● ለአንድ ተንቀሳቃሽ የእጅ ስልክ እስከ መቶ ሺህ ብር ግዢ ተፈጽሟል
አዲስ አበባ፡- ለከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች በተጋነነ ዋጋ ተንቀሳቃሽ ስልክና ላፕቶፕ ኮምፒውተር የሚገዙ የመንግሥት መስሪያ ቤቶች የግዥን መመሪያና ህግ እየጣሱ በመሆኑ ህገ ወጥ መሆናቸውን የመንግሥት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ አስታወቀ፡፡ ለአንድ ባለስልጣን አንድ ስልክ እስከ መቶ ሺ ብር ግዥ መፈጸሙንም ገልጿል።
የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ማርታ ሉዊጂ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለፁት፤ ለተቀላጠፈ ሥራ በሚል የሚኒስትሮች ምክር ቤት ለከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ተመላሽ የማይሆን ተንቀሳቃሽ ስልክና የላፕቶፕ ኮምፒውተር ግዥዎችን ፈቅዷል፡፡
ይሁን እንጂ ‹‹መመሪያውን ተፈፃሚ ለማድረግ የእቃዎች ደረጃ፣ የገንዘብ ጣሪያና በጥቅል ተገዝተው ይከፋፈሉ ወይስ በየመስሪያ ቤቱ ይገዙ የሚሉና ተጨማሪ ዝርዝር መመሪያዎች ስላልተወሰኑ ምንም አይነት ግዥ እንዳይካሄድ ለሚመለከታቸው ሚኒስቴር መስሪያ ቤትና ለተጠሪ ተቋማት›› ኤጀንሲው በደብዳቤ ማሳወቁን ገልፀዋል፡፡ ነገር ግን ‹‹ለአንድ ባለስልጣን አንድ ስልክ እስከ መቶ ሺ ብር በማውጣት ግዥዎች እንደተፈፀሙ መስማታቸውን›› ገልፀው፤ ይህ አይነት እንቅስቃሴ ለግል ጥቅም ሲባል የሚደረግ በመሆኑ ህገ ወጥ ነው ብለዋል፡፡
ሁሉም የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች አግባብነት ባለው መንገድ ብቻ መጠቀም አለባቸው ያሉት ዋና ዳይሬክተሯ በተለይ ደግሞ ውድ በሆነ ዋጋ ለመግዛት መፈለግ ጤነኝነት አለመሆኑን ተናግረዋል። የሚገዙ እቃዎች ደረጃ ያልወጣላቸው በመሆኑ እንዲሁም ሕግና መመሪያን በጣሰ መልኩ የሚደረጉ ግዥዎች ተቀባይነት የለውም፡፡ ትውልድንና ሀገርን ከሚመራ አመራር እንዲህ አይነት ተግባር መፈጸም የለበትም ሲሉ አሳስበዋል፡፡
‹‹የህዝብን ንብረት ለመዝረፍ ያለመ ካልሆነ በስተቀር ሁሉም ባለስልጣን ሲጠቀምበት የነበረው ላፕቶፕ ኮምፒውተርና ተንቀሳቃሽ የእጅ ስልክ ስላለው ከመመሪያ ውጭ ለመግዛት የሚያስቸኩል ነገር የለም፡፡ የሥራ ኃላፊዎች በርካታ ንብረቶችን የሚያስተዳድሩ በመሆናቸው ሕዝብን እንዲያገለግሉ የተሰጣቸውን ዕድል በአግባብ መጠቀም ይኖርባቸዋል፡፡ በዚህ ግዜያዊ ውክልና የህዝብን ኃላፊነት በመዘንጋት የራስን ጥቅም ማካበት አመራርነትን የሚመጥን ባለመሆኑ መቅረት አለበት” ብለዋል፡፡
ዋና ዳይሬክተሯ እንዳሉት፤ መመሪያውን ተፈፃሚ ለማድረግ ከደረጃዎች ኤጀንሲና ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ጋር በጋራ እየተሰራ ነው፡፡ በቅርብም ዝርዝር መግለጫዎች ይወጣሉ፡፡ ዝርዝር መመሪያው የዘገየበት ዋናው ምክንያት ደግሞ በየጊዜው የቴክኖሎጂ እድገት ስላለ ጥራትንና ቆይታን ያማከለ እቃ ለመግዛትና ለየትኛው መስሪያ ቤት ምን አይነት እቃ ያስፈልገዋል የሚለውን ለይቶ ለማወቅ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡ እንዲሁም ግዥው በማዕቀፍ ይሁን ወይስ በየመስሪያ ቤቶች የሚለውንም ውሳኔ ለመስጠት በማሰብ መሆኑ አስታውቀዋል፡፡
አዲስ ዘመን ህዳር 7/2012
ሞገስ ጸጋዬ