነባለን እውነተኛ ፌዴራሊዝምን እናሰፍናለን፣ ነጻና ተአማኒ ምርጫ እናካሂዳለን ተብሎ እየተሰራ ይገኛል። ከዚህ ጎን ለጎንም ይህን ሂደት ለማደናቀፍ የሚሰሩ ቁማርተኛ ፖለቲከኞች ከዚህም ከዚያም ብቅ ብቅ በማለት ላይ ናቸው። ከአንዳንድ ፖለቲከኞችና አክቲቪስቶች የሚሰነዘሩ አስተያየቶችም ህዝብን በህዝብ፣ አንዱን ሀይማኖት በሌላው ላይ የሚያነሳሱ እና ግጭቶችን የሚያባብሱ ናቸው። በዚህም መተኪያ የሌለውን ህይወት በመስዋዕትነት እየከፈልን ነው።
የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት ያሰቡት እነዚህ አካላት ያለፉ የታሪክ ቁስሎችን በመቀስቀስ “ የዚህ ብሄር ስስ ብልት ይሄ ነው” ብለው በሚያሰራጩት አጀንዳ አንዱ ብሄር በሌላው ብሄር ላይ፤ አንዱ ሀይማኖት በሌላው ላይ እንዲነሳ አሁንም ሳያሰልሱ እየሰሩ ናቸው። የሚያስተላልፏቸው መልዕክቶችም ህዝብን ከህዝብ የሚያፋቅር ሳይሆን የሚያፋጅ ነው። በተለይ ወንድምና እህትማማች የሆነውን የአማራና የኦሮሞ ህዝቦችን ለማጋጨት እየተሰራ ያለው ስራ በእጅጉ ከባድና አደገኛ ነው።
ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ሀገርን የሚለውጡ የምርምርና ስርጸት፣ የአዳዲስ ሃሳቦች መፍለቂያ የነበሩ ቢሆንም አሁን ግን የብጥብጥና ግጭት ማዕከል በመሆን ላይ ናቸው። እናት ልጇን ልካ በስጋትና በሰቀቀን የምትኖርበት፣ የሀይማኖት አባቶች የሚያለቅሱበት፣ አረጋውያንና ሌሎችም የሚያዝኑበት ደረጃ ላይ ደርሰናል። አሁን አሁን ቤተሰብ ልጁን ተጨንቆ፣ ተርቦና ደክሞ አሳድጎ እና አስተምሮ ለከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ሲያበቃ የሚያስበው ተምሮ ይመረቃል ሳይሆን ዛሬ ነገ አስከሬን ይመጣልኝ ይሆን ብሎ ነው። ይሄ በጣም የሚያሳዝን ነገር ነው። ይሄ እንዲሆን የሚሰሩ በውስጥም በውጪም ያሉ አካላት በሰው ህይወት ቁማር እየተጫወቱ መሆናቸው ሊነገራቸውና በቃ ሊባሉ ይገባል።
ይህን የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት የሚሰሩ አካላት ተማሪን በተማሪ ላይ እያነሳሱ የሚያጋድሉ ነገር ግን እነሱ የማይሞቱ ናቸው። ህዝብን ከህዝብ፤ ሀይማኖትን ከሀይማኖት ለማጋጨት ገንዘብ በመመደብና ስልጠና በመስጠት እንዲሁም ሌላም ድጋፍ በማድረግ የዳር ተመልካች እንዲሁም በሰው ልጆች ስቃይ፣ ዋይታ እና እንግልት የሚሳለቁ ናቸው። ይሄንን ሁሉም ሰው ሊገነዘበው ይገባል። በተለይ እየሞተ ያለውና ለሌሎችም ሞት፣ መፈናቀልና ስደት ምክንያት የሆነው ወጣት ይሄ ክፉ ደዌ መሆኑን አውቆ ሊመክተው ይገባል።
ወጣቱ ምክንያታዊ በመሆን ነገሮችን መመርመር ባለመቻሉ አሁን የፖለቲካ ቁማርተኞች መጫወቻ ሆኗል። በተለይ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የስልጣን ጥም ያለባቸው ፖለቲከኞች መጠቀሚያ እንዳይሆኑ የተሳሳቱ ወሬዎችን በማጥራትና በስሜት ባለመንጎድ አገርና ህዝብ የሚጠብቅባቸውን ኃላፊነት ሊወጡ ይገባል።
የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት የሚሰራው በማንነት ላይ ያነጣጠረ፣ በሃይማኖት ላይ የተመሰረተ ግጭት ድምር ውጤቱ እያንዳንዱን ቤት የሚያንኳኳ እንጂ እየመረጠ የሚጎዳ ሊሆን እንደማይችል መገንዘብ ይገባል። ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚከሰተው ውጤት ደግሞ ከመቶ ዓመት በፊት ተከስቶ ነበር ተብሎ ከሚተረከውም በላይም የከፋ እንደሚሆን መገንዘብ ያስፈልጋል።
ግጭቶችን ለመከላከልና ለመፍታት የሃሳብ ልዩነቶች ላይ ውይይት ማድረግ ያስፈልጋል። ሁሉም ሰው ስለሰላም ያገባኛል የሚል አመለካከት መያዝ አለበት። በህዝብ ህይወት ላይ የሚሰራው ቁማር በሚያስከትለው ቀውስ ኢኮኖሚውም በዛው ልክ እያሽቆለቆለ መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል። ሁሉም ነገር ግጭት ወደ ማርገብ ፤ ሁሉም ነገር ወደ ፖለቲካ እንዲሆንና የዜጋውንም ስነ ልቡና ያልተረጋጋ በማድረግ አጠቃላይ ቀውስ እንዲፈጠር ጭምር እየተሰራ መሆኑን ሁሉም ሰው ተገንዝቦ ሊከላከል ይገባል። ይሄንን የክፋት ሀይሎች እኩይ ተግባር በመከላከል፣ በማውገዝ እንዲሁም ለሀገራዊ አንድነት እና ለሀገር ሰላም ሁሉም ዘብ መቆም አለበት። አጥፊዎችንም ለህግ በማቅረብ የእጃቸውን እንዲያገኙ መተባባርም ጊዜው የሚጠይቀው ግዴታ ነው።
መንግሥትም በመዋቅሩ ውስጥ ሆነው ግጭት የሚቀሰቅሱ ኃይሎችን መፈተሽና የህግ የበላይነትን ለማስከበር ከህዝቡ ጋር ተባብሮ መስራት አለበት። ኀብረተሰቡ አገሪቱን እስካሁን አፅንቶ ያቆያትን የመተሳሰብና የመከባበር እንዲሁም ሌሎች እሴቶች ለወጣቶች ማስተማር መቻል አለበት። በአጠቃላይ ግን ለፖለቲካ ጥቅም ተብሎ በሰው ህይወት ላይ የሚቆመረው የፖለቲካ ቁማር ሊቆም ይገባል።
አዲስ ዘመን ህዳር 7/2012