አዲስ አበባ፡- በትግራይና በአማራ ህዝቦች መካከል ለዘመናት የቆዩ የሃይማኖት፣ የባህልና ሌሎች እሴቶች እንዳይሸረሸሩ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ተገለጸ። አሁን ላለው አለመግባባት ያለፈውን ትውልድ ከመውቀስ በዘለለ በሰከነ መንፈስ ተነጋግሮ ለመጪው ትውልድ የተሻለ አገር ማስረከብ ያስፈልጋል ተብሏል።
የሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ አለማየሁ እጅጉ በካፒታል ሆቴል የአማራና የትግራይ ክልሎችን ግንኙነት ለማጠናከር በተዘጋጀው የምሁራን የምክክር መድረክ ላይ እንደተናገሩት፤ በሀገር ግንባታ ዙሪያ የአማራና የትግራይ ሕዝቦች ከፍተኛ ሚናን ተጫውተዋል፡፡ በተለይ ደግሞ ጠላትን ድል በማድረግ ለሀገር ሉአላዊነት ዘመናቸውን ሙሉ በጋራ አስጠብቀዋል፡፡ ሆኖም ግን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በፖለቲካ ልሂቃኖች መካከል የተፈጠረው አለመግባባት ከሁለቱ ክልል ሕዝቦች አልፎ ለሀገር አለመረጋጋት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
የሁለቱ ህዝቦች ምሁራን የህዝቦችን አንድነት የሚያጠናክሩ ንግግሮችን ከማድረግና የእርስ በርስ ግንኙነቶችን ከማጠናከር ይልቅ ልዩነቶችን በማጉላት ሰላሟ የተጠበቀ ሀገር እንዳትኖር አድርገዋል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ እንደ ፖለቲከኞች ሀሳብ ቢሆን ሁለቱ ህዝቦች ወደ ጦርነት በገቡ ነበር ብለዋል። ነገር ግን ህዝቦቹ ምሁራኖቹን ባለመከተላቸው በደስታና በሀዘን አንድነታቸውን እንዳጠናከሩ መቀጠላቸውን ገልጸዋል፡፡
የሁለቱ ሕዝቦች ምሁራን አባቶቻቸው ደማቸውን አፍስሰው አጥንታቸውን ከስክሰው የመሰረቷት ሀገር እንደ ሀገር ጠንካራ እንድትሆን እንደምሁር ዓለም አቀፋዊ፣ አህጉራዊና ሀገራዊ ሀሳብን በማፍለቅ ለሀገር ግንባታና አንድነት መስራት እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል፡፡ ከራስ በላይ ለሀገር ቅድሚያ በመስጠት ሀገርን መታደግ እንደሚኖርባቸውም አሳስበው በተለይ ደግሞ እንደ ምሁር በሁለቱ ህዝቦች ባህላዊ የሰላም እሴቶች ላይ ጠንካራ ሥራ በመስራት የህዝቦችን ማህበራዊ ግንኙነት ማጠናከር እንዳለባቸው አመልክተዋል፡፡
የሕግ ባለሙያና የአማራ ምሁራን አባል አቶ ዮናስ ተስፋ በበኩላቸው፤ የምሁራን የምክክር መድረኩ ዋና ዓላማ በፖለቲካ አጀንዳዎችና በፖለቲካ ልሂቃኑ የፖለቲካ ጥያቄዎች ላይ ለመወያየትና ያላቸውን ልዩነቶች በውይይት ለመፍታት እንዲችሉ ለማድረግ የታሰበ ነው ብለዋል። እንዲሁም በፖለቲከኞች መካከል ያሉ ልዩነቶች ላይ በመወያየት ለመፍታት ለፖለቲካ ልሂቃኖች ምቹ የሆነ የውይይት መድረክን ለመፍጠር የታሰበ ነው፡፡
ምሁራኑ ከውይይት ውጭ አዋጭ የሆነ መንገድ እንደሌለ አውቀው ተቃርኗቸውን በሰለጠነ መንገድ መፍታት እንዲችሉ ለማድረግ መሆኑንም አስረድተዋል። ፖለቲከኞች ባላቸው ተቃርኖ ሰላማዊ መንገድን ተከትሎ አሸናፊ መሆንን ከመምረጥ ይልቅ በጡንቻ አሸናፊ ለመሆን ሙከራዎችን የሚያደርጉ ከሆነ የሀገርን ሰላምና የሁለቱን ሕዝቦች አንድነት አደጋ ላይ እንደሚጥል በማወቅ ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለባቸውም አሳስበዋል፡፡
ከመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የመጡት ዶክተር ገብረእየሱስ ተክሉ በበኩላቸው፤ የትግራይና አማራ ህዝቦች ከቋንቋ ውጪ የሚለያያቸው ጉዳይ አለመኖሩን ያነሳሉ። በእነዚህ ህዝቦች መካከል ያልነበረውን ልዩነት ለሥልጣንና ሌሎች ጥቅሞች ሲባል እንዲፈጠር ተደርጓል የሚል እምነትም አላቸው። በመሆኑም በአብሮነት እንጂ በልዩነት የሚመጣ ጥቅም ዘለቄታ ስለማይኖረው ችግሮችን በውይይት መፍታት ያስፈልጋል ብለዋል።
አዲስ ዘመን ህዳር 7/2012
ሞገስ ጸጋዬ